[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት በጣም ተቆጥተዋል]
- ምን ሆነሻል?
- ጋዜጣው ላይ የተጻፈውን አንብበኸዋል?
- ምንድን ነው የተጻፈው?
- ለመሆኑ ምን እየሠራችሁ ነው?
- ሥራችንን ነዋ የምንሠራው፡፡
- እኮ ሥራችሁ ምንድን ነው?
- አገር ማልማት ነዋ፡፡
- ማጥፋት ማለትህ ነው?
- ሴትዮ ምንድን ነው የምታወሪው?
- ዘመኑ የኢንፎርሜሽን መሆኑን ረሳችሁት እንዴ?
- ዘመኑማ የኢሕአዴግ ነው፡፡
- ለመሆኑ ሕግ የምታወጡት ምንን መሠረት አድርጋችሁ ነው?
- የሕዝብን ጥቅም ነዋ፡፡
- ኧረ አይመስለኝም፡፡
- ታዲያ ምንን መሠረት አድርገን ነው?
- ምቀኝነትን፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- በኢንተርኔት ስልክ መደወል ልትከለክሉ ነው አይደል?
- ታዲያ መንግሥት በሠራው መሠረተ ልማት ኒዮሊብራሊስቶች ኪሳቸው ሲደልብ ዝም ብለን እንይ?
- መወዳደር ነዋ፡፡
- ከኒዮሊብራሊስቶቹ ጋር?
- ታዲያ ሥራ እንድፈታ ነው የምትፈልገው?
- ለምን ትፈቻለሽ?
- ሥራዬን የምሠራው በስልክ እንደሆነ ታውቃለህ?
- ስልክሽ ተቋረጠ እንዴ?
- ስልክ እኮ የምደውለው አገር ውስጥ ሳይሆን ውጭ ነው?
- ታዲያ መደወል ነዋ፡፡
- ሰውዬ የአንተን ስልክ እኮ መንግሥት ስለሚከፍልልህ ምንም ላይመስልህ ይችላል፡፡
- የአንቺን ስልክ ራስሽ የምትከፍዪ ትመስያለሽ?
- ስማ ውጭ ካሉት ዕቃ አቅራቢዎች ጋር በየቀኑ በኢንተርኔት ነው እኮ የምደዋወለው?
- እና አሁን ማን ከለከለሽ?
- ይኸው ሊቆም አይደል እንዴ?
- ምኑ?
- What’s up?
- እሱማ መቆም አለበት፡፡
- ለምን?
- ባህላችን አይደለም፡፡
- ምንድን ነው ባህላችን?
- የእኛ ባህል እንዴት ዋልሽና እንዴት አደርሽ ነው? የምን What’s up ነው?
- ሰውዬ ስለቴክኖሎጂ ምንም አታውቅም እንዴ?
- ቴክኖሎጂንና What’s up ምን አገናኘው?
- በኢንተርኔት ስልክ መደወያ አፕሊኬሽን ነው እኮ?
- ነው እንዴ?
- አይ የአንተ ነገር?
- በViber ተጠቀሚያ፡፡
- እሱም ሊከለከል ነው፡፡
- ግን እኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጐበታል አይደል?
- ለመሆኑ ማን ነው ባለድርሻ አካል?
- እ…
- በዚህ ጉዳይ እኮ ባለድርሻ አካሉ ተጠቃሚው ሕዝብ ነው፡፡
- እና Viber ተጠቃሚ ሁላ እንዲወያይ ትፈልጊያለሽ?
- እንደዛ ካልሆነ መተው ነዋ፡፡
- ምኑ ነው የሚተወው?
- ክልከላው!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ክቡር ሚኒስትር በጀቱ ተፈቅዷል፡፡
- የምን በጀት?
- ያቀረብነው ፕሮፖዛል በዶነሮቹ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
- የትኛው ፕሮፖዛል ነው?
- የምርምር ተቋም ለመገንባት ያስገባነው ፕሮፖዛል፡፡
- ስንት ነበር የጠየቅነው?
- ሁለት ሚሊዮን ዶላር፡፡
- ይቺ እኮ አንድ ኮንቴይነር ዕቃም አትጭን፡፡
- የምን ኮንቴይነር ነው?
- ይቅርታ ከሌላ ነገር ጋር ተጋጭቶብኝ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዕቃ ያስመጣሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ?
- የምን ዕቃ?
- እንደሚባለውማ የማያስመጡት ዕቃ የለም አሉ፡፡
- ሰው መቼም የሚሠራ ሰው አይወድም፡፡
- ሰውማ የሚጠላው ሌላ ነገር ነው፡፡
- ምንድን ነው የሚጠላው?
- የሚሰርቅ ሰው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ውጭ ያለ ዘመዳቸው ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስማ አንድ ሥራ እልክልሃለሁ፡፡
- የምን ሥራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለአንድ ፕሮጀክት ዶነሮች ፈንድ ለቀዋል፡፡
- በጣም ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ፕሮጀክቱን ደግሞ የውጭ ኩባንያ ቢሠራው እነሱ ለመቀበል ይቀላቸዋል፡፡
- ለዚህ አይደል እንዴ እዚህ ይኼን ኩባንያ የከፈትነው፡፡
- ስማ ፕሮጀክቱ ለእኛ መሥሪያ ቤት የምርምር ተቋም ማቋቋም ነው፡፡
- በጀቱ ምን ያህል ነው?
- ሁለት ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር ያለመደብዎትን?
- ምነው?
- ሁለት ሚሊዮን ምን አላት ብዬ ነዋ?
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ከቪ8 እና ከቤት ዕቃ አታልፍም እኮ፡፡
- ያው ዶላሯ ትጠቅማለች ብዬ ነው፡፡
- ለነገሩ የተረፈው የልጆች ትምህርት ቤትና ለቤተሰቡ መዝናኛም ይሆናል፡፡
- እኔም እሱን ብዬ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሼር ያላቸው ኩባንያ ባለቤት ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለአንድ አዲስ ቢሮ ሙሉ የቢሮ ዕቃ ይዘጋጅ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዕቃ የለም፡፡
- ለምን ተብሎ?
- ኤልሲ የለም፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
- ታዲያ ምን ላስብ?
- ኮሚሽኔን!
[ፕሮጀክቱን ፈንድ ያደረገው ድርጅት ኃላፊ ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደወለ]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሄሎ ፈንደር፡፡
- ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራ ነዋ፡፡
- ፕሮጀክቱ ሳይጠናቀቅ ገንዘቡን አጠናቀቃችሁት እኮ?
- የአቅም ግንባታ ላይ ብዙ ስላወጣን እኮ ነው፡፡
- የማን አቅም ነው የተገነባው?
- የሠራተኞቹ ነዋ፡፡
- እኔ ግን የደረሰኝ ሪፖርት ሌላ ነው፡፡
- የምን ሪፖርት ነው የደረሰህ?
- የተገነባው አቅም የሠራተኞቹ አይደለም፡፡
- የማን አቅም ነው የተገነባው ታዲያ?
- የእርስዎ!
[አንድ ደላላ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለ]
- ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድን ነው የምታወራው?
- ጡረታ መውጣት ፈለጉ እንዴ?
- ኧረ የጡረታ ዕድሜ 80 መሆን አለበት እያልኩ ያለሁት እኔ አይደለሁ እንዴ?
- እስከ ሰማንያ ዓመትዎ ሥልጣን ላይ ሊቆዩ?
- ሰማንያ ስደርስም ማስጨመሬ አይቀርም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ሕግ ከወጣ እኮ ሥራ ልናቆም ነው፡፡
- የምን ሕግ?
- ቴሌ የሞባይል ስልኮች ካልተመዘገቡ እያለ ነው፡፡
- ይመዝገቡዋ ታዲያ ምን ችግር አለው?
- ታክስ ያልተከፈለበት ስልክ አገሪቷ ውስጥ መሥራት አይችልማ፡፡
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር ከሥራ መፈናቀላችን ነው፡፡
- ለመሆኑ ስንት ኮንቴይነር ስልክ ነው መጋዘን ያለው?
- አራት ኮንቴይነር፡፡
- እና አራት ኮንቴይነር ያልተሸጠ ስልክ አለ እያልከኝ ነው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የድለላ ሥራውን አቆምክ ልበል?
- ክቡር ሚኒስትር እንቅስቃሴው እኮ ተቀዛቅዟል፡፡
- አሁን ቴሌ የሚመዘገብ ነገር ጠፍቶ ነው ስልክ የሚመዘግበው?
- የሚመዘገብ ነገር ምን አለ ብለው ነው?
- ለምሳሌ የባለሥልጣን ሀብት፡፡
- እሱማ ሲመዘገብ አብዛኞቻችሁ የምትገኙት አንድ ቦታ ነው፡፡
- የት ነው የምንገኘው?
- እስር ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቴሌ ስልክ ሲደውሉ በአንድ ጥሪ ገባላቸው]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ ጋ ለመደወል 25 ጊዜ ነው የሞከርኩት፡፡
- ምን አሉኝ?
- ኔትወርኩን ለምን አትሠሩትም?
- ኧረ ይሠራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የኔትወርኩን ሥራ ትታችሁ ሌላ ነገር ለምን ትፈተፍታላችሁ?
- ምን ፈተፈትን ክቡር ሚኒስትር?
- ሞባይል ስልክ ልትመዘግቡ ነው አሉ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ባትመዘግቧቸው ምን አለበት?
- ታክስ ያልከፈሉትን ለመለየት ነዋ፡፡
- ለመሆኑ ታክስ ያልተከፈለባቸው ስልኮች ምን ይደረጋሉ?
- እዚህ አገር መሥራት አይችሉማ፡፡
- ታዲያ የት ልንሸጣቸው ነው?
- ምኖቹን ክቡር ሚኒስትር?
- ማለቴ ታክስ ባይከፍሉ ምን ችግር አለው?
- ክቡር ሚኒስትር ታክስ ከፍለው ስልክ የሚያስገቡት እየተጐዱ ነው፡፡
- ነፃ ገበያ አይደል እንዴ?
- እሱማ ነፃ ገበያ ነው፡፡
- ይወዳደሩዋ ታዲያ?
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ወደ ቁም ነገሩ እንምጣና አራት ኮንቴይነር ስልክ ያለው ሰው ምንድን ነው የሚደረገው?
- እሱማ እጁን ቢሰጥ ይሻለዋል፡፡
- እጅህ ይቆረጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ደላላው ጋ ደወሉ]
- ምን አገኙ ክቡር ሚኒስትር?
- አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡
- ሕጉ እንዳይወጣ ማድረግ አይችሉም?
- እሱ የሚቻል አይመስለኝም፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- ሞባይሎቹን መልሰን ኤክስፖርት ማድረግ አለብን፡፡
- እንዴት አድርገን?
- ሌላ አገር መሸጥ አለባቸው፡፡
- ኤክስፖርት ለማድረግ እኮ እዚህ አገር እሴት መጨመር አለበት፡፡
- ከዚህ በላይ እሴት እንዴት ይጨመርበት?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ኢትዮጵያ እኮ የተቀደሰች አገር ናት፡፡
- ስለዚህ?
- ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በመውጣቱ ብቻ እሴት ተጨምሮበታል ማለት እንችላለን፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ኢትዮጵያ እኮ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠራች አገር ናት፡፡
- ለነገሩ ከዚህ በላይ እሴት መጨመር ምን አለ?
- እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
- ስለዚህ ምን ይደረግ?
- ፈቃድ ይውጣ፡፡
- የምን?
- የሪኤክስፖርት!