በዚህ ጽሑፍ ስለ ሕገ መንግሥታዊነት እናነሳለን፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት ማለት በሕገ መንግሥት የተዘረዘሩት መሠረታዊ መርሆች በተግባር ሲተገበሩ፣ የመንግሥት ሥልጣን ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ሲገደብ፣ ሕገ መንግሥት በተግባር ከሁሉም ሕግጋትና አሠራሮች በላይ መሆኑ ሲረጋገጥ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው “The noun “constitutionalism” simply means adherence to the principles laid down in the Constitution. It means adherence to constitutional procedures and provisions” የሚለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ሁሉም አገር ሕገ መንግሥት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት የሚኖረው ግን በዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የተቀመጡ መርሆች ተግባራዊ ሲሆኑ ነው፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን መርህ መነሻ በማድረግ በዚህ ጽሑፍ ሕገ መንግሥታዊነትን እንፈትሻለን፡፡
መርሕና ተግባር
ሕገ መንግሥቱ የ20ኛ ዓመት ልደቱን ባከበረበት ማግስት እንኳን ተግባራዊነቱን የሚገዳደሩ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንኳር (አስኳል) የሚባሉት መርሆች ሳይቀሩ ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ መሆን ዳገት ሆኖባቸዋል፡፡ በሕገ መንግሥት ታሪካችን አሁን የያዝነው ሕገ መንግሥት ሃይማኖትንና መንግሥትን ለማፋታት በማሰብ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የመጀመሪያው የ1980ው የደርግ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆኑን በመደንገግ ሃይማኖት የግል መሆኑን ደንግጓል፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ሰው ባለሥልጣንም ቢሆን በግል የመሰለውን ሃይማኖት የመከተል መብት ያለው ሲሆን፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖር ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ሰጥቷል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ከሆኑ ደግሞ መንግሥት አወንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መልኩ በሃይማኖት ላይ ጣልቃ አይገባም እንደማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በደርግ ዘመን የነበረው ተግባር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንዲል በተግባር ሃይማኖቶችና እምነቶች ፀረ ልማት፣ ፀረ አብየትና ጎታች እንደሆኑ ስለሚታሰብ ንብረታቸው ሲወረስ፣ አማኞቻቸው ሲሰደዱ እንዲሁም ተቋሞቻቸው ሁሉ የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ ተመልክተናል፡፡ የደርግ ሕገ መንግሥት ተሞክሮ መንግሥትና ሃይማኖትን የሚያፋታው ሕጉ ብቻ ላለመሆኑ በቂ አስረጂ ነው፡፡ ሕጉ ተፋተዋል ቢልም በተግባር መፋታታቸውን የሚያሳይ አስተሳሰብ ተግባርና ተሞክሮ ከሌለ መለያየታቸው የይስሙላ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ሕገ መንግሥታዊነት ያስፈልጋል፡፡
በ1987 የወጣውና አሁን ከ20 ዓመት በላይ የሆነው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አሉኝ ከሚላቸው ምሰሶ መርሆች አንዱና ዋነኛው ይኼው የመንግሥትና የሃይማኖት ፍቺ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከመውጣቱ በፊት የነበሩት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ያለመው ሕገ መንግሥት፣ የአገሪቱን ሕዝቦች ሕብረ ብሔራዊነትና ብዙኃ ሃይማኖትነት በግልጽ አውጇል፡፡ ከእምነት ነፃነት አንፃር የግለሰቦች የሃይማኖት መብት የፈለጉትን እምነት በመምረጥ፣ በግል ወይም በኅብረት እምነታቸውን በመግለጽ የተከበረ መሆኑን ከመግለጽ በተጨማሪ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ እንደማይገባ ተደንግጓል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነፃነት ተከብሯል፣ ሃይማኖቶች እኩል መሆናቸው ተሰምሮበታል፣ መንግሥቱም ሴኩላር፣ በሃይማኖት ጣልቃ የማይገባ፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት የሌለበት የሕግ ሥርዓት መሠራቱን ሕገ መንግሥቱ በተለያዩ ድንጋጌዎቹ አስቀምጦ እናገኛለን፡፡ አሁንም የዚህ ሕገ መንግሥት ጥንካሬ የሚታየው ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ድንጋጌዎቹን ለማስፈጸም መንግሥት ባለው ቁርጠኝነት ላይ ነው፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖቱ ፍቺ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተከብሮ በተግባር በአንድም ሆነ በሌላ ከተጣሰ ወይም ሊከበር የሚችልበት ተቋማዊና ባህላዊ አሠራር መመሥረቱን ካላሳየ ከቀድሞው ሕገ መንግሥት እንደሚለይ አጥብቆ መከራከር አሳማኝ ላይሆን ይችላል፡፡ አሁንም የጥሩ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረቱ ሕገ መንግሥት መኖሩ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ የያዛቸው መርሆች በተግባር ሲተገበሩ ሕገ መንግሥታዊነት ሲኖር ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ ላይ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን ደንግጎ በተግባር አለማክበርና በሕገ መንግሥት መርሁን ሳይደነግጉ አለማክበር ልዩነታቸው ሰፊ ላይሆን ይችላል፡፡ በሕገ መንግሥት መደንገግ የሃይማኖት ነፃነት፣ ራሱን ችሎ ከመንግሥት ድጋፍና ነቀፌታ ውጭ በምልዓት ለመተግበር፣ የሕግ ዋስትና ለማግኘት እንደሚረዳ የታመነ ነው፡፡ ግን በሕጉ ላይ ያለው በተግባር የማይከበር ከሆነ ግን የሕገ መንግሥታዊነትን ባህልን ስለሚያጠፋ አደጋ ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥት መቅረፅ ሕገ መንግሥታዊነትን ከማምጣት ይቀላልና፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሃይማኖትና የመንግሥትን መለያየት ባልደነገገበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማምጣት፣ መብቱን ለማስከበር መግፍኤ ምክንያት ይሆናል፡፡ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩት ሕገ መንግሥታት አንዱን ቤተ እምነት መንግሥታዊ ሃይማኖት በማድረጋቸው የሃይማኖት ተቋማት በእኩል የማይታዩ ሆነው ነበር፡፡ የመንግሥት ሃይማኖት የነበረችይቱም የውስጥ የእምነት ነፃነት ስላልነበራት፣ ከጥቅሙም ጉዳቱ ስለሚያመዝን ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ለማምጣት መነሻ ሆኗል፡፡ በዚህ ዘመንም በሕገ መንግሥቱ መርሁን ከመቅረፅ እኩል ወይም በላቀ መልኩ ለአፈጻጸሙ፣ ለተግባራዊነቱ ካልታገልን የመርሁን መኖር ጥቅሙን ለመመስከር ያስቸግረናል፡፡
ይዘቱና መንፈሱ
የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት አሁን ባለው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 11 እና በአንቀጽ 27 ላይ በግልጽ ተደንግገዋል፡፡ የመጀመሪያው ስለ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ይናገራል፤ ሁለተኛው ደግሞ ስለ እምነት ነፃነት ይደነግጋል፡፡ የመጀመሪያው ድንጋጌ ሦስት መሠረታዊ መርሆችን ቀርጿል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፣ እንዲሁም መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ከተቋማቱ ልዩነትና እያንዳንዳቸው ከሚሠሩት ሥራ መለያየት ጋር ይያያዛል፡፡ መንግሥት ጳጳሳትን ለቤተ ክርስቲያን አይሾምም፣ የመስኪድ ኢማሞችን ወይም የፕሮቴስታንት ፓስተሮችንም አይሾምም፡፡ ሥራቸውንም አይመራም፣ በበላይነት አይከታተልም፡፡ የሃይማኖት ጉዞአቸውን ወጪ አይሸፍንም፣ ዕቅድ አውጥቶ አያስፈጽምም፡፡ ቤተ እምነቶቹም ፕሬዚዳንቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን፣ ሚኒስትሮችን ወይም ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎቹን አይሾሙም፤ ሥራቸውንም የመምራት ሥልጣን የላቸውም፡፡ በአፄዎቹ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ነገሥታቱን እንደምትቀባው፣ በፀሎት እንደምታነግሰው፤ አሁን ቤተ እምነቶች መንግሥት የሚሾማቸውን ባለሥልጣናት አትቀባም፣ የፀሎት ሥርዓትም አታከናውንም፡፡ መንግሥት ከፈጣሪና ከአምላክ ጋር በተያያዘ እምነቱን የመወሰን ድርሻም ሥልጣንም የለውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያም ይህንኑ ነው በአጽንኦት የሚገልጸው፡፡ ማብራሪያው፡-
‹‹መንግሥት የሃይማኖት ነፃነት ከማስከበር በቀር የሃይማኖት ተቋማትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን አያደራጅም፤ አያግዝም፣ መንግሥት የሃይማኖት ስብከት የሚካሄድበትን ትምህርት ቤት አይከፍትም፤ ለሃይማኖት ትምህርት ቤቶችም ዕውቅና አይሰጥም፡፡ በመንግሥት ሥራ ላይ እስካለ ድረስ ማንም የሕዝብ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን ለየትኛውም ሃይማኖት መወገን አይኖርበትም፤›› ይላል፡፡
ሁለተኛው ድንጋጌ የሃይማኖት ነፃነትን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው አለማመንን ጨምሮ የመረጠውን ሃይማኖት የመያዝ፣ የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረትም ማንኛውም ሰው የመንግሥት ተሿሚን ጨምሮ በግሉ የመረጠውን እምነት የመከተልና የመተግበር መብት አለው፡፡ በግል ሕይወቱ ዝክርም ይዘክር፣ ሰደቃም ያውጣ፣ ጭንቅላት ላይ ጭኖም ይፀልይ ሕገ መንግሥቱ አይከለክለውም፡፡ የሚከለክለው እምነት አገላለጽ ከጤና፣ ከሰላም፣ ከሞራል ወይም ከደኅንነት ጋር እንዳይጋጭ ነው፡፡ እምነቱን ከግሉ ባለፈ በሕዝብ ተቋማትና በተሰጠው ሥልጣን ላይም ከተጠቀመበት ግን ሕገወጥ ይሆናል፤ ኢ-ሕገ መንግሥታዊም ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ ስለ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት እንደዚህ ዓይነት ድንጋጌዎችን ከያዘ አፈጻጸሙ ለምን ዳገት ሆነበት? መርሁ በሕገ መንግሥት ደረጃ ዋስትና ማግኘቱን እስከምንረሳው ድረስ አሁን አሁን የምንመለከታቸው ተግባራት አሳሳቢ ሆነዋል፡፡ ጸሐፊው ከዚህ ቀደም በዚህ አምድ ላይ በጻፋቸው ጽሑፎች የሃይማኖትና መንግሥት መለያየትን በተግባር በጥሞና እንድንመለከተው ያደረጉንን ሁለት ማሳያዎች በመዘርዘር ጉዳዩን ተመልክቶታል፡፡ በቤተ እምነት ተከታዮች መካከል የሚታዩ የትንኮሳ ወይም የጠብና የጥላቻ ሁኔታዎችና አንዳንድ ቤተ እምነቶች በደብዳቤዎቻቸው ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ባለሥልጣናት ግልባጭ በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን እየሸረሸሩ መሆኑን አንስተን ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡
የጥሰት ዓይነት
የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት መርህ ከሚጣስባቸው አጋጣሚዎች አንዱና ዋነኛው መንግሥት በዜጎች የሃይማኖት ነፃነት መብት ላይ ወይም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሲገባ ነው፡፡ መንግሥት ስንል ተቋማቱና መንግሥት የሾማቸውን ባለሥልጣናት ማለታችን ነው፡፡ ይህ ጥሰት በሦስት መልኩ ሊፈጸም ይችላል፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን ለመገደብ የሚሆኑ ምክንያቶችን አስፍቶ ወይም ለጥጦ በመተርጎም የሃይማኖትንና የመንግሥትን መለያየትን መርህ ሲጥስ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያም ይህንን ተግባራዊ ምልከታ የተከተለ ይመስላል፡፡ ማብራሪያው የዜጎች የእምነት ነፃነት እንዲረጋገጥ መንግሥት በሃይማኖታዊ ጉዳይ እጁን ማስገባት እንደሌለበትና በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ካስገባ ግን ከሌሎቹን ዜጎች በተለየ ዓይን ተመለከተ ማለት እንደሆነ መግለጹ በዚህ መነሻነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በመግባት አጀንዳ በመቅረፅ፣ መመርያ በመስጠት በአስተዳደሩ፣ በሥርዓቱ፣ በአመራሩ ወዘተ. የሚፈተፍቱ ከሆነ ሕገ መንግሥቱ ያልፈቀደላቸውን ሥራ እየሠሩና የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት (Secularism) መርህን እየጣሱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ አንዳንድ የዋሃን የሃይማኖት አባቶች ‹‹እከሌ የተባለ ባለሥልጣን እንዲህ ብሎኛል፣ ይህን መመርያ ሰጥቶኛል፤›› እያሉ በስም ሳይቀር ሲናገሩ መሰማታቸው የሚዘገበው ከዚህ አንፃር ነው፡፡
ሁለተኛው መንግሥት፣ ተቋማቱና ባለሥልጣናቱ በቤተ እምነቶች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በገለልተኝነትና መርህን መሠረት አድርገው ካልመሩትና ካልመዘኑት መርሁ መጣሱ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድ አካባቢ የአንድ ቤተ እምነት አማኞች የሌላውን አማኝ ማምለኪያ ቦታ ሲያቃጥሉ፣ አማኝ ሲያፍኑ ወይም ሲደበድቡ የሚመለከተው ባለሥልጣን ከግል እምነቱ ገለልተኛ በሆነ መልኩ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ ተጎጅዎች እንዲካሱ፣ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ካላደረገ የመንግሥት ድርሻና የቤተ እምነቶቹ ድርሻ ተቀላቅሎ መርሁ ይጠፋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የመንግሥትና የሃይማኖት ፍቺ መርህ ሊጣስ የሚችለው መንግሥትን የሚወክሉ ሠራተኞች፣ ሹሞች ወይም ባለሥልጣናት በሕቡዕ ወይም በግልጽ አንድን እምነት የሚጠቅም ወይም የሌላውን የእምነት ተከታይ የሚጎዳ ሥራ ሲሠሩ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ባለሥልጣናት በግላቸው የፈለጉትን እምነት መከተላቸውን ባይከለክልም፣ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው ግን የተሾሙበት የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርግባቸው አይፈቅድም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በእጁ ስላለ ብቻ እሱ የሚከተለውን እምነት ወይም ሃይማኖት የማይገባውን የመንግሥት ልዩ ጥቅም (ነፃ ግብር፣ ቦታ፣ ፈቃድ ወዘተ.) የሚሰጥ ከሆነ ሕገ መንግሥታዊነትና የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት ውኃ በላው ማለት ነው፡፡
በአንዳንድ አገሮች የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ቢኖርም ለርዕሰ ብሔር ወይም ለመሪ በእምነታቸው ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ የሚፈቀድበት ሕግ ወይም ልማድ ይኖራቸዋል፡፡ በእንግሊዝ ንግሥቷ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንንና እምነቱን ለመጠበቅ የምትገባውን ቃለ መሃላ ዓይነት ወይም በልማድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በቃለ መሃላው እግዚአብሔርን ሊጠራ እንደሚገባው ዓይነት ማለት ነው፡፡ በአገራችን ግን በሕግም ሆነ በልማድ በእግዚአብሔር ስም ቃለ መሃላ እንዲፈጸም፣ በመንግሥታዊ ሥራ ፓርላማን ጨምሮ የአንድ እምነትን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ንግግር ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ይከለክላል፡፡
ሕገ መንግሥታዊነትን ዋስትና መስጠት
የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት በሕገ መንግሥቱ ላይ መኖራቸው መልካም ቢሆንም አለመፈጸማቸው ሕገ መንግሥታዊነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከወጣ 20 ዓመታት ቢያልፉም የመለያየቱን ምንነት፣ ስፋትና ጥበት፣ የመንግሥትና የሃይማኖት ድጋፍና ትብብር በዝርዝር ፖሊሲና ሕግ አለማብራራቱ መርሁ ሰርጾ እንዳይታወቅ፣ እንዳይተገበር፣ ጥሰቶች ተለይተው እንዳይወጡ ያደረጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሕግ ሥርዓት ጥናትና ምርምር ተቋም የተወሰነ ጅምር ቢኖርም ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት የሚረጋገጠው መርሁን በመዘርዘርና የባለድርሻ አካላትን ኃላፊነት በማመልከት ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት በግልና በሥራ ኃላፊነት በሚሠሯቸው ሥራዎች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ካላወቁ እንኳን ሕገ መንግሥታዊነትን እውን ሊያደርጉ ሕገ መንግሥቱንም ሊጥሱ ይችላሉ፡፡ ሥልጣን ያለተጠያቂነት አይሰጥም፡፡ ከተሰጠም ፍጹም ይሆናል፡፡ ፍጹም ሥልጣን ደግሞ ፈጽሞ ያባልጋል፡፡ Absolute power corrupts absolutely እንዲል፡፡ ሕገ መንግሥትን የመጣስ አዝማሚያ በእንጭጩ ካልተቋጨ አደጋው ሰፊ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ትርጉም የሚኖራቸው ሕገ መንግሥታዊነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ነው መንግሥትም ከሃይማኖት መፋታቱን አምነን የምንቀበለው፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡