Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚኒስትሮቹ ስለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕቅድ ምን ይላሉ?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገሪቱ የምትመራበት የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንፎርሜሽን ዕቅድ በመጀመርያው አምስት ዓመቱ ትግበራ የተወጠኑት አብዛኞቹ ግቦች ከመንገድ መቅረታቸውን ያምናሉ፣ ይቀበላሉ፡፡ የመጀመርያው ዕጣ በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ እንዳይደገም ሥጋት የገባቸው የሚኒስትሮች ድምፅ መሰማት ጀምሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ስብሰባ ወቅትም የሚኒስትሮቹ ሥጋት ተስተጋብቷል፡፡

የቀድሞው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነርና የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከባልደረቦቻቸው ጋር የመሩት የምክክር መድረክ በአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ትግበራ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንኩ ገዥ እንደ ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣን ሳይሆን፣ እንደ ተሰናባቹ ኮሚሽነር የመሩት ስብሰባ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የዕቅዱ አተገባበር ምን ይመስል እንደነበር ብቻም ሳይሆን ቀሪዎቹን ዓመታት በምን መልኩ መጓዝ አለበት የሚለው ትኩረት የተሰጠው የውይይት ነጥብ ነበር፡፡

የየሚኒስቴሩ ሹማምንት ከወትሮው ለቀቅ ባለ የሐሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ፣ የየፊናቸውን ሲገልጹ በተደመጡበት፣ መገናኛ ብዙኃንም ሒደቱን እንደ ልብ እንዲዘግቡ በተጋበዙበት መድረክ፣ የ2007 በጀት ዓመትን መነሻ በማድረግ እስከ 2010 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ድረስ የነበረው የዕቅዱን ሒደት በስፋት ያቀረቡት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም (ዶ/ር) ነበሩ፡፡ በዕቅዱ የተዘረዘሩት አብዛኞቹ ግቦች በእስካሁኑ አካሄድ ከቀጠሉ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ መንገድ ላይ መቅረቱ አይቀሬ እንደሚሆን የሚያሳዩ አኃዞችን እያጣቀሱ አቅርበዋል፡፡

ከአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እስከ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚዘልቀው የአምስት ዓመት ዕቅድ፣ በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ብሎም የዋጋ ንረት፣ የወጪ ንግድ፣ የታክስ ገቢ፣ የመንግሥት ወጪ፣ ብድርና ዕርዳታ፣ እንዲሁም የአገሪቱ የዕዳ መጠንና የክፍያ ጫና ወዘተ ተቃኝተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ጌታቸው (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ በ2009 ዓ.ም. (በወቅቱ ዋጋ ሲተመን) ወደ 1.8 ትሪሊዮን ብር አድጓል፡፡ ይህም በ2008 ዓ.ም. ከነበረው 1.2 ትሪሊዮን ብር ኢኮኖሚ አኳያ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ አገሪቱ በኢኮኖሚው መስክ እንድታድግ ይጠበቅ የነበረው በ11.2 በመቶ ገደማ ቢሆንም፣ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. በአማካይ በ9.5 በመቶ ማደጓን አትተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በስምንት በመቶ ገደማ ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ እስካለፈው ዓመት ያደገው በ4.5 በመቶ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪ በ20 በመቶ ሲጠበቅ፣ የነበረው የግብርና ዘርፍ፣ ከዚሁ ጋር ተቀራራቢ ዕድገት ቢያሳይም አብዛኛው ማለትም እስከ 17 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ያበረከተው ግን የግንባታ ዘርፉ ሆኗል፡፡ ይህም ማለት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው 18 በመቶ ዕድገት ከአምስት በመቶ በላይ ሊራመድ አልቻለም፡፡ እርግጥ የአምራች ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ስምንት በመቶ እንዲሆን ታቅዶም ነበር፡፡ በፍጻሜው ግን ከአምስት በመቶ ፈቅ አላለም፡፡

የኮሚሽነሩ ሪፖርት በአገሪቱ ለታየው የዋጋ ግሽበት መባባስ ምክንያት ያደረገው በጥቅምት 2010 ዓ.ም. የተደረገውን የምንዛሪ ተመን ለውጥ ሲሆን፣ ከሐምሌ 2009 እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ለተከሰተው የ19 በመቶ የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት ለተፈጠረበት ክስተት ተጠያቂ የሚያደርገው የምንዛሪ ተመኑን ጨምሮ የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ነው፡፡ ምግብ ነክና ሌሎች ሸቀጦች እንደ ልብ ሊዘዋወሩ አለመቻላቸውም ችግሩን አባብሶታል፡፡ 

እንዲህ ያሉትን ጨምሮ በርካታ ነጥቦችን በሪፖርት ያቀረቡት ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው፣ በዕቅዱ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት ፍጥነትና ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ነባሩ ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ‹‹በእስካሁኑ አካሄድ ከቀጠልን ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ ነው፤›› በማለት በሪፖርቱ የቀረቡትን ሥጋቶች አጠናክረዋል፡፡

የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ታሳቢ ካደረጋቸው መነሻዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ትክክል ያልነበሩ ናቸው ሲሉ ከጠቀሷቸው ውስጥ፣ የድርቅ መከሰትና መጠኑ እንደተከሰተው መጠን እንደሚሆን ያልተጠበቀበት አንዱ ችግር ነበር፡፡ ‹‹የፖለቲካ ትኩሳትና ግጭቶች በተወሰነ ደረጃ በዕቅዱ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፉም በኢኮኖሚው ላይ ግን ወሳኝ ተፅዕኖ ያሳረፉበት…›› ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ እስከ ዓምና መጨረሻ ድረስ 863 ዶላር ቢደርስም፣ አሁንም ድረስ ከ23 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖርባት አገርና የገነባችው ኢኮኖሚም፣ በወጪ ንግድ መቀዛቀዝ፣ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ እጥረት አደጋ ውስጥ የገባበት ወቅት ስለመሆኑ የቀድሞው ኮሚሽነር አብራርተዋል፡፡  

‹‹ትራንስፎርሜሽን አልመጣም›› 

አገሪቱ ኢኮኖሚ ከግብርና ተኮር ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር እንዲሸጋገር፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛት የሚመረቱበት ኢኮኖሚ እንዲሆን የሚያስቡት የየአምስት ዓመታቱ ዕቅዶች በወረቀት ላይ የቀሩ የሚመስሉበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው የአገሪቱ ሚኒስትሮች ሲጠቃቅሱ ተደምጠዋል፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላለፉት 15 ዓመታት ያህል ጥሩ ለውጥ እያሳየ ቢመጣም፣ የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ለአደጋ ተጋላጭነቱ እያየለበት መምጣቱን አትተዋል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው ለውጥና ዕድገት የታሰበውን ያህል እንዳልሆነ፣ በግብርና መስክ የሚጠበቀውም ቢሆን ሊሳካ እንዳልቻለ፣ ለወጪ ንግድ መዋል የሚገባው ምርት እንዳልጨመረ፣ እንዲጨመርምር ተገቢውን አመራር መንግሥትና የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳልሰጡ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጤናማነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ችግሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ የውጭ ዕዳ መጠን እየጨመረ በመምጣቱም የዓለም የገንዘብ ድርጅት  (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያን ከፍተኛ የብድር ዕዳ ጫና ካለባቸው አገሮች መደብ መልሶ እንዳስቀመጣት ይናገር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከከፍተኛ የብድር ዕዳ ጫና ካለባቸው አገሮች ተርታ የወጣችው ከሰባት ዓመታት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡

እንዲህ ያሉ መነሻዎች በቀረቡበት ውይይት ወቅት ከሚኒስትሮች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ጭብጥ ያላቸው፣ አኃዛዊ የሙግት ነጥቦችን በማንሳት ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ እንደ መጀመርያው ‹‹እንዳይከሸፍ›› ያሳሰቡባቸው ሐሳቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እንደ ሚኒስትር ጌታሁን (ዶ/ር) መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ ካልመጣባቸው ምክንያቶች ውስጥ አገሪቱ ያላትን ሀብትና አቅም ካለመጠቀሟ ይመነጫል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ከ110 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ውስጥ እሳቸው የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት (ኤፍኤኦ)ን አኃዝ ጠቅሰው እንዳቀረቡት 36 በመቶው መታረስ የሚችል መሬት ነው (እንደ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) አኃዝ እስከ 60 በመቶ የሚደርሰው መሬት ሊታረስ የሚችል ነው)፡፡  

ሚኒስትር ጌታሁን (ዶ/ር) እንደሚገልጹት ሊታረስ ከሚችለው መሬት ውስጥ እስካሁን የታረሰው 16 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱ ካላት ሊታረስ የሚችል መሬት ውስጥ ምን ያህሉ እንደሚታረስ አለመጥቀሱ፣ የመስኖ እርሻን አለማሳየቱ የዕቅዱ ችግሮች ናቸው፡፡

እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ችግር በዚህ አይወሰንም፡፡ የምርታማነትም ችግር ሌላው ኢኮኖሚያዊ መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው አገሮች ተርታ ትመደባለች ያሉት ሚኒስትር ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የዓለም አማካይ የምርታማነት ደረጃ በሔክታር ስድስት ቶን ምርት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን 2.4 ቶን በሔክታር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በሔክታር እስከ 12 ቶን የሚያመርቱ አገሮች እንዳሉም አስታውሰዋል፡፡ ሚኒስትሩ አላበቁም፡፡ ኢትዮጵያ 59 ሚሊዮን የሚቆጠር የቀንድ ከብት ሀብት ቢኖራትም፣ የወተትና የሥጋ ምርት እጅግ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ‹‹እየተሠራ ያለውን ሥራ እንወቀው፡፡ ግብርና መሠረታዊ ክለሳ ይፈልጋል፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ከሽፏል፡፡ ሁለተኛውም እንዳይከሽፍ የሚኖሩትን ሥራዎች ከወዲሁ እንያቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ግብርናው ብቻም ሳይሆን፣ ኢንዱስትሪው ዘርፍም ችግሮች እንዳሉበት ያሳዩት፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሀብት ፈጠራ ይልቅ የሰው ጉልበት ላይ መመሥረቱን በመተቸት ነበር፡፡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሰው ጉልበትን በመውሰድ የተመሠረተ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ያወጣል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ጌታሁን ሁሉ ሌሎችም ሚኒስትሮች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ አፈጻጸሞችና ችግሮቹ ዙሪያ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ኡባህ ሞሐመድ በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የቱንም ያህል ቢሮጥ የማይደረስባቸው ዕቅዶች እንዴት ይታያሉ? በማለት የጠቀሱ ሲሆን፣ ‹‹የአምስት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸሞች በየዓመቱ ቢፈተሹ ኖሮ አሁን የሚገኝበት ችግር ላይ አይወድቅም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በዕቅዱ ውስጥ የተካተቱት ግቦች የተለጠጡና ወቅታዊ ጉዳዮችን በአግባብ ያልፈተሹ ከመሆናቸውም በላይ ዕቅዱ ላለመሳካቱ ‹‹መጠየቅ የነበረባቸው አካላት በአግባቡ ያልተጠየቁበት ነው፤›› ብለውታል፡፡ የአፈጻጸሙ ችግሮች ከኃላፊዎች ጋር መያያዝ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

የ‹ምፅዋት ኢኮኖሚ› አንድምታዎች

እንዲህ ያሉ ትችቶች የተስናገዱበት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዞ፣ አደጋ ላይ ለመሆኑ አንደኛው ምክንያት አገሪቱ ያለባት የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ እጥረት ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ስድስት ወራት ብቻ ለብድር ዕዳ ክፍያ ከ688 ሚሊዮን ዶላር በላይ መከፈሉን የኮሚሽኑ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ በብድር ዕዳ ጫና ሳቢያም ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ተቀዛቅዘዋል፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በ2011 በጀት ዓመት እንደማይገነቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡

የአገሪቱ የወጪ ንግድ በ2.9 ቢሊዮን ዶላር ቢወሰንም፣ ለገቢ ንግድ የሚወጣው ግን እስከ 16 ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ ይህም የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት እያሰፋው መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑ ሲነገር ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ የሰሞኑን ያህል መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ለመሆን የበቃ አይመስልም፡፡ የመንግሥትን ትኩረት በማግኘቱም ጭምር ጉዳዩ ከመነጋገሪያነት አልፎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ አስከትሏል፡፡ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ገንዘቦችን ያከማቹ ወደ ባንክ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እየወሰዱ እንዲያስገቡ ‹‹ኋላ ሳትነግሩን እንዳትሉ፤›› ማለታቸውን ተከትሎ በየጠርዙ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ባንኮች እየጎረፈ፣ ሲሻውም በየኬላው ወደ ውጭ ሊሸሽ ሲል እየተያዘ ስለመሆኑ እየተሰማ ነው፡፡

ከእንዲህ ያሉት ዕርምጃዎች ቀደም ብሎ ግን ሁለት ዓበይት ጉዳዮች አይዘነጉም፡፡ ይኼውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሾሙ ሰሞን ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሦስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል መገባቱና አንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ አገሪቱ ካዝና ተቀማጭ የመደረጉ ዜና ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖረው ኢትዮጵያ ያደረጉት ጥሪና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከቀን ፍጆታው አንድ ዶላር በመቆጠብ ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የጠየቁበት፣ የንዋየ አደራ (አንቺንአሉ መኮንን የተባሉ ግለሰብ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ትረስት ፈንድን ንዋየ አደራ ባሉት ፍቺ መሠረት) አሠራር እንደሚቋቋም አስታውቀው ነበር፡፡

ይህን ጉዳይ የታዘቡ አስተያየት ሰጪዎች ‹‹የምጽዋት ኢኮኖሚ›› የሚል ቅጽል ፈጥረውለታል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ዘለቄታዊነትም ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚሁ ስለንዋየ አደራ ጉዳይ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለዚህ ሥራ የሚያግዝ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ ከመግለጽ በቀር ብዙም አልጠቀሱም፡፡ ወደ ባንኮች እየገባ ስለሚገኘው የገንዘብ መጠን ብዛትም ወደፊት እንደሚገለጽ በመጠቆም ተቆጥበዋል፡፡

አገሪቱን የኢኮኖሚ አቋም እንደ አስተያየት ሰጪዎች አባባል ከ‹ምጽዋት› ወደ ልማት እንዲያተኩር፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመነጭ ለማድረግና አምራችነቱ እንዲረጋገጥ ግብርና ላይ መሥራት ወሳኝ ዕርምጃ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ አብዛኛው የአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ የሚያነሳቸው መሠረታዊ የቴክኖሎጂ (ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችና የምርት መገልገያዎች) አቅርቦት ችግሮች እንዲቀረፉለት መጠየቁን ይናገር (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡

ኢኮኖሚው ዶላር የማመንጨቱ ሚናም የመንግሥት ትልቁ ትኩረት እንደሆነ፣ ይህም የማንኛውም አገር የኢኮኖሚ ህልውና የተመሠረተበት ዘርፍ በመሆኑ የሞት ሽረት ጉዳይ ስለመሆኑ፣ ኮሪያዎች፣ ቻይናዎችና ሌሎችም በፍጥነት ያደጉ አገሮች ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው መነሻው ወደ ውጭ የሚልኩት ምርትና የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ አስተዋጽኦ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች