Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዘንድሮ ኑሮ ከቅዠት በምን ይለያል?

ሰላም! ሰላም! ባሻዬ አንድ የቅርብ ዘመዳቸው ጠቅሎ አገሩ እንደሚመጣ ነግረውኝ ደህና ይዞታ ያለው የሚሸጥ ቤት እንድፈልግ አዘውኛል። ‘አግኝቻለሁ’ ብዬ ስሄድ የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄና መልስ ያዳምጣሉ። ያለወትሮው ሬዲዮናቸው መጮሁን አስተውዬ፣ ‹‹ስንት ለስንት ናቸው?›› አልኩ። ኳስ መስሎኝ። ‹‹መሀል ሜዳና ጎል አጥርቶ መለየት የሚችል ዓይን ይዤ ኳስ በሬዲዮ ልከታተል? እንኳን በድምፅ በዓይናችን በብረቱ እያየንም ግቡንና አገባቡን እያምታታን ነው፤›› ብለው ተቀኙ። አይ ባሻዬ! ወዲያው ስለቤቱ ጉዳይ ስናገር ቀልባቸው ወደ እኔ ይሳባል ብዬ ‹‹ቤቱ …›› እንዳልኩ ‹‹ቆይ!›› ብለው ተቆጡ። ጠያቂው፣ ‹‹በከበሮና በፀናፅል የሚዜም መንፈሳዊ ዜማ ምን ይባላል?›› ብሎ ጠይቆ መላሽ አጥቷል። አንድ አንድማጭ በስልክ ተጋፍቶ ተንደርድሮ አየር ላይ ገባ። ምነው? የታክሲ ግፊያ ብቻ መሰላችሁ እንዴ ጉልበታችንን ያሟጠጠው? እንዳታስጠልፉኝ ተውኝ አሁን ስለኔትወርክ አላወራም።

‹‹የቅድሙን ጥያቄ! የቅድሙን ጥያቄ!›› አድማጩ ይጎተጉታል። ‹‹በከበሮና በፀናፅል የሚዜመው መንፈሳዊ ዜማ የሚለውን ለመመለስ ነው?›› ሊገላግለኝ ነው ብሎ አድማጩን አሸናፊነትን እንደምታበስር የመለያ ምት መቺ ቆጥሮታል ጠያቂው። ‹‹አዎ! አዎ!›› አድማጩ አንድ የሚያውቃት ዕውቀት ይህቺ ብቻ ትመስል እንደ ልጅ ጓጓ። ‹‹በል መልስ እሺ ምን ይባላል?›› ሲለው ‹‹በገና!›› ብሎት አረፈው። ‹‹ምን?›› ጠያቂው ተወዛገበ። ‹‹በገና!›› ደገመው። ጥያቄውን ቢደግምለት ፍንጭ ቢሰጠው በተዘዋዋሪ መልሱ ከመልስ ምድብ እንደማይመደብ ቢያስረዳው፣ ‹‹የለም በገና ነው!›› ብሎ ደረቀ። ይኼኔ ነው ባሻዬ ሬዲዮናቸውን ያጠፉዋት። አጠፋፋቸው እስከ ምፅዓት ድረስ እንዳይከፈት ዓይነት ነው። በዝግታ ከመቀመጫቸው ተነስተው፣ ‹‹በኋላ እንነጋገራለን፤›› ብለው ብቻ በጠራራ ፀሐይ ተጠቅልለው ተኙ። አሁን ጥያቄ ብዬ ‘ፍራሽና ብርድ ልብስ ተደርጎበት ለመተኛነት የሚገለግለን ጎን ማሳረፊያ ምን ይባላል?’ ብል . . . ‹‹አንሶላ!›› የሚል አድማጭ አይጠፋም ማለት እኮ ነው። አይዟችሁ ደግሞ ይኼን ያህል አሳንሶ ይገምተናል ብላችሁ ጨዋታዬን እንዳታቋርጡ። የውኃ፣ የመብራትና የኢንተርኔት መቆራረጡ አይበቃም እንዴ?

ዛሬ ታዲያ የሆድ የሆዳችንን የምንጫወተው በእግር ኳስ ቋንቋ ቢሆንስ? ወግ ስለያዝን ታዲያ የመሀል ሜዳ ዳኛ ፊሽካና የመስመር ዳኛ ባንዲራ አንጠብቅም። ስለዚህ ስንጀምር በ‘ሎጬ’ ይሆናል። ‘ሎጬ’ አንድ ከማለቴ በፊት እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ወገኔን እንደ ራሴ፣ እኔን እንደ ሌላው ስታዘብ የማገኘው በኑሯችን ሜዳ አንዳችን ሌላችንን ስንኮምክ አይደለም። ኩመካ አዲስ የሆነበት የፌስቡክ ‘ጄነሬሽን’ አባል ‘አብዶ’ በሚለው ይያዝልኝ። ኦ ለካ አብዶም አማርኛ ነው። እሺ በቃ ‘ትሪክ’፡፡ እናም ኩመካው ራስ በራስ ላይ ነው። ምናልባት ለጠላት አልበገርም ተብሎ ራስን በራስ ማጥፋት ፍፁም ጀግንነት ነው ብለን ፋይል ስለዘጋንም ይሆናል። ይኼ የመጀመሪያው ‘ሎጬ’ ነው። ሁለት ሦስት አራቱን በደምሳሳው ልንገራችሁ።

ለምሳሌ ሌላኛው ‘አብዶ’ ከ80 እስከ 85 በመቶ በግብርና የሚተዳደር ወገን ይዘን፣ በቀን ሦስቴ መብላትን በፖለቲከኞቻችን ጫንቃ ላይ ብቻ ጥለን፣ መንገድ ላይ መብላት አፍረን፣ መንገድ ላይ መፀዳዳት ደንብ ነው ብለን፣ ጡት እልዳጠባ ሕፃን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ‹‹ነውር ነው እሺ!››፣ ‹‹አይደረግም እሺ!›› ስንባል ኃፍረት ባጠገባችን ሳያልፍ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚያስተላልፋቸው የአውሮፓ ኳስ ግጥሚያዎች የምንፈልጋቸውን አይደለም በሚል ብቻ ደማችን ከፍ ይላል። ልባችን ይደክማል። እንደ ልብ አግኝተን ያልቃምነውና ያላባከነው ስኳር በሽታ ሆኖ ከች ይላል። እንግዲህ የትኛውን ‘ሎጬ’ እርስዎን ራስዎ ላይ እንዳገቡት አስበው ይድረሱበት። አይሻልም ዳኛው? ኦ ለካ ዳኛ የለም ተባብለናል!

ሌላ ምሳሌ ምግብና እኛን በተመለከተ ልቀጥል። የምግብ ዓይነቶች የሚል ሬስቶራንቶቻችን የሜኑ አልበም ከማቀናጀታቸው በፊት፣ በመሐሙድና በጥላሁን ድምፅ ከቅልጥም እስከ ቆሽት አዘፍነናል። በልቼ ጠገብኩ ባይ ባይኖርም ገንፎ፣ አጃ፣ ቡላ፣ ጨጨብሳ፣ ቂንጬ፣ ዶሮ ወጥ፣ እንቁላል፣ ወተትና ማር በዜማ ሲወደሱ ዕልል ብለናል። ዛሬ ይሄውላችሁ . . . ዛሬ ‘ጊዜ የለም’ በሚል ሆሊውድ አመጣሽ ብሒል ልጆቻችንን (አዋቂዎቹን ተውን አንዴ ስላወቅን) በተጠቀለሉና በታሸጉ የፋብሪካ ምርቶች ወስፋታቸውን እየዘጋን ትምህርት ቤት መላክ ያዝን። ዝም ብላችሁ ብቻ በገዛ እጃችን ጤናችን ላይ የምንሠራውን ‘አብዶ’ ቁጠሩ። እንዲያው ባሰብኩት ቁጥርማ ሌላ ሌላው ሳይሆን የሚያመኝ ቢያንስ ተፈጥሮ የለገሰንን ጤናማ አመጋገብ አጥብቀን ለመያዝ ‘ታይም ኢዝ ጎልድ’ ማለት መጀመራችን ብቻ ነው። ‹‹ዋት?’ ሙት በለኝ እስኪ፤›› አሉ ባሻዬ እያረሩ ሲስቁ!

በዚህ ጉዳይ ብቻዬን አንጀቴ አሮ አይቀርም ብዬ ለባሻዬ ልጅ አብዶዎቹንና ሎጬዎቹን ሳስቆጥረው፣ ‹‹ምን ያበሳጭኸል ታዳያ ብቻህን?›› አለኝ። ‹‹እኮ እኛና ጊዜ ታርቀን? እኮ እንደ አንድ ዜጋ የምንሞላት ትንሽ ክፍተት የአገር ምሰሶን ትደግፋለች ብለን አምነን ሥራ ባህላችን ሆኖ?›› አልኩት። ‹‹መልሱ ከእኔ ሲሆን ደስ ስለሚልህ እንጂ ለምን በየቢሮው እየዞርክ አታይም?›› አለ። ጥሩ! ሳሻሽጥና ሳከራይ፣ ኮሚሽኔን ይዞ የተሰወረውን ሳሳድድ የነገረኝን ሳልረሳ ቀኝ ግራ አስተዋልኩ። ጠዋት በሶ በጥብጠን (ምንም ቢሆን የስንዴ ተዋፅኦ መሰለኝ ባንዲራችንን በዓለም የአትሌቲክስ መንደሮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረገው) ለመጠጣት ጊዜ የለኘም ማለት የጀመርን ሰዎች፣ መሥሪያ ቤት ገብተን ከኮምፒዩተር ጋር ካርታ ስንቆምር (የዘንድሮ ኮምፒዩተር ምኑ ይታመናል ያቋምር ይሆናል ብዬ እኮ ነው)፣ በቄስ እከሌና በቄስ እከሌ መሀል የተደረገን ሃይማኖታዊ ሙግት ስንደግፍ ስንቃወም በአንጃ ተከፋፍለን በየፌስቡኩ ስንሰዳደብ ስንውል አየሁ። የተገኘችዋን አጣጥሞ በልቶ ጤናማ ዜጋ ለመሆን ግን ‘ኖ ታይም!’ . . . ብሏላ ዴንዝል ዋሽንግተን። በሻይ ሰዓትና በግምገማ ውዝፍ ሥራ እያከማቸን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ሦስት ብር ብቻ ስለምናዋጣ ምንም ችግር አይታይብንም። (ይኼን ያልነው እኛው ነን) ኧረ ይኼን የ‘ሎጬ’ ጉዳይ ላቁመው ተው?! ወይስ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ባለ በሌለ ኃይሉ የሚፍጨረጨረውን መንግሥታችንን እያማን እኛ ከማከራየት፣ ቡቲክ ከመክፈት፣ በካፌና ሬስቶራንት ከተማ ከማጣበብ፣ መሸታ ቤት ከመቀለስ ያልዘለለ የጎመን በጤና ቢዝነስ ወዳድነታችንን ልጨምረው? አሁን ኳሷ ፎሪ ሳትወጣ፣ ወይ እኔ በቀይ ሳልወጣ ሌላ ነገር እናውራ!

የእጅ ውርወራ ለባሻዬ ዳያስፖራ ተሰጥቷል። ባሻዬ ያ ቤት እንድፈልግለት የነገሩኝ ዘመዳቸው ከትናንት ወዲያ ምሽት አገሩ ይገባ ኖሮ ከልጃቸው ጋር እንድንቀበለው አዘዙ። ባሻዬ ካዘዙ ምን ይደረጋል? የባሻዬ ልጅ ደግሞ ኤርፖርቱንና የማስፋፊያ ሥራውን በጨለማ እያየ፣ ‹‹እንዲህ በየጊዜው እያፈረሱ እያጠሩ አስፋፍተው ይችሉታል?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹ማለት?›› አልኩት የሚተነብየው ነገር እንዳለው ገብቶኝ። ‹‹መላ አዲስ አበባ የኤርፖርቱ አካል ካልሆነች አያዋጣም፤›› ብሎ አረፈው። ‹‹ኧረ ዝም በል ሰው እንዳይሰማህ። በመንግሥት ማስተር ፕላን የተተራመስን ሰዎች በግለሰብ ፕላን ምን ልንሆን እንደምንችል አታስብም?›› አልኩት ደንግጬ። ‹‹አባባሌ መላው የአገሬ ሕዝብ ዕድሉን ካገኘ አገሩን ጥሎ ከመሄድ ስለማይመለስ፣ ልብ የገዛ ጊዜ አንድ ቀን ግርር ብሎ ቢመጣ ይህቺን የምታህል ግንባር መሬት ቀርቶ አገሩ ጠቅላላ አየር ማረፊያ ካልሆነ ያስቸግራል ብዬ ነው፤›› አይለኝም? ዕድሜው ይጠርና ይኼ የተዛባ የአየር ንብረት፣ ቦሌ እንደ ድሮው ቢበርድ ኖሮ ሰውነቴን ለማሞቅ አውሮፕላን ከሚበርበት የጫማ ከፍታ በላይ እንከተከት ነበር። ልብ ካላችሁ ታዲያ ይኼም ፈገግታ አንዱ ‘ሎጬ’ ነው።

ይኼን እያወራን አንድ ቀይ ጃኬት የለበሰ ባለ ብዙ ሻንጣ ዙሪያችንን ሲዞረን እናየዋለን። እንግዳችንን ቆሞ መጠበቅ እየመረረን መጣ። ‘አውሮፕላንም የታክሲ ሠልፍ ዕጣ ገጠመው እንዴ?’ እያልኩ ሳሾፍ ያ ባለ ቀይ ጃኬት በማይክሮስኮፕ ባክቴሪያ እንደሚያበጥር ላብራቶሪስት ዓይኑን አጨንቁሮ የባሻዬን ልጅ እያየ ስሙን ጠራው። ተሳስመን ዕቃውን ጭነን ወደ ሠፈራችን ስንጓዝ ዳያስፖራው፣ ‹‹አገሩ ሰላም አይደለም እንዴ?›› ብሎ እያፈራረቀ አየን። ‹‹ኧረ ሰላም ነው ምነው?›› ብንለው፣ ‹‹ምንድነው ታዲያ እንዲህ የጨለመው? ለምዳችሁት ይሆናል እንጂ መንገዱ ‘ሴፍ’ አይመስልም፤›› ብሎ ስለመንገድ መብራት እጥረት አወራ። ውሎ ሲያድርማ ስለሻማ እጥረት ምን ይለን ይሆን ብለን ዝም። ምስኪን!

በሉ እንሰነባበት። እንደ ልቤ ተሯሩጨ ሥራ እንዳልሠራ ያ የባሻዬ ዳያስፖራ አገኘሁ ብሎ እዚህ እንጀራ ላይ አልቀመጥ አልነሳ አለ። እሱን ይዘን ከባሻዬ ልጅ ጋር ሆስፒታል ለሆስፒታል ሆነ። ጎበዝ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት አለ ተብለን የተጠቆምንበት ሆስፒታል ያጋጠመኝ ግን ለጉድ ነው። በመጀመሪያ እንዲያ ደጋግፈነው በሽተኛውን ይዘን ስንገባ ከመጤፍ የሚቆጥረን ሰው ጠፋ። ካርድ ክፍል የተመደቡ ሁለት ሴቶች በየግላቸው የሚሠሩበትን ፀጉር ቤት እያነሱ ‘የእኔ ይበልጣል ያንቺ ያንሳል’ ይጠዛጠዛሉ። ቀረብ ብዬ አንደኛዋን፣ ‹‹ካርድ እዚህ ነው?›› ስላት ‹‹እናንተ ጋ አንዷን ፀጉሯን ቆርጠው ጠንቋይ ቤት አስደግመውባት ያበደች ልጅ አውቃለሁ፤›› ትላለች ህልውናዬን ክዳው። ‹‹ኧረ ባክሽ ሰው ታሞብናል አንዴ ካርድ አውጭልኝ፤›› ስላት፣ ‹‹ነገም ያንቺ ዕጣ ይኼው ነው፤›› ብላ በስላቅ ባልደረባዋን ገላመጠች። ትዕግሥቴ አልቆ ስጮህ፣ ‹‹ስም ማን ልበል?›› ማለት ጀመረች። ለአካል ሕክምና ይህቺን ያህል ጮኸን ከተደመጥን ለመንፈስና ለነፍስ ጥያቄማ ፓርላማ ገብተን ስንጮህ አስቡት የሚመጣውን ለውጥ። ማለቴ ካስገቡን . . .ማለቴ ከገባን . . . ማለቴ ከተመረጥን ማለቴ ነው። ወይ ማለትና እኔ ዘንድሮ!

ደግሞ ካርድ ክፍሏን አልፈን ነርሶቹ መጡ። ነርሶቹ ደግሞ ሌላ የቡና ወሬ። ይኼኔ ዳያስፖራችን ክፉኛ አዝኖ፣ ‹‹ቀባሪ አታሳጣኝ አገሬ ግደለኝ’ የሚለው ሰው ለምንድነው?›› ብሎ ሲጠይቀኝ ከሰማኋት ቆየች ያለች ቀልድ ትዝ ብላኝ ዘና እንዲል ነገርኩት። የአገራችንን የቀብር ሥነ ሥርዓት ያስተዋለ ህንዳዊ ነው አሉ። ሰው ከሞተ ወዲያ ያለውን ፀጉር መንጨት ደረት መድቃት አይቶ ይጠይቃል። ‹‹እኛ በአገራችን ሰው ሲሞትብን ነፍሱ ወደ ሌላ አካል ተዛውራ ትቀጥላለች ብለን ስለምናምን ሞትን እንደ ቁም ነገር አናየውም። ሬሳውንም እናቃጥላለን። እዚህ ግን ከአረሳችሁት መሬት የተቀበራችሁበት ይበልጣል። ለምን እያቃጠላችሁ መሬቱንስ አትቆጥቡም?›› ሲል አሉ ከእኛ መሀል አንዱ፣ ‹‹አይ እኛ ሰው አናቃጥልም። ካቃጠልንም በቁሙ ማቃጠል እንጂ አስከሬን ክቡር ነው፤›› ያለውን ነገርኩት። ሕመሙን እስኪረሳ ሳቀ። አቤት ግን በቁም አቃጥሎ የጨረሰን ነገር ብዛቱ። ደግሞ አሁንም እዚያና እዚህ ስንጠቁም ሌላ ‘ሎጬ’ እንዳናስመዘግብ አደራ፡፡ ‘በበኩሌ ከአሁን ወዲያ አላቃጥልም’ ብለን ለራሳችን ቃል እንግባ። ‹‹ለውጥ ከራስ ይጀምራል›› አላለም እንዴ አክሊሉ ለማ . . . ማን ነው አልበርት አንስታይን? ይቅርታ አክሊሉ ፈረንጅ ስለመሰለኝ ነው . . . ሆሆሆሆ . . .  ‘ቅዠት ውስጥ ተሁኖ ስንቱ ይዘባረቃል ቢባል፣ የዘንድሮ ኑሮ ከቅዠት በምን ይለያል?’ ያለው ማን ነበር? መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት