[አንድ ጋዜጠኛ የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነህ?
- ክቡር ሚኒስትር በጣም አስቸገሩኝ እኮ፡፡
- ምን አደረግኩ ደግሞ?
- በስንት መከራና ጭቅጭቅ እኮ ነው የተገኙት፡፡
- ምን ፈልገህ ነው ለመሆኑ?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝብ እኮ ከእርስዎ ብዙ ይጠብቃል፡፡
- ሰውዬ ከዚህ በላይ ልፈንዳልህ እንዴ?
- ፍንዳታን ምን አመጣው?
- ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ልሁንላችሁ?
- ሕዝብ እኮ ስለሚሠሩት ሥራ መግለጫ እንዲሰጡ ይፈልጋል፡፡
- የምን መግለጫ ነው?
- ይኸው እኛ ራሳችን ደብዳቤ ብናስገባ፣ የሕዝብ ግንኙነቱን ብናናግር ምንም ዓይነት ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
- ከዚህ በላይ ምን ዓይነት መግለጫ ነው የምትፈልጉት?
- ክቡር ሚኒስትር አልፎ ተርፎ በግል አማካሪዎ በኩል ቃለ መጠይቅ እንዲሰጡን ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
- አንተ ጋዜጠኛ ነህ አይደል?
- ስለሱማ አይጠራጠሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አገሪቱ ውስጥ ምን ዓይነት ሥራ እየሠራሁ እንደሆነ እያወቅህ የምን መግለጫ ነው የምትለኝ?
- ስለሚሠሩት ሥራ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለብዎ፡፡
- በየጊዜው ጋዜጣዊ መግለጫ ይላክላችኋል አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ጋዜጠኛ እንጂ በቀቀን አይደለሁም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- እርስዎ ያሉትን እንደ በቀቀን እየደገምኩ አላስተላልፍም፡፡
- ታዲያ ምንድነው የፈለግከው?
- ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
- ለምንድነው ጋዜጣዊ መግለጫ የፈለግከው?
- ለሚሠሩት እያንዳንዱ ሥራ ተጠያቂ መሆኑዎን ያውቃሉ መቼም?
- አገሪቱ ውስጥ የሚገርም ለውጥ እንዳለ ትጠራጠራለህ እንዴ?
- እኔም እኮ የምፈልገው ለውጡን በተመለከተ ጥያቄ ለመጠየቅ ነው፡፡
- በዚህ ወቅት እኮ ካለው የሥራ ብዛት የተነሳ ቅዳሜና እሑድ ሳንል እየሠራን ነው፡፡
- እኔም እኮ ስለምትሠሩት ሥራ ለመጠየቅ ነው የመጣሁት፡፡
- ለወሬ ጊዜ የለንም ስልህ?
- ክቡር ሚኒስትር ለውጡ እኮ ግልጽነትና ተጠያቂነትን አምጥቷል እያላችሁ አይደል እንዴ?
- በሚገባ እንጂ፡፡
- ስለዚህ ለሚዲያው ግልጽ ሆነው ስለሚሠሩት ሥራ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡
- አንድ ነገር ስላልገባህ እኮ ነው፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- አንድ ፊልም ሲሠራ የሚያልፍበትን ሒደት እንይ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የፊልሙ ዳይሬክተር የፊልሙን ሒደት ለተመልካቾቹ ይፋ ያደርጋል?
- እ. . .
- በዚያ ላይ ዳይሬክተሩ በፊልሙ ውስጥ የተሳተፉትን ተዋናዮች እንዴት እንደመረጣቸው ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ አንድ የፊልም ዳይሬክተር በፊልሙ ውስጥ የሚያደርገውን ነገር ለሕዝብ እንደማይገልጽ ሁሉ፣ እኛም ስለምንሠራው እያንዳንዱ ነገር ለሕዝቡ ማሳወቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡
- እደዚህ ከሆነማ መሠረታዊ ችግር አለ ማለት እኮ ነው፡፡
- የምን ችግር?
- ለለውጡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ወዴት አሉ?
- እሱማ ፊልሙ ለሕዝቡ ይፋ ሲደረግ መታወቁ አይቀርም፡፡
- አሁን ገባኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው የገባህ?
- ምን እየሠራችሁ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡
- ምን እየሠራን ነው?
- ፊልም!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው አስጠሩት]
- አንተ ምን ሆነህ ነው?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እንደምትመስል ራስህን አይተኸዋል?
- ምን ሆንኩኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ አግብተሃል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር ምነው?
- ታዲያ እንደዚህ ሆነህ ከቤትህ ስትወጣ፣ ሚስትህ ዝም ብላ አየችህ?
- ምን ሆኛለሁ ግራ አጋቡኝ እኮ?
- ለማንኛውም በሸሚዝህ ቁልፎች ዓይኖቼን እንዳታጠፋኝ፡፡
- ሸሚዜ ምን ሆነ ክቡር ሚኒስትር?
- ቦርጭህ እኮ የሸሚዝህን ቁልፎች ሊያስፈነጥራቸው ነው፡፡
- መቼም ቀልደኛ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ እየቀለድኩ አይደለም፣ ራስህን በመስታወት ተመልክተኸዋል?
- ይኼን ያህል ወፍሬያለሁ እንዴ?
- የአንተ ደግሞ ቅርፅ የሌለው ውፍረት ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላው ሰውነትህ ቀጠን ብሎ ቦርጭ ብቻ ነው ያለህ፡፡
- ታዲያ ምን ይጠበስ?
- ዝም ብለህ ማታ ማታ ድራፍትህን ስለምትልፍ እኮ ነው እንደዚህ ቦርጫም የሆንከው፡፡
- እንከባበር እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
- እንደ አንተ ዓይነት ሰው እንዴት ነው እዚህ ሊሠራ የሚችለው?
- ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር?
- እንደ አንተ ዓይነት ቅርፅ የሌለው ውፍረት ያለው ሰው እንዴት ከእኛ ጋር ይሠራል?
- ከመቼ ጀምሮ ነው ውፍረት የሥራ ብቃት መመዘኛ የሆነው?
- በአሁኑ ወቅትማ ዋነኛ መመዘኛ መሥፈርት ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንደ ኢሕአዴግ እኮ ግራ የሚያጋባ ፓርቲ የለም፡፡
- እንዴት?
- አንድ ሰሞን ታማኝነት ዋነኛ መመዘኛ ነው ይል ነበር፣ አሁን ደግሞ ውፍረት የሥራ መመዘኛ ሆነ?
- ሰሞኑን አለቃችን ምሁራንን ሰብስበው ፑሽአፕ እንዳሠሯቸው አልሰማህም?
- ስለዚህ ከዚህ በኋላ የመንግሥት ሠራተኛ አትሌትና ቦክሰኛ መሆን አለበት እያሉ ነው?
- አሁን ወሬውን ትተህ አሥር ፑሽአፕ ውረድ፡፡
- ምን?
- እዚህ ፊቴ ነው እድትሠራልኝ የምፈልገው?
- ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ለነገሩ በዚህ ቦርጭ ልትሠራው እንደማትችል ገብቶኝ ነበር፡፡
- በጣም አዝናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን በአስቸኳይ ከመንግሥት ተጨማሪ በጀት ማስለቀቅ አለብን፡፡
- የምን በጀት?
- ጠቅላላ ሠራተኛችን መግባት አለበት፡፡
- የት ነው የሚገባው?
- ጂም!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለሚስታቸው ስልክ ደወሉ]
- አሪፍ የቢዝነስ ሐሳብ አለኝ፡፡
- የምን የቢዝነስ ሐሳብ?
- እኛ ቢሮ አካባቢ በፍጥነት ቤት ተከራዩ፡፡
- እናንተ አካባቢ እኮ ዶላር ለመመንዘር ብዙ አይመችም፡፡
- ቤቱን የምትከራይው ዶላር ለመመንዘር አይደለም፡፡
- ታዲያ ለምንድነው?
- እንድትከፍቺ ነዋ፡፡
- ምን?
- ጂም!
[ክቡር ሚኒስትር የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የነበረና በቅርቡ ጥሪ ከተደረገለት ሰው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- እንኳን ደስ አለህ?
- ለምኑ ይሆን ክቡር ሚኒስትር?
- መቼም አለቃችን ያቀረቡትን ጥሪ ሰምተሃል?
- የትኛውን ጥሪ?
- ተባራችሁ የነበራችሁ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች እንድትመለሱ ጥሪ ቀረበላችሁ አይደል እንዴ?
- እኔ እንኳን ለዚህ ጥሪ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነኝ፡፡
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር የተባረርነው በግፍ ቢሆንም፣ እኔ አሁን የተሻለ ነገር አለኝ፡፡
- ከመምህርነት ውጪማ የተሻለ ነገር የለም፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን እያልክ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ከተባረርኩ በኋላ እኮ የንግድ ሥራ ውስጥ ገብቼ በጣም የተሳካ ሕይወት እየመራሁ ነው፡፡
- እሱንማ እኔ አውቃለሁ፡፡
- ስለዚህ በሥራው መቅረት ሕይወቴ ብዙም አልተጎዳም፡፡
- አሁን ግን የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም አለብህ፡፡
- የቱን አጋጣሚ ክቡር ሚኒስትር?
- ቀጣዩን ትውልድ ማስተማር አለብህ፡፡
- ምንድነው የማስተምረው?
- በፊት ምን ነበር የምታስረምረው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ጭልጥ ብዬ ንግድ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡
- ብትገባስ ታዲያ?
- ስለዚህ ማስተማር አልችልም፡፡
- ቢያስ እንኳን ስለሕይወት ስኬትህ ለምን አታስተምርም?
- ይቅርብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ኃላፊነት አለብህ እኮ፡፡
- የምን ኃላፊነት?
- ቀጣዩን ትውልድ የማስተማር ነዋ፡፡
- እሱማ የእናንተ ኃላፊነት ነው፡፡
- እና አላስተምርም እያልክ ነው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትንሽ የምታገኘው ገንዘብ እንኳን አያሳሳህም?
- የምን ገንዘብ ክቡር ሚኒስትር?
- ያው ተመለሱ ከተባላችሁ እስከዛሬ የነበራችሁ ደመወዝ ከተከፈላችሁ በአንዴ ሚሊየነር ትሆናላችሁ እኮ?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ አሁንም ሚሊየነር ነኝ፡፡
- ቢሆንም ሌላ ሚሊዮን አትጠላም መቼም?
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ማስተማር እኮ ሚሊየነር አያደርግም፡፡
- ታዲያ ምንድነው ሚሊየነር የሚያደርገው?
- መዝረፍ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]
- አንድ ነገር ላስቸግር ነበር የመጣሁት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ጊዜ የለኝም፡፡
- ይኼ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በጣም ትልቅ ጉዞ ነው እያዘጋጀን ያለነው፡፡
- እኔም የመጣሁት በጉዞው ላይ ለመነጋገር ነው፡፡
- ምንድነው የምንነጋገረው?
- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አሜሪካ ልትሄዱ ነው አይደል?
- አዎን ምነው?
- ያው እሳቸውን አጅበው የሚሄዱ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሉ አይደል?
- እሱማ የሚያጅቧቸው ባለሥልጣናት ይኖራሉ፡፡
- እኔንም አብራችሁ እንድታካትቱኝ ነዋ፡፡
- ኪኪኪ. . .
- ምን ያስቅሃል?
- ክቡር ሚኒስትር አሁንም አሜሪካ ብርቅዎ ነው?
- ስማ አሜሪካ ለቁጥር የሚያዳግት ጊዜ ነው የሄድኩት፡፡
- ታዲያ አሁን ለምን መሄድ ፈለጉ?
- መደመሬን ለማሳየት ነዋ፡፡
- ከተደመሩ እዚያ ድረስ ለምን መሄድ ፈለጉ?
- መደመሬን በተግባር ለማሳየት ነው፡፡
- እዚህም ሆነው መደመርዎን በተግባር ማሳየት ይችላሉ እኮ?
- እዚያ የምሄድበት ዓላማ አለኝ፡፡
- የቤዝ ቦል ጨዋታ ሊያዩ ነው?
- አትቀልድ እንጂ?
- ታዲያ አሜሪካንን ሲጎበኙ ሲልከን ቫሊን አላየሁትም ብለው ነው የሚሄዱት?
- ለምን ትቀልዳለህ?
- አሜሪካ ታዲያ ለምን መሄድ ፈለጉ?
- መደመሬን በተግባር ለማሳየት አልኩህ እኮ፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላችሁን ዶላር አምጡ አላሉም?
- አዎን ብለዋል፡፡
- ስለዚህ የእሳቸውን ጥሪ ተቀብዬ መደመር ፈልጌ ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- አሜሪካ መሄድ የምፈልገው ለዚሁ ነው፡፡
- ለምኑ?
- ላመጣው ነዋ፡፡
- ምኑን?
- ዶላሩን!