Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርለማሰባሰብ በታቀደው የዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ላይ የተነሱ መሠረተ ቢስ ሥጋቶችና ተግዳሮቶች

ለማሰባሰብ በታቀደው የዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ላይ የተነሱ መሠረተ ቢስ ሥጋቶችና ተግዳሮቶች

ቀን:

በዮሐንስ ወልደገብርኤል

በቅርቡ ግዙፍና ሰፊ ሥልጣን ያለው የሚመስል አዲስ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የሚያቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ፣ የምክር ቤቱ አባላት በረቂቁ ላይ ውይይት በማድረግ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የሕግ፣ የፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ልከውታል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም በረቂቅ አዋጁ ላይ ገንቢ ሐሳቦች፣ ግብዓቶችና አስተያቶችን ለማሰባሰብ በመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 9 ሰዓት ድረስ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ የማኅበራት ተወካዮችና ግለሰቦች ጭምር ተሳትፈውበት ልዩ ልዩ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡

ከብዙ መሰል የውይይት መድረኮች በተለየ ሁኔታና በርካታ ታዛቢዎችን በአስገረመ መልኩ የመመርመርና የዓቃቢያነ ሕግነት ሥራዎችን ከመደበኛ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ ተቋማቶች ተገምሶ፣ በየመሥሪያ ቤቶቻቸው ማቋቋሚያ ሕግጋት ላይ እንዲሰጣቸው የተደረጉትና ቀድሞ የሞተው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ወራሽ ከሆነው ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥርና ክትትል ውጪ፣ ማንም ሃይ ሳይላቸው፣ እንደ ልባቸው በሥልጣናቸው ሲጠቀሙባቸውና ሲገለገሉባቸው የቆዩት የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቢያነ ሕግና ሌሎች ሠራተኞቻቸው በንቃትና በትጋት ጉልህ ተሳታፊ ሆነው ውለዋል፡፡

- Advertisement -

ዓቃቤ ሕግ የሕግ አስከባሪና የሕዝብ ጥቅም ጠባቂ፣ ሕዝብን በመወከል በገለልተኝነት የሚከሰውን ተጠርጣሪ ጨምሮ የማናቸውንም ዜጎች የሰብዓዊ መብት ጠባቂና አስጠባቂ፣ ለሙያው፣ ለፍትሕ ሥርዓቱና ለሕግ የበላይነት ጥበቃ ቀደምት ተቆርቋሪና ቀናዒ መሆን ያለበት ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገሪቷ የወንጀል ፍትሕ ትክክለኛውን መስመርና አቅጣጫ እንዲይዝ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ ዓቃቢያነ ሕጉ በረቂቅ ሕጉ ላይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ በብዛት መገኘታቸው ሙያውም ሆነ ሕጉ ያስገድዳቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በውይይቱ ወቅት እንደታየው ከእነኚህ ተቋማት የመጡት ሠራተኞች በአነሷቸው ጥያቄዎች በእጅጉ ሲያሳስባቸው የነበረው ሕግ የማስከበር ተግባር፣ የወንጀል ሕጎችና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ተሰባስቦ፣ ወጥና አንድ ዓይነት በሆነ መልኩ ተፈጻሚ ስለሚሆንበት፣ እንዲሁም መላውን የአገራችንን ዜጎች በምርመራና በክስ ሒደት ስለሚኖራቸው የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ሙያው ስለሚያድግበትና ስለሚበለጽግበትና በሥልጣን አተገባበሩ ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ ጭብጦች፣ ወዘተ. ሳይሆን ይልቁንም እስካሁን ድረስ ለየመሥሪያ ቤቶቹ ተሰጥተው የነበሩት ሥልጣኖቻቸው ሊቋቋም ወደታሰበው  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መተላለፉ ስለሚኖረው አሉታዊ አንድምታ ነበር፡፡

ዓቃቢያነ ሕጉ በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደታሰበው የመመርመርም ሆነ የመክሰስ ሥልጣኖች ከየተቋማቱ ከተገፈፉ ‹‹የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያሽመደምድና ጥርስ አልባ የሚያደርገው ስለመሆኑና በግብር አሰባሰብ ላይም ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑ›› ከመገለጹም በላይ፣ በአንድ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊ እንደተገለጸው ‹‹የሕግ ማስከበሩ ሲጠነክር ገቢ ይጨምራል፣ ሲላላ ይቀንሳል ሕገወጥነትም ያስፋፋል›› የሚሉና መሰል ልዩ ልዩ ክርክሮች አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ጭራሹን የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ በሚቋቋመው በአዲሱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውስጥ የእነኚህ ተቋማት ዓቃቢያነ ሕግ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ረቂቅ ሕጉ ያስቀመጣቸው የቅጥር ማበጠሪያ ሥነ ሥርዓቶችና ቅድመ ሁኔታዎች ለሥራ ዋስትናቸው ሥጋት ላይ እንደጣላቸው በመግለጽ፣ በሙያቸው አግባብ ሕዝብን በመወከል በረቂቅ ሕጉ ላይ ማንሳት ከሚገባቸው አንገብጋቢ ጭብጦች ያፈነገጠ የግል ጉዳያቸውንና ጭንቀታቸውን ሲጠይቁ ተሰምተዋል፡፡

መክረውና ዘክረው በረቂቅ አዋጁ ላይ በትጋት ለመሳተፍ የመጡት የሚመስሉት እነኚህ የኮሚሽኑና የባለሥልጣኑ ሠራተኞች፣ ተቋሞቻቸው የሚያከናውኑዋቸውን ሥራዎች ባህሪያት ‹‹የተለዩ›› መሆናቸውን፣ ‹‹ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡና ውስብስብ መሆናቸውን›› በማስረዳት የተከራከሩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ቢያንስ በአንድ የኮሚሽኑ ሠራተኛ እስካሁን የነበረውን ‹‹ስኬታማ የፀረ ሙስና ትግል›› እንዳይቀለበስና ጥላ እንዳያጠላበት በመግለጽ ለራስ በራስ በተነገረ የምሥራች መልዕክት “Self Congragulatoy Message” ለመከራከር ተሞክሯል፡፡

ሌላው አስገራሚው የዕለቱ ክስተት የነበረው በረቂቅ አዋጁ ላይ ለቀረቡት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥና ማብራሪያ እንዲቀርብ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕድሉን ሕጉን ለአዘጋጀው አካል ሲሰጡ፣ የኮሚሽኑ ተወካዮች የረቂቅ ሕጉ አርቃቂዎች ይህ ዕድል ሊሰጣቸው እንደማይገባ ይልቁንም በዕለቱ መፈጸሙ የሚገባቸው ወይም ያለባቸው ኃላፊነት ‹‹የሚሰጣቸውን ሐሳብና አስተያየት መቀበል›› እንጂ፣ ለጥያቄዎች መልስ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለባቸው ተደምጧል፡፡ በሌላም በኩል ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች መልስም ሆነ ማብራሪያ መስጠት ሳያስፈልግ አስተያየትና ሐሳብ መስጠቱ ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት የኮሚሽኑ ሠራተኞች አድማ በሚመስል ሁኔታ ከሰብሳቢው ጋር አተካራ መፍጠራቸው ታይቷል፡፡ ውድ ጊዜያቸውን መስዋዕት በማድረግ ካለምንም ጠባብ የጥቅም ወይም የሥልጣን ፍላጎት ሙያዊ አስተዋፅኦ ለውድ አገራቸው በማድረግ ልምድና ዕውቀታቸውን ለማካፈል የመጡትን አንጋፋና ጎልማሳ ሙያተኞችና ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችን ባለማክበርና ከቁም ነገር ባለመቁጠር ጭቅጭቅ ቢፈጥሩም፣ የውይይቱ ሰብሳቢ በትዕግሥትና በማቻቻል መንፈስ መድረኩን የፓርላማው የሕግና የአስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በረቂቁ አዋጅ ላይ ለሚያደርገው ዝርዝር ዕይታ የሚረዳውን ሐሳብና አስተያየት ለማሰባሰብና ለማዳበር መጥራቱን ለማስታወስ ከመገደዳቸውም በተጨማሪ፣ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ፍላጎት በብዙኃኑ የድምፅ ብልጫ ፍላጎት ቀሪ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ይህ ጸሐፊ በመንግሥት መዋቅር ሥር ባሉት ተቋማትና ሠራተኞቻቸው መካከል የዚህ ዓይነት የሐሳብ ልዩነት በይፋ በፓርላማው ሲደረጉ በነበሩ መሰል ውይይቶች ላይ እምብዛም በብዛት ገጥሞት የማያውቅ ቢሆንም፣ በእጅጉ የሚመኘውና እንዲበረታታ የሚፈልገው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የውይይቱ መሠረታዊ ጭብጥ በሆነውና የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ተመልሰው እንደ ቀድሞው ወደ እናት መሥሪያ ቤቶቻቸው እንዲሰባሰቡ በሚያደርገው ረቂቅ ሕግ ላይ፣ የኮሚሽኑም ሆነ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ተቀባይነት ካላቸው ሕጋዊና ንድፈ ሐሳባዊ ምክንያቶች ውጪ በለሆሳስ አልፎ አልፎም ስሜት በተቀላቀለበት ሁኔታ ሲቃወሙ መስማቴና መመልከቴ፣ እስካሁን ተቋማቱ የመመርመርንም ሆነ የመክሰስ ሥልጣናቸውን ፍፁም ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ ሲጠቀሙበት ለመቆየታቸው ሥጋትን አሳድሮብኛል፡፡

እነኚህ የመመርመርና የመክሰስ መሠረታዊ ሥልጣኖች በአገራችን ዜጎች ሰብዓዊና የንብረት መብቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ አንድምታ የሚያስከትሉ በመሆናቸው፣ ሥልጣንና ኃላፊነቶቹ እንዲሁም ተግባራዊ አፈጻጸማቸው የሕዝብን መብት በሚያስጠበቁ አግባቦች፣ ተጠያቂነት ሊያስከትሉ የሚገባቸውና ቁጥጥር ሊለያቸው የማይገባ ከባድ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሥልጣኖች ከተቋማቱ ሊወሰዱ አይገባም የሚለው መከራከራያ ሲቀርብ ዕውን ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለተከሰሱና እንዲሁም ለተበደሉ ሰዎች ባላቸው ሰብዓዊ ስሜትና ተቆርቋሪነት ነው ወይስ በሌላ ምክንያት? የሚለው ግልጽ ሊሆንልኝ ባለመቻሉ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አጭረውብኛል፡፡

ከሁሉ የሚያስገረመው የኮሚሽኑ ሠራተኛ የሆነ ተሳታፊ ከኮሚሽኑ ሊወሰድ የታሰበው የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን በጥናት ላይ ያልተመሠረተና ተገቢነት የሌለው መሆኑን ከመግለጹም በተጨማሪ፣ ኮሚሽኑ ግን እነኚህን ሥልጣኖች እንዲሰጡት ሲደረግ በሚገባ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ይህ ጸሐፊ በሚገባ እንደሚያስታውሰው ስለኮሚሽኑ አመሠራረት ጥናት ያደረገው የውጭ አገር አማካሪ ባደረገው ጥናት ላይ ኮሚሽኑ ሁለቱም የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን በአንድ ላይ፣ አለበለዚያም ከሁለቱ አንዱ ሊሰጠው ይገባል ወይ? በሚለው ነጥብ ላይ አማራጮችን ከነምክንያታቸው ማቅረቡን ያስታውሳል፡፡ በዚህም መሠረት ኅዳር 2006 ዓ.ም. ይህ ጸሐፊ ከዚህ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ እንዳመለከተው በጥናቱ ላይ የሚከተለውን መግለጹን ያስታውሳል፡፡

የመጀመሪያውና ሁለቱ ሥልጣኖች በአንድ ላይ ለተቋሙ መሰጠት አለባቸው የሚለው በመላው ዓለም በፀረ ሙስና ትግል መንገድ ፈጽሞ የተለመደ አይደለም፡፡ ይኼ የተለመደ የሚሆንባቸው አገሮች በሥራ ላይ ያሉት የመርማሪና የዓቃቤ ሕግ ተቋማት ሥልታዊ የሆነ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል የሚል እምነት በመንግሥት ላይ ካደረ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም በተለምዷዊውና ተቀባይነት ባለው አሠራር ምርመራ የሚያካሂደው በፖሊስ ነው፡፡ ክስ የሚመሠርተው ደግሞ በዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ተቋማት ለፀረ ሙስናው ትግልና ዓላማው ፈጽሞ ጠቀሜታ የላቸውም ተብሎ ከታመነና ራሳቸው ሙሰኛ ተቋማት ናቸው ተብለው ከተፈረጁ፣ የፀረ ሙስናው ተቋም ሁለቱም ሥልጣኖች ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

ሁለተኛ ሥልጣኑ ቢለያይ የዚህ ዕምቅ ጠቀሜታው ተጠያቂዎችን ለፍርድ በማቅረቡ ላይ መዘግየት ይፈጠራል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ዓቃቤ ሕግ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ ወይም ወስዶ የሙስና ወንጀሎች ላይሠራ ይችላል የሚል መከራከራያ ይነሳል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት በዚህ ጊዜ ወይም መሀል ወሳኝ የሆኑ ማስረጃዎች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ በአራተኛ ደረጃ ኮሚሽኑ ጉልበት የሌለው እንዲሆን ያደርጋልና በዚህም ምክንያት የፀረ ሙስና ትግሉ የተጨናገፈ እንዲሆን ያደርጋል የሚል መከራከራያ ይቀርባል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን ተነጣጥሎ ለፀረ ሙስና ተቋሙ ሊሰጠው ይገባል በሚለው ነጥብ ላይ ሁለቱም ሥልጣኖች መለያየት ይገባቸዋል፡፡ ወይም መርማሪ ወይም ከሳሽ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ሁለቱን ሥልጣኖች ጠቅልሎ መያዝ የለበትም የሚሉ ምሁራን የሚያቀርቡት ክርክር ተቋሙ፣ አንደኛ ከልክ ያለፈ ጉልበትና ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ፣ በሕጉና በተዘረጋለት ሥርዓት ምንም ልጓም ሳይበጅለትና ሳይገደብ ተቋሙን እንዳሻው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ሁለተኛ ተቋሙ ሕጐችን በዘፈቀደና በጉልበት ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡ ሦስተኛው ነጥብ በተለይ ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው በማይሠሩባቸው ሥርዓቶች ወይም ሁኔታዎች ተቋሙ በባዶ ወይም ደግሞ ደካማ በሆነ ማስረጃ ጐጂ የሆነ ፍትሕና ፍርድ፣ ወይም ጐጂ የሆነ ውሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ አሳዛኝ የሆነ የፍትሕ መጨናገፍ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ በንፁኃን ሰዎች ላይ ተገቢነት የሌለው ፍርድ ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም ራሱ መርማሪ ነው፣ ራሱ ከሳሽ ነው፣ እንዳሻው የፍትሕ ሒደቱን ያሽከረክራል፡፡ ፍርድ ቤቱም ነፃም ገለልተኛም ስላልሆነ በመሀሉ ተጎጂው ዜጋው ይሆናል፡፡

አራተኛው ተቋሙ በአሠራሩ ነፃ ካልሆነ ወደ ፖለቲካ መሣሪያነት ሊወርድ ይችላል፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች በማይበረታቱበት ሁኔታ ተቀናቃኞችን ለማጥቃት መሣሪያ ይሆናል፡፡ አምስተኛውና የመጨረሻው ምክንያት ሁለቱም ሥልጣኖች እንዲለያዩ ማድረጉ፣ ተቋሙ ሚዛኑን የጠበቀ ትክክለኛ የሆነ ሥራ እንዲሠራ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ነው፡፡

ሁለቱም ሥልጣን ተሰጥቷቸው ተቋሙ ከልክ ያለፈ ጉልበት ካገኘ፣ የመንግሥት ሠራተኞች በሥጋት ፊታቸው የቀረበውን ጉዳይ ከመወሰንና ሥራቸውን ከመሥራት ይልቅ ራሳቸውን ወደ መጠበቅና በፍርኃት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ያደርጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሲቪል ሰርቪሱ ዳተኝነት የበዛበትና የተሽመደመደ ተቋም ይሆናል የሚል ነጥብም አለ፡፡ ሌላው ከባዱ ምክንያት ሁለቱም ሥልጣኖች የተሰጠው ተቋም በአግባቡ ለመሥራት ብቃት ያላቸው ሙያተኞች መቅጠር፣ ማሠልጠንና ማቆየት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ሥልጣኖች ያላግባብ ጥቅም ላይ ለመዋል የተጋለጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ብቃት ያላቸውን ኃላፊነት የሚወስዱ መርማሪና ዓቃቤ ሕግ ሊኖረው ይገባል፡፡ ዕወቀት፣ ብቃት፣ ታማኝነትና አስፈላጊው አቅም ያላቸው መርማሪዎችና ዓቃቢያነ ሕግ ማፍራት ወይም ማግኘት ደግሞ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ እነኚህን ሙያተኞች በአግባቡ እንዲሠሩ ማድረግ ደግሞ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡

አማካሪው በመጨረሻ ላይ ለመንግሥት የሰጠው ሐሳብ አንድ የሚቋቋመው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋም ሁለቱንም ሥልጣኖች ደርቦ እንዲይዝ አይመከርም ብለው ነበር የደመደመው፡፡ በተለይ ደግሞ የፀረ ሙስና የዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ሊሰጠው አይገባም፡፡ ማተኮር ያለበት በምርመራ፣ በመከላከልና በማስተማር ሥራ ላይ ነው የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ይህ ሐሳብ የተሰጠበት ምክንያትን ሲያብራራ በደርግ ጊዜ ከነበረው ሁኔታ በመነሳት ሁለቱንም ሥልጣኖች ጠቅልሎ መስጠት በጣም ከፍተኛ የተሰበሰበ ሥልጣን ያላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ከሚል ነው፡፡ ሌላው ለዘለቄታውም ቢሆን ኮሚሽኑ በመከላከልና በማስተማር ላይ ማተኮር ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የመክሰስ ሥልጣን መስጠት የማያስፈልግ ስለሆነ፣ ምናልባት በፍትሕ ሚኒስቴር ወይም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አንድ የዓቃቤ ሕግ አሃድ መፍጠር ይቻላል በማለት ሐሳቡን ቋጭቷል፡፡

በኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዘንድ የመመርመርና የመከሰስ ሥልጣኖችን በተመለከተ፣ በቀድሞው የጉምሩክ ባለሥልጣን ለበርካታ ዓመታት ፊናንስ ፖሊስ ይባል በነበረው የፖሊስ ሠራዊት አካል ቀጥሎም ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በጉምሩክ ፖሊስ አማካይነት ሲከናውን መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የባለሥልጣኑ የምርመራ አሠራሮች የተለዩ ባህሪያት ያላቸው መሆኑ የማይካድ ቢሆንም፣ የምርመራው ሥራ በመሠረቱ በአጭር ጊዜያት ሥልጠናና የአቅም ግንባታ ተግባራት በመደበኛው ፖሊስ ሊከናወን የሚችል ነው፡፡ የጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ከጉምሩክ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የዓቃቤ ሕግ ሥራዎችን እንዲሠራ በፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና እየተሰጠው፣ በሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት ክትትል እየተደረገበትና ለሚኒስቴሩ ስለሥራው አካሄድ ሪፖርቱን እያቀረበ ለአራት አሠርት ዓመታት ሲሠራ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ በ1985 ዓ.ም የማዕከላዊ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ሲቋቋም፣ ለጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ አገልግሎት ሠራተኞች ይሰጥ የነበረው ውክልና ቀሪ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የምርመራ መዛግብት እየቀረቡለት በሚፈለገው ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና ልዩ የጉምሩክ ሕግጋት ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ተግባራቱን ለማከናወን ባለመቻሉ ምክንያት፣ በባለሥልጣኑ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ በማስከተሉ እንደ ቀድሞው የፍትሕ ሚኒስቴር ውክልናውን እንዲሰጥ ተለምኖ በ1995 ዓ.ም. መጀመሪያ ለአራት የሕግ ባለሙያዎች፣ በመቀጠልም በርከት ላሉ የሕግ ሙያተኞች ውክልና ተሰጥቶ ሥራቸውን መሥራት ቀጠሉ፡፡ በተመሳሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገር ውስጥ ገቢ የሕግ ሙያተኞችም እንዲሁ ይህ ውክልና እንዲሰጥ ተደርጎ፣ ከባለሥልጣኑ ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የዓቃቤ ሕግ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ተደርጓል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የዓቃቤ ሕግ ሥራውን እየተከታተለና ሪፖርትም እየቀረበለት የዓቃቤ ሕግ ሥራው ሲሠራ ቆይቶ በ2001 ዓ.ም. ከየትኛው የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር ተሞክሮ እንደተወሰደ ሳይታወቅ፣ አስቀድሞ በአገራችን ከነበረው በውክልና ለባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የሕግ ባለሙያዎች እየተሰጠ ሲከናወን ከነበረው ሥራ ያፈነገጠ አዋጅ ወጣ፡፡ ምንም ዓይነት የዓቃቤ ሕግ ዕውቀትም ሆነ ሙያ ለሌለው የባለሥልጣኑ የበላይ ኃላፊ ተጠሪ የሆነ ራሱን የቻለ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣንና ኃላፊነት በሕግ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በዚህም ሕግ መሠረት የገቢዎችና ጉምሩክ ዓቃቤ ሕግ የተሰኘ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴርም ሆነ ከማንኛውም የዓቃቤ ሕግ ተቋም የተነጠለ የኮሚሽኑ ዓይነት ዓቃቤ ሕግ ተመሠረተ፡፡ ይህ የዓቃቤ ሕግ ተቋም እጅግ አስፈላጊ ሆኖ እንኳን ቢገኝ እንደ ቀድሞው ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውክልና እየተሰጠው እንዲሠራ ከማድረግ በስተቀር፣ የተናጠል ህልውና ይዞ እንዲቀጥል ማድረጉ አስፈላጊነት አልነበረውም፣ አይኖረውም፡፡ የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ለአገራችን አዲስ ተቋም ከመሆኑም በላይ፣ አስቀድሞ ልምዱ ስላልነበር የዓቃቤ ሕግ ሥራው ከየትኛው አገር ልምድና ተሞክሮ እንደተወሰደ ግልጽነት የሌለው በመሆኑ ከፍ ተብለው እንደተገለጹት ተቋማት ለመተቸት አልተቻለም፡፡ እንግዲህ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በፓርላማው የሕዝብ ውይይት ወቅት በተለይ የኮሚሽኑ ሠራተኞች የሰጡት ሐሳብ ከየት እንደመጣ በበኩሌ ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ይህ ጸሐፊ በኮሚሽኑ በዓቃቤ ሕግ በሠራባቸው የመጀመሪያ ጥቂት ወራት ሌላው ቢቀር በኮሚሽኑ መዋቅር ውስጥ ዓቃቤ ሕግን የሚመለከት የሥራ ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት፣ የኮሚሽኑ አዋጅ ከወጣ በኋላ መዋቅሩ እንዲዘረጋ ተደርጎ የዓቃቢያነ ሕግ ረቂቅ የሥራ መዘርዝሮችን ማዘጋጀቱን ያስታውሳል፡፡

በዚህም መሠረት አሁን ሊቋቋም እየታሰበ ባለው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የኮሚሸኑና የባለሥልጣኖቹ ዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቱ እንዲዛወር መደረጉ፣ የመርመራ ሥራውም ወደ ፖሊስ መመለሱ የኮሚሽኑንና የባለሥልጣናቱን ሠራተኞች ድንጋጤ ውስጥ ሊጨምራቸው የሚገባ አይሆንም፡፡ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ያለበቂ ጥናት ነው የሚለውንም ክርክራቸውን የሚደግፍ፣ ቢያንስ ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ በፊት በተደረገው ጥናትና በአማካሪዎቹ ሐሳብ ድጋፍ የለውም፡፡

ሊቋቋም የታቀደው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የራሱ የሆኑ የሕግ፣ የአወቃቀር፣ የሥልጣን ውክልና፣ የተጠሪነት፣ ወዘተ. ጉድለቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ ጭምር ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ተበታትነው የነበሩት የተሰባሰቡ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ወጥ፣ ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነቱና ገለልተኝነቱ የተጠበቀ ዓቃቢያነ ሕግም በተዋረድ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተጠሪ የሚሆኑበት ሥርዓት ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የዘረጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የኢሕአዴግ መንግሥት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን አፍርሶ አሁን ደግሞ እንደገና እንዲቋቋም በማድረጉ ከፍተኛ ጉዳት በአገርና በሙያው ላይ ያስከተለ ቢሆንም፣ አሁን ግን ይህንን ስህተቱን ለማስተካከል የወሰደው ዕርምጃ ዘገየ ከሚባል በስተቀር ወቅታዊነት ያለው መሆኑ ሊያከራክርም ሊያጨቃጭቅም ባልተገባ ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...