የመንግሥት ተቋማት ሙስናን መከላከል የሚያስችላቸው ስትራቴጂ ቀርፀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ መንግሥት ያዘዘ ሲሆን፣ ይህንንም ማድረግ ያስችል ዘንድ የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 6 እና 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ከመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ለተውጣጡ ከ250 ለሚሆኑ የሥነ ምግባር መኮንኖች ሥልጠና መስጠቱ ታወቀ፡፡ የኮሚሽኑ ሙስናን የመከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት ለስትራቴጂው አዘገጃጀት ተግባራዊነትም ያግዛል በተባለው ሥልጠና ላይ ተሳታፊዎች (የሥነ ምግባር መኮንኖች) ሲመረጡ ኮሚሽኑ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዘርፎች ከግንዛቤ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከከተማ አስተዳደር መሬት ጋር በተያያዘ የሚሠሩ፣ በግንባታው ዘርፍ፣ ፍትህ አስተዳደርና ከፍተኛ ግዥ በሚፈፀምባቸው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ካሉ ሠልጣኞቹ ተመርጠዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ተመሳሳይ ሥልጠናዎች ከዚህ ቀደምም ይሰጡ ነበር፡፡ ነገር ግን የሥልጠናውን ውጤት በመከታተል ረገድ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን የመንግሥት ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሙስናን መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ስለተላለፈ ከኮሚሽኑ የሚመደቡ ባለሙያዎች በየተቋማቱ የሚኖረውን ስትራቴጂ የማዘጋጀትና የመተግበር እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ይሆናል፡፡ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በመንግሥት ተቋማት፣ በልማትና ሕዝባዊ ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበው የሙስና መከላከል ስትራቴጂ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ስትራቴጂውን በሚገባ ለመንደፍ ደግሞ የተቋማት የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች ሚና ወሳኝ በመሆኑ ለባለሙያዎቹ ሥልጠናው እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ የስትራቴጂው ተፈጻሚነትም በየተቋማቱ በየበጀት ዓመቱ የበጀት ዓመቱ የዕቅድ አካል ሆኖ በበላይ አመራር እንዲገመገም እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ ከታህሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሔደው ሦስተኛው አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይልማርያም ደሳለኝ የመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ነድፈው ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስታውቀው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት መነሻ ይሆን ዘንድ ስትራቴጂካዊ ሠነድ አዘጋጅቷል፡፡ የካቲት ላይ የመንግሥት ተቋማት የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ውይይት በተደረገበት መድረክ የመንግሥት ተቋማት የሙስና መከላከል አዲስ ስትራቴጂ ቀርፀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ፤ ይህን ሳያደርጉ ለሚደርስ ጥፋት ተቋማቱን የሚመሩ ኃላፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡