Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጥራት የናፈቀው የትምህርት ሥርዓት

ጥራት የናፈቀው የትምህርት ሥርዓት

ቀን:

የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራም የጥራት ማረጋገጫ ከሌለው ልማትን ከማፋጠንና ቴክኖሎጂን በማሳለጥ ፈንታ ችግር ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ጥራትን የማስጠበቅ ዓላማ ያነገበ አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ዝግጅቱም እየተከናወነ ያለው ላለፉት 24 ዓመታት ሥራ ላይ የዋለውን የትምህርት እንቅስቃሴ በመገምገምና የቀጣዩን ዓመታት አቅጣጫዎችን በመቀየስ ነው፡፡

ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀውና በአፍሪካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ዙሪያ ለሁለት ቀናት የተወያየውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) ሲከፍቱ እንደገለጹት፣ አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ ለዝግጅቱ ግብዓትና ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ልዩ ልዩ  ጉዳዮችም ተለይተዋል፡፡

የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ፣ ለውይይትም ቀርቦ በምሁራን እንደሚተችና የማዳበሪያ ሐሳቦችም እንደሚካተቱበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከእንዲህ ዓይነቱ  ዓለም አቀፍ ጉባዔ የተገኙት ገንቢ ሐሳቦችና ተሞክሮዎች ለፍኖተ ካርታው ጥንካሬ እንደ ግብዓት እንደሚያገለግሉ አስረድተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሥርዓተ ትምህርት ቅኝ ገዥዎች ከነበሩት ምዕራባውያን በተወረሰ ንድፈ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህም ማለት ፍራንኮፎን ተናጋሪ አገሮች የፈረንሣይን፣ አንግሎፎን ተናጋሪዎች ደግሞ የእንግሊዝን ንድፈ ሐሳብ ይጠቀማሉ፡፡ ምናልባትም ለየት ያለና የተቀላቀለ በአብዛኛው ወደ አሜሪካ ያደላ የትምህርት ሥርዓት የወረሰችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡

ከዚህ አኳያ አፍሪካውያን የተስማሙበት፣ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የታመነበትና በ2052 ዓ.ም. የሚሳካ አጀንዳ እንደሚቀረፅ፣ የአጀንዳውም መፍትሔ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ያጠነጠነ የትምህርት ሥርዓትን ማስፈንና መተግበር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይህ ዓይነቱም ሥርዓተ ትምህርት አፍሪካን ከጥገኝነት ከማላቀቅ ባሻገር  ያልተጠቀመችበትን ሀብት አውጥታ ድህነትንና ኋላቀርነትን፣ በሽታን፣ ሥራ አጥነትን፣ ስደትንና ግጭቶችን አስቀርቶ በምትኩ ዕድገትና ብልፅግን፣ ሥራ ፈጣሪና ተመራማሪ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት እንዲኖራት ያደርጋል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ማስረጃ ላይ የሚያምንና ትምህርት ማስረጃ ማግኘትን ብቻ እንደ ግብ የሚወሰድ ማኅበረሰብ መፍጠር የለባቸውም፡፡ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ብቃታቸው የሚመዘንበት የማረጋገጫ ሥርዓት አገሮች እየዘረጉና እያረጋገጡ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በጉባዔው በአገር ውስጥና በውጭ ምሁራን የተዘጋጁ ከ30 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን ያስታወሱት የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት፣ ‹‹ጽሑፎቹ በሚገባ ከተደራጁና አንደምታቸው ከተለዩ በኋላ ዩኒቨርሲቲው በሚያካሂደው ስትራቴጂ ፕላን ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ድርጅቶችና በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ ለሚንቀሳቀሱ ተቋማት ሁሉ እንዲዳረሱ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ጉባዔውን ብቻውን ያካሄደ እንደነበር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በትምህርት ሥራ ላይ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት እያሳደረ በመምጣቱ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበር፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድና ዩኔስኮ በአጋርነት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ይህም ፍላጎት አብረን መበልፀግ አለብን ወደ ሚል እሳቤ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አባባል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወቱ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ያሉት በኪራይ ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ ከኪራይ ውድነት አልፎ የመማር ማስተማሩ ሥራ በጠባብ ክፍሎች ውስጥ ማካሄድ አማራጭ የሌላው ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡

ከኢንቨስትመንት አኳያ በሌሎች የልማት መስኮች ለሚሰማሩት የግሉ ዘርፍ መንግሥት እየሰጠ ካለው ማበረታቻ አንፃር በትምህርት ዘርፍ ለሚሰማራው የግሉ ዘርፍ የሚሰጠው ማበረታቻ አጥጋቢ ነው ለማለት እንደማያስደፍር፣ ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ ምንም እንኳን ተግባራዊ ባይሆንም ማበረታቻ እንዲሰጥ የሚጠቁሙ አንቀጾች እንደነበሩበት፣ በ2009 ዓ.ም. የወጣው ሁለተኛው አዋጅ ግን አንቀጾቹን እስከማስወጣት መድረሱን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ምንም እንኳን በአዋጅ የተፈቀደ ማበረታቻ ባይኖርም በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲከታተሉ መፈቀዱን ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ገልጸው፣ ይህም ለዘርፉ ትልቅ እገዛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ወደ 300 የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲ መሪዎች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ የሚሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶችና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...