Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹አመለካከታችንና የስፖርታችን ‘ሶፍት ዌር’ በጣም ኋላ ቀር ነው›› ኃይሌ ገብረሥላሴ

‹‹አመለካከታችንና የስፖርታችን ‘ሶፍት ዌር’ በጣም ኋላ ቀር ነው›› ኃይሌ ገብረሥላሴ

ቀን:

ከማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላ ጀምሮ እስከ አረንጓዴዎቹ ጎርፎች ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ አውድማ ስሟን ተክላ ቆይታለች፡፡ የዚህ ዘመን አለኝታዎችም ደራርቱ ቱሉ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስህን፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና ሌሎችም እያሉ የአገሪቱ የስፖርት ጀግኖች ስም በዓለም አደባባይ እየደመቀ እየጎላ የአገሪቱ የወርቅ ባለዕድልነት የሚቆም የሚገታ አይመስልም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን የአይበገሬዎቹ የወርቅ አሸናፊነት በተለይ በወንዶቹ እየቀነሰ፣ እየደከመ የአገሪቱ ደማቅ ሰንደቅ ዓላማም የዓለም አደባባይን የሚናፍቅበት ጊዜ መታየት መጀመሩ ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡ ሥጋቱን የሚጋሩ የስፖርቱ ቤተሰቦችም ከየአቅጣጫው ድል ጠፋ፣ ጀግና አትሌት አዳዲስ የዓለም ክብረወሰኖችን እየበጣጠሰ ዓለምን አስደምሞ የአገሩን ሰዎች በደስታ ሲቃ የሚያስነባ፣ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ነገር ሳይጠቀም ተፈጥሮ በሰጠው ፀጋና ሥራ ብቻ ተጠቅሞ የሚወጣ ጉልበታም አትሌት ይናፍቅ ጀመረ፡፡ የእነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉና የእነ ቀነኒሳ በቀለንና ሌሎችንም ዱካ የሚከተለው ቁጥሩ ደበዘዘ፡፡ ይባሱን በዓለም አደባባይ ጭራ እየሆኑ ውድድሮችን ማጠናቀቅ አልበቃ ብሎ፣ የአገሪቱንና የቀድሞዎቹን ገናና ታራክ በሚያጎድፍ ተግባር ላይ በመሰማራት አቋራጭ ፈላጊ አትሌቶች መብዛታቸው የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ሕዝቡን ከማስከፋቱም በላይ ቀደምት ስፖርተኞችንም አሳፈረ፡፡ ዝምታውን ዝም ማለት ያልወደዱት ቀደምት አትሌቶችም አቋም መያዛቸውን አስታወቁ፡፡ ቀደምቱ የአገሪቱን የስፖርት መዋቅሮች የሚመሩ ኃላፊዎች የስፖርቱ ሙያ ከሌላቸው በቀር እስከ መጨረሻው ዝም እንዳይሉ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መልስ እየጠበቁ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡ የቀድሞዎቹ አትሌቶች ጥያቄም ውጤት እያጣ ከመጣው የአትሌቲክስ ዘርፍ በተጨማሪ ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ዜናም አስቆጥቷቸዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ሁሉ መንስኤው ስፖርቱን በዕውቀትና በክሕሎት የማይመሩ አካላት ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸውን፣ ከእንግዲህ እንዲህ እንዳይደረግ ሲሉ አቋም መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል የቀደምት አትሌቶችን ጥያቄ አስመልክቶ ይፋ የሆነ መግለጫ ባይሰጥም፣ አንዳንድ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ጥያቄው እንደ ጥያቄ የምንቀበለው ቢሆንም የሪዮ ኦሊምፒክና ዝግጀቱ ከቀረው ጊዜ አኳያ ትኩረታቸውን ወደ እዚያ አድርገው ከኦሊምፒክ በኋላ ግን ቀደምት አትሌቶቹም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚያነሷቸው አጠቃላይ ችግሮችና ክፍተቶች ዙሪያ ለመወያየት እቅድ እንዳለ ነው ያስረዱት፡፡ በሌላ በኩል ቀደምት አትሌቶች በተለይም በአሁኑ ወቅት አትሌቲክሱ በመንታ መንገድ ላይ መገኘቱን በመግለጽ ለብሔራዊ አትሌቶች ማኅበር አቤቱታቸውን እንዳቀረቡ፣ የማኅበሩ አመራሮችም መድረክ ፈጥረው እንዲያወያዩዋቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ከሚጠቀሱት ቀደምት አትሌቶች ውስጥ የኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ እንዲሁም በሌሎችም ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አገሩንና ራሱን በትልቁ የታሪክ መዝገብ ላይ ያስቀመጠው ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዱ ነው፡፡ ደረጀ ጠገናው በወቅታዊው የአትሌቶች ጥያቄና የሙያ ብቃት ዙሪያ አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡– አትሌቲክስ ለአንተና ለቀደምት አትሌቶች ምንድነው?

ኃይሌ፡- የማንነታችን መገለጫ፣ ሁሉ ነገራችን ነው፡፡ ለእኔ ደግሞ ከዚህም በላይ ነው፡፡ ብዙ ነገር ያየሁበት የወጣሁበት የወረድኩበት ማንነቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱ ታሟል እያላችሁ ይመስላል?

ኃይሌ፡- እውነት ነው ታሟል፡፡ አሁን ግን ታሟል በሚል ብቻ ዝም የምንልበት ጊዜ ያበቃ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ከንፈር በመምጠጥ ብቻ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ለምን ታመመ፣ መድኃኒቱስ ምንድነው? በቀጣይስ? በሚለው ዙሪያ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የአትሌቲክሱ ውጤት ማሽቆልቆል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የተተኪ አትሌቶች ጉዳይ አለ፣ ያልዘመነ አሠራር አለ፣ በዚህ ጉዳይ እንደ ሙያተኛ ብቻ ሳይሆን በውስጡ እንዳለ ሰው የተለመደ፣ በግሌ የማላምንበት አነጋገር አለ፡፡ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማነፃፀሪያ ሁሌም ኬንያ ነች፡፡ ኢትዮጵያውያን 100 ሚሊዮን ኬንያውያን 45 ሚሊዮን በምን እንገናኛለን፡፡ ሌላው ደግሞ ማራቶን በወንድ በሴት፣ በ10,000 በወንድ በሴት እንዲሁም በሌሎች ርቀቶች በተመሳሳይ እያለ ይወርዳል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ሌላው የስህተታችን መሸፈኛ ደግሞ በኦሊምፒክ አልያም በዓለም ዋንጫ ሁለት ወይም ሦስት የወርቅ ሜዳሊያ የምናገኝበት አጋጣሚ ነው፡፡ በዚህ መንገድ መጥቶ ውድቀቱን ከምናየው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- አንተም ሆንክ ሌሎች ቀደምት አትሌቶች እስከዛሬ የት ነበራችሁ?

ኃይሌ፡- ጥያቄያችን እንዲህ እንዳሁኑ ጎልቶ አልወጣም እንጂ በአትሌቲክሱ እየተፈጠረ ስላለው ችግር መነጋገር የጀመርነው ከስድስት ወር በፊት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ በአበረታች ንጥረ ነገር ዙሪያ ከዋዳም ሆነ ከአይኤኤኤፍ ሰዎች መረጃዎች ይደርሱን ስለነበር ነው፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋር ጥረት አድርገናል፤ ግን ሰሚ አላገኘንም፡፡ ነገሩም እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ መፍትሔውን በተመለከተ በእኛ ደረጃ ቀርቶ በመንግሥት ደረጃ እንኳ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት የከበደበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እንደሚነገረው የመመርመሪያ ማዕከሉን በኢትዮጵያ ለማቋቋም የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ለግንባታው ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ስለሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሲነገር እንደሰማሁት እስከ 350 አትሌቶችን አገሪቱን ማስመርመር ይጠበቅባታል፣ ይህም በራሱ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድን አትሌት ናሙና ለማስመርመር እስከ 600 ዶላር ይጠይቃል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን እንዲህ ቀለል ተደርጎ የሚነገርበት አግባብ በግሌ ያሰጋኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሚመሩት ከብዙዎች ጋር አልተዋወቅም፡፡ ነገሩ እንዲህ ቆርቁሮኝ የምናገረው ማንንም ለመጉዳትና ለመጥቀም አይደለም፡፡ ስፖርቱ የኖርኩበት ለዚህ ደረጃም የበቃሁበት በመሆኑ ውድቀቱን መመልከት ስለማልፈልግ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጎን ለጎን አሁን ለምትጠቅሰው የአሠራር ክፍተት ሌላ እንደሥጋት የምታክለው ይኖርሃል?

ኃይሌ፡– ለዚህ ጥያቄ መልሴ ጥያቄ ነው፡፡ ተተኪ አትሌቶች አገሪቱ በምትፈልገው መጠን አሏት? በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያሉ አሠራሮች አንዳችም እንከን የለባቸውም? በአሠልጣኝና በአትሌቶች ምልመላና ምዘና ዙሪያስ? በአጠቃላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርስ ያለን ግንኙነት እንዴት ነው? ኢትዮጵያ የበርካታ ታዋቂና ስመገናና አትሌቶች አገር ነች፡፡ ከዚህ አኳያ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ተገቢውን ቦታ ለምን አጣች?

ሪፖርተር፡-  የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ችግሮች የቅርብ ጊዜ ሳይሆኑ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ስለመሆናቸው የሚናገሩ አሉ፡፡

ኃይሌ፡- አሁንም አንከባለን ለተከታዩ ትውልድ እናወርሰው? ወይስ ወይም ተቀራርበን በችግሮቹ ዙሪያ ተነጋግሮ ወደ መፍትሔ መሄድ? በዚህ ዙሪያ እኔም ሆንኩ ባልደረቦቼ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ችግር ትናንት የተፈጠረ ነው እያልን አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ከነበረው ጠንካራውን በመውሰድ ድክመቱን ደግሞ በማረምና ከጊዜው ጋር እኩል ሊራመድ በሚያስችል መልኩ አሠራሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል ነው የምንለው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ የማነሳው ከአትሌቶች ሥልጠና ጋር ተያያዞ በእኛ ጊዜ የነበረው ማለትም የቡድን ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ በአሠራር ሊሻሻል ይገባዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የኦሊምፒክና  የዓለም ዋንጫ አካሄዶች ነበሩ፡፡ እነዚህ አሁን አሉ? የሉም፡፡ በዚህ ዙሪያ ለምን ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በዚያን ጊዜ የአበረታች ንጥረ ነገር ጉዳይ ከነውርም በላይ ነውር ስለሆነ እንዲህ እንደ አሁን ሲወራ አይደመጥም፡፡ የምንገኝበት ዘመን እጅግ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ባለበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እኩል መራመድ ባንችል መከተል ግን የግድ ነው፡፡ የእኛ አመለካከትና የስፖርታችን ‹‹ሶፍት ዌር›› እጅግ በጣም ኋላ ቀር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በዚህ ዘመን አያስኬደንም፤ ይህንን ማስተካከል ይኖርብናል፣ መነጋገር ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡– በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ26 የማያንሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የራሱ ሕንፃ፣ የራሱ ሆቴልና ሌሎችም የገቢ አማራጮች ያሉት በመሆኑ ከሌሎቹ የተሻለ ተደርጎ የሚደመጥበት ነገር አለ፡፡

ኃይሌ፡– ነበረው ብንል ነው የሚያስኬደው፡፡ ምክንያቱም የተጠቀሱት የገቢ ምንጮች መቼ ነው የተገነቡት? መቼ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት? ዛሬስ በምን ደረጃ መገኝት ነበረባቸው? ስንል በነበሩበት ናቸው፡፡ ሀብቱ እንዴት ተገኘ? በጊዜውና በወቅቱ የነበርን ሰዎች እናውቀዋለን፡፡

ሪፖርተር፡– በውስጡ ከነበራችሁ ዝርዝሩን ለመናገር ችግር አለው?

ኃይሌ፡- በግልጽ የምናወራበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች እነ ኃይሌ ይህንን የሚሉት ሥልጣን ፈልገው ነው፡፡ ቦታውን ስላልያዙት ቆጭቷቸው ነው፣ የሚሉ ስለማይጠፉ የዚያ ሱስ እንደሌለብን እንዲያውቁት፤ እስከዚያው ግን አንገብጋቢ ወደ ሆነው የአትሌቲክሱ አሠራርና ውጤት ላይ ብናተኩር ነው የሚበጀው፡፡ በዚህ ጉዳይ መነጋገር ካለብን በጋዜጣና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተናጠል ሳይሆን፣ ይመለከተኛል የምንል ሁሉ መድረክ ተፈጥሮ ፊት ለፊት መሆንም ይኖርበታል፡፡ ያን ጊዜ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት እውነቱን ተረድተው የራሳቸውን ውሳኔ ይሰጣሉ፣ መነጋገር ክፋት የለውም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው ቤቱን ለማፍረስ አይነሳም፡፡ በዚህ በኩል ያልኖሩበት ያላለፉበት ከሕይወታቸው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው ከሆነና አዲስ መጪዎች ከሆኑ ቤቱን ላለማፍረሳቸው ዋስትና የለኝም፡፡ ነባር ነዋሪዎች ከሆኑ ግን አያፈርሱም፡፡ ለዚህም ነው እንነጋገር የምንለው፡፡ በዚህ መልኩ ከሆነና እኔም ሆንኩ ባልደረቦቼ ተሳስተን ከሆነ ሒሳችንን ወስደን አርፈን እንቀመጣለን፣ ምንም ችግር የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት እንደነዚህ የመሰሉ ለስፖርቱ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን ይዛችሁ ለመነጋገር ዝግጁ አይደለንም ያሏችሁ አመራሮች አሉ?

ኃይሌ፡- ጥያቄ ያቀረብነው በፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ወክሎ ለተቀመጠው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ነው

ሪፖርተር፡– ከማኅበሩ ያገኛችሁት መልስ አለ?

ኃይሌ፡– እስካሁን የለም፡፡ መድረኩን  ይፈጥሩናል ብለን እንጠብቃለን፣ ካልሆነም ሒደቱን ጠብቀን ወደ ሚመለከተው አካል የማንቀጥልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሌላው ደግሞ አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆኗል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ተመልከቶ ተመልክቶ አንድ ቀን መጠየቁ አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- በአቤቱታችሁ ውስጥ የሙያ ብቃት ጥያቄም አለ?

ኃይሌ፡– አትሌቲክሱ በፕሮፌሽናሎች መመራት አለበት ብለን ነው የምናምነው፡፡ ስፖርት ስለወደድኩት ብቻ እመራዋለሁ ማለት አይደለም፡፡ መሆንን ይጠይቃል፡፡ እርግጥ ነው ማንም ሳይንሱን ሊማረው ይችላል፡፡ ያንን ወደ መሬት ለማድረግ ግን የሙያው ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡ የስፔኑ ታላቅ ክለብ ሪያል ማድሪድ የሚሠለጥነው በማን ነው? ስፖርት ሳይንስ ባጠናው ዚነዲን ዚዳን ነውን? ይኼ በሪያል ማድሪድ ብቻ አይደለም በእንግሊዝ፣ በጣሊያን በፈረንሣይና በሌሎችም ዓለማት 99 በመቶው ስፖርት የሚመራው በሙያው አልፈው በበቁ ሰዎች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ከዚህ የሚለይበት ምክንያት ለምን? የእኔ ልጆች አትሌቲክስ ይወዳሉ መሮጥ ግን አይችሉም፡፡ መሥራት ያለብንን አውቀን ብንሠራ ችግሩ ምንድነው? ሰዎች በችሎታቸው በአቅማቸውና በእውቀታቸው ልክ ቢሠሩና ብንለውጥ ችግሩ ምንድነው? በግሌ ለሰዎቻችን ልቦና እንዲሰጣቸው ነው የምጠይቀው፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱ ከዚህ በባሰ ሳይወድቅ ማዳን የምንችለው በዚህ መልክ መረዳዳት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ይኼ በአትሌቲክሱ ብቻ አይደለም፡፡ ወጣቶቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር የሚሰዉለት እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ እንደሌላው ሙያ ሁሉ የተከበረ ሙያ ነው፡፡ ስናከብረው ያስከብረናል፣ ስናቀልለው ደግሞ ያቀለናል፡፡ ማስፈራራቴ አይደለም፡፡ አትሌቲክሱ አሁን ከሚገኝበት በበለጠ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገባበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አሁንም ለማስተካከል በትንሹ አምስት ዓመት ያስፈልገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱ በአሁኑ ወቅት በሚጠይቀው ዕውቀትና ክህሎት ልክ ሙያተኞች አሉ ብላችሁ ታምናላችሁ?

ኃይሌ፡- ሁለተኛ ዲግሪና የመጀመሪያ ዲግሪ በሚለው መስፈርት ካልሆነ፣ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ አይደለም በትልልቅ ደረጃ ሳይቀር መምራትና ማስተዳደር የሚችሉ አሉ፡፡ ልምድ ትልቅ ዕውቀት ነው፡፡ በርካታ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች በሁሉም ስፖርቶች እንዳሉ እንሰማለን፡፡ የሥልጠናው ክፍተት እንዳለ ሆኖ የመዋቅር ችግር በትልቁ እየተነሳ ነው፡፡ ታዲያ ችግሩን እንዴት መፍታት አቃታቸው? ምስጢሩ ስፖርት የራሱ አካሄድና ዕውቀት ስላለው ነው፡፡ እንግሊዛዊው ሰባስቲያን ከከአገሩ አልፎ የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ)  እየመራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ ስለምን ተሳነን? በግሌ አቅሙም ሆነ ብቃቱ አለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም ነው ዝምታ ይብቃን! ስፖርቱ ሕይወታችን፣ ማንነታችን ነው ብለን የተነሳነው፡፡ ምክንያቱም ለአትሌቲክሱ የስፖርት ሳይንስ ምሁር አልያም የስፖርቱ ዶክተሮች አበበ መኰንን፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ቀነኒሳ በቀለና ሌሎችም ናቸው፡፡ ይቅርታ ይኼ የሙያ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማለት የሳይንሱ ምሁሮችን ሙያ ለማሳነስ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሙያ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– አትሌቶች እግር እንጂ እስኪቢርቶ የሚጨብጡበት እጅ የላቸውም የሚሉ አሉ፡፡ አባባሉን ትሰሙታላችሁ?

ኃይሌ፡- የምንናገረው ስለምንሰማ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሳይንስ ለስፖርት አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ የስፖርቱ ሳይንስ ከቢሮ ወጥቶ መሥራት አለመሥራቱ እንጦጦ ላይ ሲረጋገጥ ነው የማምነው፡፡ ለሪፖርት ከሆነ ግን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የወረቀት ችግር የለባትም፡፡ በርካቶች አሏት፡፡ በዚህ ቢሆን ኖሮ ስለስፖርታችን ባልተነጋገርን ነበር፡፡ ለእኔ ትክክለኛው የአትሌቲክስ ስፖርት ምሁር አሰላ በቆጂ የሚገኙት አቶ ስንታየሁ እሸቱ ናቸው፡፡ እነ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለና አሁን እስካሉት ጥሩነሽ ዲባባና ሌሎችን በማፍራት የተረጋገጠ ዕውቀት አሳይተውናል፡፡ ይህን የሚክድ ካለ ልንነጋገር እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡– የፌዴሬሽኑን የአመራርነት ሚና ተረከብ ብትባል ተቋሙን ለመምራት ጊዜው ይኖርሃል?

ኃይሌ፡– ከእንግዲህ ከዳር ቆሜ አትሌቲክስ ወደቀ፣ ሞተ ማለት አልፈልግም፡፡ አትሌቲክስ ሁሉ ነገሬ ነው ካልኩ ችግሩን ከመሠረቱ በጣጥሶ ለመጣል ካለኝ ፍላጎት ተነስቼ ነው፡፡ መሥራት ባልችል ለማሠራት ሺዎችን ማቆም እንችላለን፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ እኔ ከምመራቸው ካምፓኒዎቼና ድርጅቶቼ በላይ ነው፡፡ እነዚህ የአትሌቲክሱ ውጤቶች ናቸው፡፡ በማንኛውም መልኩ አትሌቲክሱን ለማዳን ጊዜዬን መስዋዕት ለማድረግ ባልወስን ኖሮ አልናገርም፤ ግን ፍጹም ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ ክፍተቶች ይኖሩብኛል፡፡ ሰዎች ከግል ፍላጎታቸው በመነሳት ከሚለጥፉት አላስፈላጊ ታርጋ ተቆጥበው ለአትሌቲክሱ በጋራ እንነሳ ነው የምለው፡፡ ማናችንም ከአገሪቱ ሕግና ሥርዓት ውጪ ልንሆን አንችልም፡፡ ስፖርቱ የጋራችን ነው፡፡ ለእኔ ደግሞ የተለየ ቦታ ነው ያለው፡፡ ስፖርቱ አንዳንድ ጊዜ ቅንነትን ይፈልጋል ስለሆንም ቅን እንሁን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...