የአብሥራ ፍቃዱ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በድንገት እናትና አባቷ ሲሞቱ ከታላቅ እህቷ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ብዙም ሳይቆይ የታላቅ እህቷ ባለቤት ወሲባዊ ትንኮሳ ያደርስባት ጀመረ፡፡ በወቅቱ የ11 ዓመት ታዳጊና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ የእህቷ ባል ከትንኮሳ አልፎ ሊደፍራት ሲሞክር ቤቱን ጥላ ወጣች፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ ጎዳና ላይ መኖር ጀመረች፡፡ አሁን የ16 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ በተለምዶ 100 ደረጃ በሚባለው አካባቢ ትኖራለች፡፡
የጎዳና ኑሮ ስትጀምር 100 ደረጃ አካባቢ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶችን ጓደኛ አደረገች፡፡ ቀስ በቀስ አዋዋሉና አስተዳደሩን ተላመደችው፡፡ እንዴት ገንዘብ ማግኘት እንደምትችልና እንዴት ራሷን ከጥቃት መከላከል እንዳለባት ነገሯት፡፡ የጎዳና ሕይወት ግን ከገመተችው በላይ ፈታኝ ሆነባት፡፡ አላፊ አግዳሚውን ስትለምን፣ የሚሰድቧትና የሚያንቋሽሿት በዙ፡፡ ሥራ ማግኘትም ከባድ ሆነ፡፡ ‹‹አንዳንድ መንገደኞች ይመቱናል፣ ይተፉብናል፣ ይሰድቡናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አዝነው ብር ይሰጡናል፤›› ትላለች፡፡ ከሁሉም በበለጠ ፈተና የሆነባት የሚደርስባት ጥቃት መሆኑን ትናገራለች፡፡ መንገደኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ጭምር የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች ላይ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚያደርሱ ትገልጻለች፡፡
በአንድ ወቅት የደረሰባትን በሐዘኔታ ታስታውሳለች፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ ጧ ያለ እንቅልፍ ወስዷታል፡፡ ድንገት አጠገቧ ተኝታ የነበረች ጓደኛዋ በፍርሃት እየጮኸች ቀሰቀሰቻት፡፡ ደንግጣ ተነሳች፡፡ አጠገቧ ወንዶች ቆመዋል፡፡ ምን እንደተፈጠረ ባይገባትም ጓደኛዋን ተከትላ እግሬ አውጪኝ አሉ፡፡ ጓደኛዋ ወንዶቹ ሊደፍሯት እንደነበረ ነገረቻት፡፡ ከዛን ቀን በኋላ ስትተኛ በሥጋት ነው፡፡ እስካሁን ባትደፈርም ብዙ ጓደኞቿ ተደፍረዋል፡፡ ያለ ፍላጎታቸው አርግዘው ወልደዋል፡፡ የአብሥራ መራራ ሕይወቷን ለመርሳት ማስቲሽ ማጨስ ጀመረች፡፡ ረሃብና ብርድን ለመቋቋም በሚል ሲጋራም ታጨሳለች፡፡
እሷና ጓደኞቿ ምሽት ላይ ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመዳን ፒያሳ አካባቢ የሚገኝ የጋራ ማደሪያ ቤትን አማራጭ አደረጉ፡፡ በቤቱ ለማደር 40 ብር መክፈል አለባቸው፡፡ ‹‹እየለመንንና የተገኘውን እየሠራን እየሸቀልንም 40 ብር ካገኘን እሪ በከንቱ ኬሻ በጠረባ ሔደን እናድራለን፤›› ትላለች፡፡ በየቀኑ 40 ብር ባያገኙም፣ ያገኙ ዕለት እፎይ ብለው ይተኛሉ፡፡ ሆኖም የአንዳንድ ቀን የሰላም መኝታም ይሁን አደንዛዥ ዕፅ ከጎዳና ኑሮ አስከፊ ስቃይ አላዳናትም፡፡
ከሁለት ወር በፊት የአብሥራና ጓደኞቿን መሠረት ይርጋ የምትባል ኬሮግራፈር (የዳንስ አቀናባሪ) ታገኛቸዋለች፡፡ ኮንቴምፕረሪ ዳንስ አሠልጥናቸው ሕይወታቸውን በመጠኑም ቢሆን የሚቀይሩበት መንገድ ልትከፍትላቸው እንደምትችል ነገረቻቸው፡፡ የአብሥራ በወቅቱ ትፈልግ የነበረው ምግብና መጠለያ ቢሆንም፣ የዳንስ ሥልጠናው ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል በማመን ተስማማች፡፡ በሳምንት ሦስት ቀን ዳንስ መማር ጀመረች፡፡
ኬሮግራፈሯ ‹‹ኖ ውሜን ቢሀይንድ›› (አንዲትም ሴት ወደኋላ እንዳትቀር) የሚል ፕሮጀክት ዘርግታ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አካል ጉዳተኞችና በሕፃናት ማሳደጊያ የሚኖሩ ሴቶችን ኮንቴምፕረሪ ዳንስ ታሠለጥናለች፡፡ ከሰዎች ገንዘብ በማሰባሰብ በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ የኪስ ገንዘብ እንዲያገኙ ለማድረግ ትሞክራለች፡፡ የአብሥራና ጓደኞቿ በደባልነት የሚኖሩበት ቤት ብትከራይላቸውም ዘላቂነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ነው የሚባል የሚያኖራቸው ገቢ የለምና፡፡
የአብሥራ እንደምትለው፣ ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ባይለወጥም ሥልጠናው ጭላንጭል እየታያቸው ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ከሱስ መላቀቅ መቻሏ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ሲጋራና ማስቲሽ አቁሞ በዳንስ መተካት ቀላል አይደለም፤ ጥንካሬ ካለ ግን የማይቻል ነገር ስለሌለ ለአሁን ሱሶቹን ትቻቸዋለሁ፤›› ትላለች፡፡ ቢሆንም ቀድሞውኑ ወደ ሱስ የገፋፋት የጎዳና ሕይወት ውስጥ ተመልሳ ከገባች ዳግም ወደ ሱስ የመመለሷ ዕድል በጣም የሰፋ ነው፡፡ ለአሁን ግን በዳንስ ራሷን በነፃነት መግለፅና ደስተኛ መሆን እንደቻለች ትናገራለች፡፡ የጎዳና ሕይወትን አስከፊነት በዳንስ መግለጽ እንደምትፈልግም ትገልጻለች፡፡
‹‹ኖ ውሜን ቢሀይንድ›› በሚል ለሁለት ወራት የሠለጠኑት ሴቶች፣ ባለፈው ሳምንት በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የዳንስ ትርዒት አቅርበው ነበር፡፡ የጎዳና ተዳዳሪና አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በዳንስ ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን፣ የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች በሱስ ሲጠመዱ፣ ፖሊሶች ሲያንገላቷቸውና ማኅበረሰቡ ሲያገላቸው በሥራቸው አንፀባርቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ አካል ጉዳተኞችን በመናቅ ከሌላው ሰው እኩል ዕድል እንደማይሰጣቸው የሚያንፀባርቅ ዳንስም አቅርበዋል፡፡
ሴቶቹ ዳንሱን ያሳዩት አንድም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ገንዘብ ለማሰባሰብ አስበውም ነው፡፡ ቋሚ የገቢ ምንጭ ካላገኙ ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለሳቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከሠልጣኞቹ መካከል በዳንስ መቀጠል የሚፈልጉት ዕድሉን የሚሰጣቸው ተቋም ቢኖር ሕይወታቸው እንደሚለወጥ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ሕይወቴ እንዲለወጥ እፈልጋለሁ፡፡ ተስፋ ያየሁበትን ዳንስ ብገፋበት ደስ ይለኛል፡፡ ትምህርቴንም መቀጠል እፈልጋለሁ፤ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ቀድሞው ሕይወት እንዳልመለስ እፈራለሁ፤›› ትላለች የአብሥራ፡፡
የሴቶቹ ሕይወት በወራት የዳንስ ሥልጠና ይለወጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ቋሚ ሥራ ካላገኙና ገቢ ከሌላቸው ወደተውት የጎዳና ሕይወት ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ ከሌለ ከሱስ ተላቆ መኖርም ከባድ ይሆናል፡፡ ለውጥ ለማምጣት የተደረገው ጥረት የአንዲት ሴት ጅማሬ ቢሆንም፣ የሌሎች አካል ትብብር ካልታከለበት ብዙ ርቀት አይሄድም፡፡
ሌላዋ ሠልጣኝ የ20 ዓመቷ ወይንሸት ታፈሰውም የአብሥራን ሐሳብ ትጋራለች፡፡ ‹‹መድረኩን አግኝተን ሥራችንን ማሳየታችን ጥሩ ቢሆንም በቀጣይ ተመሳሳይ ዕድል የሚሰጠን ከሌለ ትርጉም የለውም፤›› ትላለች፡፡ ወይንሸት በከፊል ዓይነ ስውር ስትሆን፣ በቱጌዘር የዓይነ ስውራን የተራድኦ ድርጅት ውስጥ ትኖራለች፡፡ ከተወለደችበት ባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ከአባቷ ጋር ነበር፡፡ አባቷ እንዳትማር ሲከለክሏት ተጣልታ ወደ ጎዳና ወጣች፡፡
ጎዳና ላይ ተደፍራ ልጅ ወለደች፡፡ ‹‹የጎዳና ሕይወት ልጅ ላላት አካል ጉዳተኛ ሴት ከሌላው የበለጠ ፈታኝ ነው፤›› ትላለች፡፡ ወደ ድርጅቱ የገባችው ከአንድ ዓመት በፊት በአንዲት ሴት ዕርዳታ ሲሆን፣ ቢያንስ ለልጇ የተሻለ ሕይወት መፍጠር በመቻሏ ደስተኛ ነበረች፡፡ ልጇን ከማሳደግ ባለፈ ግን ራሷን መለወጥ የምትችልበት መንገድ እንደሌላት ስለምታስብ ታዝናለች፡፡ ‹‹የመለወጥ ተስፋ የለኝም ብዬ ስለማስብ እማረር ነበር፡፡ ተስፋ በቆረጥኩበት ሰዓት ዳንስ ተስፋዬን አለምልሞታል፤›› ትላለች፡፡ ተስፋዋ ምን ያህል ያዘልቃታል የሚለው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከሥልጠናው በኋላ ተመልሳ ወደ ዓይነ ስውራኑ ድርጅት ታመራለች፡፡ ዳንስ እውነት በሕይወቷ ሁለተኛ ዕድል እንደሚሰጣት ማወቅ አይቻልም፡፡ ሥልጠናው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ አንዳች ጥቅም ላይ መዋልም አለበት፡፡
በዳንስ ስለራሷ ያላት አመለካከት እንደተለወጠ ታምናለች፡፡ የአካል ጉዳቷ ለማንኛውም ሥራ እንቅፋት እንደሚሆንባት ትገምት ነበር፡፡ ዳንስ በራስ መተማመን እንደሰጣትና በሙያው መግፋት እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ የምትደንስበት ቦታ ወይም በዳንስ የሚያሠራ ተቋም አለማግኘት ያሠጋታል፡፡ ኬሮግራፈር መሠረት የሰጠቻቸው ሥልጠና ባላት የገንዘብ ውስንነት ሳቢያ ሊቀጥል እንደማይችል ታውቅለች ወይንሸት፡፡
መሠረት ሴቶቹ ለዘለቄታው እንዲለወጡ መንግሥትና ሌሎችም እገዛ እንዲያደርጉ ትጠይቃለች፡፡ ‹‹አቅም ያላቸው ሰዎች እንዲያግዙ እንፈልጋለን፡፡ ቦታና ገንዘብ ቢኖረን የብዙ ጎዳና ተዳዳሪና አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ሕይወት መለወጥ ይቻላል፤›› ትላለች፡፡ ሴቶቹን ከሱስና የሕይወት ውጣ ውረድ ካሳረፈባቸው አሻራ ማላቀቅ ፈታኝ ቢሆንም፣ ዳንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ትናገራለች፡፡ ‹‹ወደ ሥልጠና የሚመጡት ምግብ ሳይበሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሱስ ማስወጣት ደግሞ በጣም ከባድ ነው፤›› የምትለው ኬሮግራፈሯ፣ ዳንስ በሒደት ከሱስ እንደሚያላቅቅ ታስረዳለች፡፡ በዳንስ ደስተኛ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ሊኖራቸው ስለሚችለው የተሻለ ሕይወት ግንዛቤ በመፍጠርና ተነሳሽነታቸውን በመጨመር መፈወስ ይቻላል ትላለች፡፡ ፈውሱ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ግን ቀድሞውኑም ለጐዳና ያበቋቸው መሠረታዊ ችግሮች ከተቀረፉ ብቻ ነው፡፡
የዳንስ ሕክምናን ጨምሮ ልዩ ልዩ ጥበቦችን ያማከሉ ሕክምናዎች (አርት ቴራፒ) በሌሎች አገሮች የተመደ ነው፡፡ አርት ቴራፒ የሥነ ልቦና ወይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በፈጠራ ሥራዎች ራሳቸውን እንዲገልጹና ከሕመማቸው እንዲፈወሱም ይረዳል፡፡ በእኛ አገርም በዳንስ፣ በሙዚቃና በሥነ ጥበብ ሕክምና ለመስጠት የሚሞክሩ ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በቅርቡ ለአማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሕክምና ሆስፒታል ሕሙማን የሥነ ጥበብ ሕክምና የሰጡ ሰዓሊዎች ነበሩ፡፡ መሰል ሕክምናዎች ለውጥ አምጥተዋል ማለት የሚቻለው ግን ቀጣይነታቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡
መሠረት ‹‹ዕድሉና አቅሙ ለሌላቸው ሴቶች ተስፋ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሴቶቹ ከከፋ ሕይወት እንዲወጡ ዕድል የሰጣቸው የለም፡፡ ምንም አይጠቅሙም ተብለው የተተው ናቸው፡፡ በዳንስ ግን መውጫ መንገድ አላቸው፤›› ትላለች፡፡ ሴቶቹ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዳይመለሱ ካልተደረገ ግን ለውጥ እንደማይመጣ ትናገራለች፡፡ የሷን የግል ጥረት የሚደግፉ ከሌሉ የተገነባው ፈርሶ ሴቶቹ ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለሳቸው አያጠራጥርም፡፡
ተመሳሳይ አስተያየት የሰጠችን ዳንሰኛ የውብነሽ ቁምላቸው 28 ዓመቷ ሲሆን፣ አካል ጉዳተኛ ናት፡፡ በዳንስ የሰዎችን ሕይወት ከመለወጥ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ግንዛቤ መቀየር እንደሚቻል ታምናለች፡፡ በትርዒታቸው አካል ጉዳተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በማሳየት ኅብረተሰቡ በምን መንገድ ሊረዳቸው እንደሚችል እንዳስተማሩ ትናገራለች፡፡
ጦር ኃይሎች አካባቢ ተወልዳ ያደገችው የውብነሽ ከልጅነቷ ጀምሮ የዳንስ ፍቅር ነበራት፡፡ አካል ጉዳተኞች መደነስ አይችሉም የሚለውን አመለካከት ለማሸነፍም ብዙ ውጣ ውረድ አልፋለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጃክሰን የአካል ጉዳተኞች የዳንስ ቡድን አባሎች ጋር መገናኘቷ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላት ትናገራለች፡፡ ኮንቴምፖረሪ ዳንስ ከተማረች በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረች መደነስ ጀመረች፡፡ በክራንች ተደግፋ ስትደንስ ለማመን የሚቸገሩ ተመልካቾች ገጥመዋታል፡፡ እያንዳንዱ መድረክ የሰዎችን አመለካከት እንደሚቀይር ታምናለች፡፡ መሠረት ከሠልጣኞቹ ጋር እንድትቀላቀል ስትጠይቃትም ያለማንገራገር ነበር የተቀበለችው፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ብትሳተፍም አሁንም በምታገኛቸው አጋጣሚዎች ትሳተፋለች፡፡
ብዙ አካል ጉዳተኞች እሷ ያገኘችውን ዕድል በቀላሉ እንደማያገኙ ትናገራለች፡፡ እንደሷ ያሉ አካል ጉዳተኞች ሌሎች አካል ጉዳተኞች በዳንስም ይሁን በሌላ ሙያ የመሰማራት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ማበረታታት አለባቸው ትላለች፡፡ ‹‹የሰው አመለካከት የሚቀየረው ሠርተን ስናሳይ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች ተነሳሽነቱና በራስ መተማመኑ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ማኅበረሰቡም እኩል ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፤›› ትላለች፡፡ ከሥልጠናው በኋላ እሷ፣ የአብሥራ፣ ወይንሸትንና ሌሎችም ሴቶች በጀመሩት የለውጥ ጎዳና እንዲገፉ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ትገልጻለች፡፡
ዳንስ በሕይወታቸው ሁለተኛ ዕድል እንዲሰጣቸው ከሥልጠና ባለፈ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ዕርምጃ መውሰድ የሚችሉ አካሎች መረባረብ አለባቸው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በግለሰቦች ተነሳሽነት የሚሰጡ መሰል ሥልጠናዎች ፍሬ የሚያፈሩትም ከግለሰቦች በዘለለ የብዙዎች እገዛ ሲታከልባቸው ነው፡፡