Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹ሃይላንድ›› እግሩ ውስጥ የገባው ሳላ

‹‹ሃይላንድ›› እግሩ ውስጥ የገባው ሳላ

ቀን:

ይህ በፎቶው ላይ የሚታየው ሳላ፣ ከሦስት ወራት በፊት ድርቁ በፓርኮችና በዱር እንስሳቱ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመዘገብ ሪፖርተር በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በተገኘንበት ወቅት የተነሳ ነው፡፡ ሳላው በድርቁ ከመጎዳቱ ባለፈ መግቢያው በር አካባቢ ባግባቡ መሄድ ያቃተው በአካባቢው በተጣለውና በተቆረጠው ሃይላንድ ውስጥ እግሩ በመግባቱ ነበር፡፡

ፎቶ በታምራት ጌታቸው

******

. . . በሬው! . . .

እዩት ያንን በሬ በቀንዱ ተማምኖ
ያሸብረን ይዟል ላሞች ላይ ጀግኖ
ላሞች እንደሆኑ መጠቃት ልምዳቸው
ወተት እንዲያጠጡ ኮርማ ነው ግዳቸው።

በሬ እየሸለለ፣ በሬ እየፎከረ 
በሬው እያጓራ፣ ስንቱ ደጅ አደረ፤
ይወጋል ይረግጣል፣ ሲሻው ያንሳፍፋል
በሬ ሆይ አይምሬው፣ ትውልድ ያጣድፋል።

ተው በሬ … ተው ኮርማ 
እባክህ ተመከር፣ ያገር ምክር ስማ 
ተጥለህ እንዳናይህ፣ ከቄራው አውድማ።

የሚሮጥ፣ የሚሸሽ፣ የሚበረግገው፣ 
ቀንድህን በመፍራት፣ የሚያደገድገው፣
ገና ብቅ ስትል መንገድ የሚጠርገው ᎐᎐᎐ 

ይሄ ሁሉ ፈሪ፣ ይህ ሁሉ ቦቅቧቃ
ከዘመን ፍራቻው፣ ሲባንን ሲነቃ
ሆ! ያለብህ እንደሁ ታጥቆ በቆንጨራ
ያዝ ያለህ እንደሆን ከቦ በገጀራ 
ማምለጫም አይኖርህ ለአንገትህ ካራ። 

“በሬ ሆይይ 
በሬ ሆይይ 
ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ 
መግባትህ ነው ወይይይይ”

ብለን እንዳናለቅስ ቆዳህን ሲገፉ
ዛሬን አታስጀግር ተው ሰዎች ይለፉ
በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር ይረፉ 
ላንተም አይበጅህም፣ ያጠፋሃል ግፉ።

(አብዲ ሰዒድ፣ 2005 ዓ.ም.)

******

ከአስከሬን ላይ ቀለበት የሰረቀችው ሴት እየተፈለገች ነው

በቴክሳስ በአንድ የመቃብር ሥፍራ ክፍት ከሆነ የአስከሬን ሳጥን ውስጥ ከ88 ዓመት ሟች ላይ ቀለበት አውልቃ ስትወስድ በደኅንነት ካሜራ የተቀረፀችው ሴት እየተፈለገች መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ፡፡

ፖሊስ እንዳስታወቀው፣ ከሟቿ አዛውንት ሬሳ ሳጥን ፊት ለፊት ለደቂቃ የቆመችው ሴት ወዲያው የሟችን ጣት በመጠምዘዝ ቀለበት ስታወልቅ ቪዲዮው ያሳያል፡፡

ሰራቂዋ ወዲያው ቀለበቱን ይዛ በመኪና መሰወሯም በዘገባው ተመልክቷል፡፡ በደኅንነት ካሜራ የተቀረፀውን ቪዲዮ እንድትመለከት የተደረገችው የሟች ልጅ ሰራቂዋን እንደማታውቃት ገልጻለች፡፡

*********

በደቡብ ኮሪያ አዛውንቶች በምርጫ ድምፃቸውን እንዲሰጡ መደለያ ቫያግራ ተሰጣቸው

ስንፈተ ወሲብ ያለባቸው ደቡብ ኮሪያውያን አዛውንቶችን ድምፅ ለማግኘት አዛውንቶቹ ቫያግራ እንዲሰጣቸው በመደረጉ፣ ጉዳዩ እንዲጣራ በፍርድ ቤት መወሰኑን የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ደቡብ ኮሪያውያን ከጥቂት ቀናት በፊት ምርጫ ማካሄዳቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ምርጫው የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ማስፈራሪያና የኢኮኖሚ ፈተና ጥላት ያጠላበት ነበር፡፡

የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት በመስጠት ድምፅ የመግዛት ወንጀል ተፈጸመበት የተባለው ሱዎን፣ ከአገሪቱ መዲና ሴዑል 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የሱዎን ዓቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ ‹‹ወንጀሉ መፈጸሙን አላረጋገጥንም፡፡ እውነት ሆኖ ከተገኘ ግን የምርጫ ሕግን የሚፃረር ነው፤›› ማለታቸውን የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት ባልተገባ መልኩ የሕዝብ ድምፅ መግዛት በአምስት ዓመት እስራትና 8,750 የአሜሪካ ዶላር ያስቀጣል፡፡

በአገሪቱ የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ የሚሸጥ በመሆኑ፣ እነዚህን መድኃኒቶች በመጠቀም የአዛውንቶችን ድምፅ ለመግዛት የሞከሩት የምርጫ ተወዳዳሪ መድኃኒቶቹን እንዴት በብዛት አገኟቸው? የሚለውም አጠያያቂ ሆኗል፡፡

በሕጉ መሠረት በተለያየ መንገድ የዜጎችን ድምፅ ለመግዛት የሞከረ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን በተጠቀሰው መንገድ ድምፁን የሸጠ ዜጋም ከቅጣት አያመልጥም፡፡

*******

የትራምፕ ልጆች ለአባታቸው ድምፅ አይሰጡም

በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ለመሆን የሪፐብሊካኑን ፓርቲ ለመወከል እየተንቀሳቀሱ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕና ወንድ ልጃቸው ኤሪክ ትራምፕ ለአባታቸው ድምፅ መስጠት እንደማይችሉ ተረጋገጠ፡፡

ልጆቻቸው ድምፃቸውን ሊሰጧቸው ያልቻሉት የመራጮች ምዝገባ ስላመለጣቸው እንደሆነ ትራምፕ ልጆቻቸውም ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ አባትና ልጆቹ የምዝገባ ሥርዓቱንም ኮንነዋል፡፡ ‹‹ፖለቲከኛ ቤተሰብ አይደለንም፡፡ በፖለቲካ ውስጥም ለረዥም ጊዜ አልቆየንም፤›› ያለችው ኢቫንካ የምዝገባ ሕጉ ከዓመት በፊት እንዲመዘገቡ የሚጠይቅ መሆኑን፤ ስለዚህም ያንን ምዝገባ የሚያድሱበት ዳግም ምዝገባ እንዳመለጣቸው ገልጻለች፡፡

ወንድሟ ኤሪክም ‹‹ይህ በፖለቲካ የመጀመርያ ጊዜያችን ነው፡፡ አጠቃላይ ሥርዓቱ እንዴት እንደሚሠራ አናውቅም ነበር፤›› ብሏል፡፡

******

ሱናሚና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች

‹‹ሱናሚ›› የጃፓን ቃል ሲሆን፣ ትርጓሜውም ከቁጥጥር በላይ የሆነ የውኃ ሞገድ ወይም መሬት ተዛንፎ አለበለዚያም ተንቀጥቅጦ በአንድ ጊዜ ሲተረተር የሚለቀው ሞገድ ነው፡፡ ይህም ሞገድ ሲነሳ ወይም መሬት ሲደረመስ ውኃውም አብሮ ይዘልና ወደታች ይወርዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጣሪያ በላይ የሚደርስ ቁመት የመዝለል ኃይል አለው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ላይ የዘለለው ውኃ ወደታች ወይም ወደ መሬት ሲወርድ ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ይወስዳል፡፡

ዶ/ር አታላይ አየለ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ኃላፊና የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ባለሙያ እንደገለጹት፣ የምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ከኬንያ ከሞምባሳ እስከ ደቡብ አፍሪካ ያሉት አገሮች ለሱናሚ አደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡

ቀይ ባሕርና ጂቡቲ ሱናሚ እምብዛም አያሠጋቸውም፡፡ ነገር ግን ጂቡቲ ባሕር ዳርቻ ያለች አገር በመሆኗ መጠነኛ የሆነ የሱናሚ ሞገድ ሊፈጠርባት ይችላል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለሱናሚ ሊጋለጡ የቻሉት ከህንድ ውቅያኖስ ወደ ኢንዶኔዢያ አካባቢ ከባሕር ጠለል ሥር የሚነሳው የመሬት መንቀጥቀው በሬክተር ስኬል ሰባትና ስምንት ማግኒቲዩድ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ሱናሚ የመነሳቱ አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው ማለት ነው፡፡

ቀይ ባሕርና ጂቡቲ ሱናሚ የሚያሠጋቸው ከተፈጥሮአዊ አቀማመጣቸው የተነሳ ሸለቆ ውስጥ በመገኘታቸው ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በኬንያዋ ሞምባሳና ሶማሊያ ጠረፍ ሱናሚ ተከስቶ ለበርካታ የሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...