በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተገነቡ ባሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አገር በቀል ኩባንያዎች ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የግል ዘርፉን ለማገዝ ፈንድ አዘጋጀ፡፡
ለቦሌ ለሚ ሁለትና ለቂሊንጦ ኢንዲስትሪ ፓርኮች ግንባታ የዓለም ባንክ 250 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ አድርጓል፡፡
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 197 ሚሊዮን ዶላር ለፓርኮቹ ለግንባታ የዋለ ሲሆን፣ 12.7 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ አገር በቀል ኩባንያዎችን በፋይናንስ ለመደገፍ ይውላል ተብሏል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥር የተቋቋመው የተወዳዳሪነትና ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ተሰማ ገዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚገኙ ትልልቅ ፋብሪካዎች ግብዓት ማቅረብ የሚችሉ አገር በቀል ኩባንያዎች የፋይናንስ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡
‹‹የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ ኩባንያዎቹን ያስተሳስራል፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ተሰማ፣ ‹‹አገር በቀል ኩባንያዎች ምርት ማቅረብ እንዳይችሉ የሚያዳግታቸውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ፈንድ ተዘጋጅቷል፤›› ብለዋል፡፡
የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በሥሩ የፈንድ አስተዳደር ያቋቋመ ሲሆን፣ የተቀመጠውን መሥፈርት የሚያሟሉ አገር በቀል ኩባንያዎች እስከ 400 ሺሕ ዶላር ድረስ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡
አቶ ተሰማ፣ ‹‹በአሁኑ ወቀት ለአገር በቀል ድርጅቶች የተዘጋጀው ፈንድ አነስተኛ ቢሆንም፣ የኩባንያዎቹን ሁኔታ ከታየ በኋላ ሌሎች የገንዘብ አማራጮች ሊታዩ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በብዛት የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳታፊ ለማድረግ ከዚህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ብዙ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡
የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሳለኝ ሆቴል ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ እንደተገለጸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማምረት፣ በማቀነባበርና በግብይት ሒደት ላይ የሚገኙ ግዙፍ ፋብሪካዎችና በአገር ውስጥ መካከለኛና አነስተኛ የግል ድርጅቶች መካከል የንግድ ትስስር እንዲፈጠር፣ የአቅምና የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዓላማው አድርጓል፡፡