በመርሐ ጽድቅ መኮንን ዓባይነህ
የደርጉ ጊዜ ዓይነት ይሁን አይሁን ገና በውል ባይታወቅም፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ይዋቀር ዘንድ ወሬ ከመሆን አልፎ የማቋቋሚያ ረቂቅ ሕግ እንደተዘጋጀለትና ይኸው ረቂቅ ለአገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውሳኔ እንደቀረበ ተሰምቷል። ይኼው ሰበብ ሆኖ ታዲያ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚፈርስና የእሱ የነበሩት መብቶችና ግዴታዎች ሁሉ አዲስ ወደ ሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንደሚተላለፉም በሰፊው እየተነገረ ነው።
ለመሆኑ ዓቃቤ ሕግና ፍትሕ ሚኒስቴር ምንና ምን ናቸው? ዓቃቤ ሕግ ተመልሶ እንዲያንሰራራስ ፍትሕ ሚኒስቴር መቀመቅ መውረድ ይገባዋልን?
የዚህ ጽሑፍ ባለቤት በወደቀውም ሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ባለው ተከታታይ መንግሥታት በተለያዩ ደረጃዎች ዓቃቤ ሕግ ሆኜ የመሥራቴ አጋጣሚ ስላነሳሳኝ፣ ከፍ ብዬ የሰነዘርኳቸውን ጥያቄዎች በመንተራስ ይችን አጭር አስተያየት አዘጋጅቻለሁና ለንባብ እንድትበቃ ብታደርጓት።
በመሠረቱ ፍትሕ ሚኒስቴር ዘርፈ ብዙ የፍትሕ አስተዳደር ተግባራትን እንዲያከናውን በሕግ የሚቋቋም አንድ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ ራሱን የቻለ የዓቃቤ ሕግ አደረጃጀት በሌለባቸው አገሮች ይኼው የአቂቦተ ሕጉ ኃላፊነት የሚሰጠው ለዚሁ መሥሪያ ቤት ነው። በሌላ አነጋገር ፍትሕ ሚኒስቴር በጠባዩ የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ጭምር ሲሆን፣ ሚኒስትሩም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጭምር እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የፍትሕ ሚኒስቴር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የካቢኔው አንድ አባል በመሆኑ፣ ይኼው አካል የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግነትን ሥልጣን ደርቦ የያዘ እንደሆነ ገለልተኝነት ስለማይኖረው በሕግ አስከባሪነት ሥራው ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርበት ይታመናል።
ስለሆነም ፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ጭምር በሚሠራባቸው ወይም አሁን በአገራችን እየታሰበ ባለው መንገድ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ራሱን ችሎ በሚደራጅባቸው ሥርዓቶች፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መሆኑ ቀርቶ ለሕግ አውጭው ምክር ቤት እንዲሆን የሚደረግበትን የተሻለ አማራጭ መከተል የተለመደ ነው። እንደ ጠቃሚ ልምድ ከተወሰደ ለአጭር ጊዜ የተሠራበት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤትም ይኼው ዓይነት ተጠሪነትና ቁመና እንደነበረው እናስታውሳለን።
ይህ ጸሐፊ በአሁኑ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አግባብ ባለው ቋሚ ኮሚቴ እየታየና የሕዝብ አስተያየት እየተሰበሰበበት የሚገኘውን የአዲሱን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያና ማደራጃ ረቂቅ አዋጅ በወፍ በረር መንገድም ቢሆን የመቃኘት ዕድል አጋጥሞታል። አዲሱን ጽሕፈት ቤት በአዲስ መልክ ለማቋቋም የተፈለገበት ዓይነተኛ ምክንያት በተለያዩ የተናጠል አዋጆች ወደ ተለያዩ አስፈጻሚ አካላት የተበታተኑትን የዓቃቤ ሕግ ተግባራትና ኃላፊነቶች መሰብሰብና በአንድ ጠንካራ አካል መዳፍ ሥር እንዲጠቃለሉ ማድረግ እንደሆነ የረቂቁ መግቢያ አስምሮበታል። በእኔ አስተያየት ይህ የፖሊሲ መንደርደሪያ የሚተችበትም ሆነ የሚነቀፍበት አንዳች ሕጋዊ ምክንያት የለም።
በአሁኑ ወቅት ባልተጠና ዕቅድ የተበተነውን የዓቃቤ ሕግ ሥራ ሌላው ቀርቶ በቁጥር ማስታወስ አይቻልም። ለእያንዳንዱ አካል የተሰጠውን የዓቃቤ ሕግ ሥራ ውጤታማ አተገባበርም በተማከለ መንገድ ለመከታተል የሚያስችል አስተማማኝ ሥርዓት የለም፡፡ ቢኖርም እንዳለ አይቆጠርም። ለምሳሌ የፌዴራሉ መንግሥት ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀሎች ረገድ ብቸኛ መርማሪ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ሆኖ በአዋጅ ተቋቁሟል። ከዚህ የተነሳ የፍትሕ ሚኒስትሩ በመርህ ደረጃ የአገሪቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሆኑ ቢታወቅም፣ ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀሎች መርማሪነትና ዓቃቤ ሕግነት የሚፈጽማቸውን ተግባራት ሕጋዊነት በቅርብ የመከታተልም ሆነ የማረም ዕድል የለውም።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጉምሩክ ወንጀሎችን የመመርመር፣ የማጣራትና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለፌዴራሉ መንግሥት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ይህ ጉዳይ ለፍትሕ ሚኒስቴር እንግዳና የማያውቀው ነገር ነው። ስለሆነም ፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ዓቃቤ ሕግ አለኝ የሚለው ሥልጣን በተለያዩ አዋጆች ባልተጠና መንገድ ያላግባብ ሲሸረሸር እንደቆየና ይህ ሁኔታ በአፋጣኝ መታረም እንዳለበት አንድና ሁለት የለውም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕግ ባለሙያዎችን በሰፊው እያነጋገረ ያለው ዓብይ ነጥብ ዓቃቤ ሕግ የሾለኩበትን ሥራዎች ከየሥርቻው የመለቃቀሙና በተማከለ መንገድ የመደራጀቱን ፋይዳ የሚመለከት አይደለም። ከእሱ ይልቅ ጠንካራ ውይይት የቀሰቀሰው በዚሁ የአደረጃጀት ለውጥ ሳቢያ ከፌዴራል መንግሥት ቁልፍ አስፈጻሚ አካላት አንዱ የሆነው ፍትሕ ሚኒስቴር ከናካቴው ይፈርሳል መባሉ ነው።
ዕርምጃው ብዙ የታሰበበት አይመስልም። በዚያ ላይ ክፉኛ የተቻኮለና የዘርፉን ባለሙያዎች አስተያየት ያላካተተ ሆኖ አየዋለሁ። በግዕዝ ቋንቋ ‹‹አቀበ›› ማለት ‹‹ጠበቀ›› ማለት ነው። ከዚህ ሥርወ ቃል ስንነሳ ‹‹ዓቃቤ ሕግ›› የሚለው ሐረግ ሕግ ጠባቂ፣ አስጠባቂ ወይም በሌሎች ዘንድ ሕግና ሥርዓት መጠበቁን ለማረጋገጥ የተደራጀ ወይም የሚደራጅ ተቋምን ይገልጽልናል።
ክላሲካል ከሚባሉት አያሌ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣንና ተግባራት መካከል፣
- ወንጀል ለመፈጸሙ ሲታመን ምርመራ እንዲደረግ ማዘዝ፣
- የወንጀል ምርመራ ተግባራትን ሕጋዊነት መከታተል፣
- ያላግባብ የተጀመረን የወንጀል ምርመራ ማስቆም፣
- አጥጋቢ ማስረጃ ያልተገኘበትን የምርመራ መዝገብ መዝጋት፣
- ወንጀል ለመፈጸማቸው አሳማኝ ማስረጃ በተገኘባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን የሕግ አንቀጽ ጠቅሶ የወንጀል ክስ መመሥረት፣
- መከራከርና ማስወሰን፣
- እንደተገቢነቱ ወደፊት የማንቀሳቀስ መብትን ጠብቆ የወንጀል ክስ ማንሳት ወይም ማቋረጥ፣
- በማረፊያ ቤቶች ቆይታና በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙትን ተጠርጣሪዎችና እስረኞች አያያዝና እንክብካቤ መከታተል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ስለሆነም የፊዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንደገና ቢቋቋም ትኩረቱን የሚስቡት ዓይነተኛ ሥራዎቹ ከፍ ብሎ የተገለጹት ናቸው። እንዲጠናከር የሚያስፈልገውም እነዚህን ሥራዎች ማዕከል አድርጐ ቢሆን ይመረጣል።
ይህ ሲባል የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው ማለት አይደለም። የመንግሥትና የሕዝብን መብቶችና ጥቅሞች በሚነኩ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችም ቢሆን፣ ሕጋዊ ወኪልና የክርክር ተካፋይ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
ከእነዚህ ውጪ ያሉት የፍትሕ ሚኒስቴር ሥራዎች በተዘዋዋሪ ካልሆነ በስተቀር ዓቃቤ ሕግን በቀጥታ የሚመለከቱ ናቸው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ፣
- የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት ማስፋፊያና ሥርፀት፣
- የንቃተ ሕግ ማዳበሪያ መርሐ ግብሮች፣
- ሕጐችን የማጠቃለል (Codification)፣
- የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥና ሥነ ምግባር ቁጥጥር፣
- የይቅርታ ጥያቄዎች መስተንግዶና ምላሽ አሰጣጥ፣
- የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች አተገባበር፣… ወዘተ በሚኒስቴሩ እንደተያዙ መቀጠል ያለባቸው ተግባራት ናቸው።
እነሆ ሚኒስቴሩን እንደታሰበው በማፍረስ ይህንን ሁሉ ፈርጀ ብዙ ኃላፊነት በአዲስ መልክ ለሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ለማሸከም የሚደረገው እንቅስቃሴ ‹‹የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ›› እንዳይሆን ክፉኛ የሚያሠጋ ነው። ሊዋሀዱ የማይችሉትን ሁሉ ለማዋሀድ እየተደረገ ያለው ጥረት ያሰብነውን ውጤታማነት አያረጋግጥልንም።
በደርግ ውድቀት ዋዜማ ተቋቁሞ የነበረው የሶሻሊስት ሕጋዊነት አስከባሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ከፈረሰባቸው ዓይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ከአቅሙ በላይ በተሸከመው ኃላፊነት መሽመድመዱ ነበር። ያም ሆኖ ደርግ ፍትሕ ሚኒስቴርን በተዳከመ ቁመናም ቢሆን ማስቀጠሉን እንጂ ከናካቴው መቀመቅ ማውረዱን አልመረጠም። የአሁኑ ዓይነት የጥሎ ማለፍ ዕርምጃም አልታየውም። ዛሬም ቢሆን ተቋማትን ለማፍረስ አንጣደፍ፡፡ መገንባት የማፍረሱን ያህል ቀላል አይሆንም፡፡ ለምንወስዳቸው የማሻሻያ ዕርምጃዎች ሁሉ አሳማኝ ምክንያት ይኑረን፡፡ በዘርፉ ያገለገሉትን ቀደምት ሙያተኞች ምክርና አስተያየት ከመጠየቅም ሆነ ከመቀበል ፈጽሞ አንፍራ፡፡ ለለውጥ ያለን ፍላጐት በጐ ቢሆንም በዕውቀት ካልተመራ ገደል ይከተናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡