የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሐዋሳ ከተማ በሳምንት አራት ቀናት በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ኤክስፕረስ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት የሚሰጠው ከአየር መንገዱ ሰባት የትርፍ ማዕከላት አንዱ የሆነው ዩኒት የበረራ አገልግሎቱን ከሚያዝያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኪው 400 ቦምባርዲየር አውሮፕላን ሰኞ፣ ረቡዕ፣ ዓርብና እሑድ እንደሚሰጥ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሐዋሳ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 20ኛው የአገር ውስጥ በረራ መዳረሻ መሆኗ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የሐዋሳ በረራ የሚጀመረው በራዕይ 2025 (የአየር መንገዱ የ15 ዓመታት የዕድገት መርሐ ግብር) በተቀመጠው የተጠናከረ የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ መስጠት ከሚል ግብ በመነሳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ አየር መንገዱ ለአገሪቱ ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት አገራዊ ግዴታ እንዳለበት አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ክልል የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችና ጎብኚዎች ወደ ሐዋሳ በሚጀመረው በረራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ለተማሪዎች፣ ለመንግሥት ድርጅቶችና ለመሳሰሉት የበረራው መጀመር ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በሐዋሳ በ457 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚያስገነባው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ግንባታ 85 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ድርጅቱ ገልጿል፡፡ የመንገደኞች ተርሚናል ግንባታ ለመጀመር ጨረታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚያወጣም አስታውቋል፡፡ የኤርፖርቱ ግንባታ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በተጠቃሚዎች በኩል ባለው ከፍተኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ምክንያት ኤርፖርቱ በከፊል አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑ ተነግሯል፡፡
የደቡብ ክልል መናገሻ የሆነችው የሐዋሳ ከተማ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ከተመረጡ ዞኖች አንዷ ስትሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ በከተማዋ ተገንብቷል፡፡