Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገሬ ኢትዮጵያ ሐዘንሽን ያቅልለው!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ናችሁልኝ? ‹‹እንደርሳለን ብለን ከመሸ ተነስተን፣ ስንገሰግስ ነጋ ምንድነው የሚሻለን?›› አለችላችሁ አንዷ አዝማሪ። እውነቷን ነው እኮ! በዚህ አካሄዳችን እንኳን ልንደርስ የት እንደምንሄድም የምናውቅ አንመስልም፡፡ ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ማንጠግቦሽን እንዲህ ብላት፣ ‹‹ኧረ ተረጋጋ። እንዴ ቅዠትና እውነትን ለይ እንጂ?›› አለችኝ። ስንት መልካም ጅማሮዎች ባሉት በዚህ ጊዜ የእኔስ እንዲህ ማለት አይገርማችሁም? ቢሆንም አንዳንዴ አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ ግን ብዙ ያስብላል፡፡

በዚህ መነሻውና መድረሻው በተዘበራረቀበት የሰው ልጅ የአኗኗር ሁኔታ መስመር አስምሮ መጓዝ እጅግ ከባድ ነገር ነው። አንዳንዱ ከመሬት ተነስቶ የገንዘብና የዝና ባለቤት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አፈር ግጦ ሳያልፍለት ዕድሜውን ይገፋል፡፡ ለአገሩ ምኑንም ሳይሰስት ሕይወቱን የገበረ ደግሞ እንደ ቀልድ ፍንግል ብሎ ሲቀር ያስቆጣል፡፡ እኔ ይኼ ያንገበግበኛል፡፡ እኔ ደላላው አምበርብር ምንተስኖት ምን ደላላ ብሆን ልቤ አዛኝ ነው፡፡ ሐዘን ሲሰማኝ ደግሞ ይከፋኛል፡፡ በተለይ ለአገሩ ሲለፋ በከንቱ የቀረ ወገኔ ጉዳይ ያንገበግበኛል፡፡

አንድ በይደር አቆይቼ የምጨርሰው ሥራ ስለነበረኝ ማንጠግቦሽ ሳታየኝ ተነሳሁላችሁና ወጥቼ ገሰገስኩ። መቼም እሷ ከአልጋ ወርዳ የሚታያት ቁርስ አሰናድታ አብረን መቀማመስ ነው። እህል ሳልቀምስ መውጣቴን በምንም ዓይነት ሁኔታ አትቀበለውም። ‹‹የዘመኑን የየዕለት ሰቀቀን እንኳን ሳንበላ በልተንም አልቻልነው፤›› ትለኛለች። ‹የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም› የሚባለውን ሰምታ ነዋ። እኛም ሲባል (ድሮ ነው ታዲያ) እናስታውሳለን። አሁን አሁን ግን ሰምቻት የማላውቅ አባባል ብትኖር ይህችው ‹የበላና የተማረ . . . › የምትባለዋን ነው። ለምን አትሉም? ተበልቶም ተምሮም አልሆንል ብሏላ። ቀልዴን እኮ አይደለም! እንቀልድ ብንልስ አጠገባችን ያለው ተጨባጭ ሀቅ እንዴት ያስችለናል?

ትንሽ እንደተጓዝኩ ይሞረሙረኝ ጀመር። የወጣሁበትን ሳላሳካ እንደማልመለስ ለራሴ ቃል ገባሁ። ኑሮ ሲወደድ አማራጩ እንዲህ ራስን ማበረታታት ነው። አይመስላችሁም? ‹‹መንግሥትም ግሽበትን መቆጣጠር ካልቻለ ከኢቲቪ ጋር ተባብሮ ኑሮን በፅናት ለመጋፈጥ የሚያስችል ቅስቀሳ ቢያስደምጠን ሳይሻል አይቀርም፤›› ይለኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ከወደቅንም የቻሉትን ያህል ተላትመዋል ብሎ ዶክመንተሪ ቢያሠራልን ቀላል ውለታ አይደለም፤›› ይለኛል። ነገረኛ ነው እኮ አንዳንዴ። ለ‹‹ሌጋሲ›› ማሰብ ማለት ከዚህ ይጀምራል አልኩና ለራሴ ብቻዬን መቆዘም ጀመርኩ፡፡    

 የቁሳቁስ ደላላ መሆኔ ስንት ነገር ያሳየኛል መሰላችሁ? ከአንዱ ወደ አንዱ ስዘዋወር የማላየው ታሪክ የለም። እኔ ልሙት! አንድ ቤት ገብቼ የሰማሁትና ያየሁት ግን አስደነገጠኝ። በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ቁም ሳጥን በአዲስ ሊተካ ተፈልጎ እሱን ተዟዙሬ እያየሁ ዋጋ እገምታለሁ። ባል ሚስትን፣ ‹‹ያን የምወደውን እንቁላል ፍርፍር በሥጋ ሥሪልኝ?›› እያለ ይለማመጣል። ‹‹ራስህ አትሠራም? ገረድህ መሰልኩህ?›› ስትለው ጆሮዬን ተጠራጠርኩ። ሙያሽ ናፈቀኝ ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል የሚያናግር ብዬ ክው አልኩ። በዚህ ዓይነትማ ምን ኑሮ ብቻ ተወደደ? የሚስቶቻችንም እጅ ነው እንጂ! ሲገኝም እኮ ጣፍጦ ካልተቀመሰ ዋጋ የለውም። የእኔን ትዳር ባየ ቁጥር፣ ‹‹አንበርብር እንዳንተ የታደለ ሰው አለ?›› የሚለኝ ትኩስ ጎጆ ወጪ ወዳጅ አለኝ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹የእኔዋ እኮ እንትን አማረኝ፣ እንትን የሚባል ቤት ተከፍቷል፣ እዚያ ሄደን እንብላ ቅብጥርሶ እንጂ፣ እስኪ ዛሬ ሙያዬን ቅመሰው ብላ አመሥግኛት አላውቅም፤›› ይለኛል ምርር ባለ ድምፀት። ተው አንተ ሰው አትማረር፡፡

እንግዲህ ሁሉም እንደሚያውቀው ማንጠግቦሽን በጣም የማከብራትና የምወዳት ባለቤቴ ናት። ሴቶች ወደ ማጀት ወንዶች ወደ ደጅ የሚባል ያረጀ ያፈጀ ተረት እኛ ቤት አይሠራም። ግን የተፈጥሮ ነገር ሆነና ከእኔ በላይ እሷ ጓዳ ስትገባ ነገሩ ሁሉ ይሰካካላታል። እጇ እንዴት ባለሙያ ነው መሰላችሁ? ሙያ በባለሙያና አቅሙ ባለው ሰው ሲከውን ወደር የለውም ያልነው እኮ ለዚህ ነው። የውዷን ባለቤቴን እጅ ለምጄ ደጅ ለደጅ በየካፌው የማባክነው ረብጣ የለም እላችኋለሁ። መተባበር ሳይረሳ ነው ታዲያ። መታደል ነው አትሉም?! እሷ ባትኖር ምን ይውጠኝ ነበር?

 የእኩልነት ትርጉሙ የተዛባባቸው እህቶቻችን አንዳንድ ያልተገባ አመልና ባህሪ ሲያሳዩ ብዙ የምታዘብበት ሁኔታና ወቅት አያሌ ነው። ለአገርና ለዓለም ስንጠብቃቸው አንድ ታዋቂ ‹‹ብራንድ›› ቻፒስቲክ እንደ ትልቅ ሥራ በፍለጋ ቀንና ሳምንት ሲያቃጥሉ ሳይ እጅግ አዝናለሁ። ታዲያ አንዷን መንገድ ላይ መሬት መሬቱን ስታይ አገኘሁዋት። የጣለችውን ዕቃ እንደምትፈልግ ጠረጠርኩ። በጠዋቱ ምን ዕቃ ጣልሽ ስላት ዕንባዋ ዱብ ዱብ አይል መሰላችሁ። ወርቅ ይሆን? የለም የአልማዝ ፈርጥ መሆን አለበት እያልኩ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ። ‹‹እህቴ ለቅሶ ምን ይፈይዳል? ንገሪኝ የጠፋብሽን?›› ስላት ‹‹ማታ ወደቤት ስገባ እዚህ ጋ ነው የጣልኩት፤›› አለችኝ። ‹‹እኮ ምንድነው እሱ?›› ስላት ጭንቅ ብሎኝ፣ ‹‹ቻፒስቲክ›› ብላኝ እርፍ። እውነትም ሥራ አጥነት ተስፋፍቷል። ይኼ ዘመናዊነት ያልደረሰበት ሥፍራና ሰው እንዳለ አስተዋልኩ! ኧረ እየተስተዋለ፡፡

በሉ እንሰነባበት። የሄድኩበትን ጉዳይ ረፋዱ ላይ ጨራርሼ ደህና ረብጣ መቁጠሬን ሳረጋግጥ ዳቢትና ሻኛ በዓይኔ ላይ ሄዱ። የሚያምረንና የሚመጥነን ማስታረቅ እንዴት ከባድ እንደሆነ እንደኔ ደህና ዝግ ስትዘጉ ታውቁታላችሁ። ብቻ ምን አባቱ ሺሕ ዓመት አይኖር አልኩና መቼም ብቻዬን መቁረጥ አልወድም ደውዬ የባሻዬን ልጅ ጠራሁት። አስቆርጠን በአዋዜ መተምተም እንደ ጀመርን የባሻዬ ልጅ ጨዋታ ጀመረ፡፡ ‹‹እኔ ምለው አንበርብር ሰሞኑን አንድ የአገራችን ታላቅ ባለሀብት ምን እንዳለ ሰማህ?›› አለኝ። ‹‹ምን አለ?›› ብለው፣ ‹‹ነጋዴዎች ስንባል ቀጣፊዎች ነን ብሎ፣ መንግሥት አንዳንዴ ዓይኑን ቢጨፍንልን ጥሩ ነው አለ ተባለ፤›› ብሎኝ አዋዜው ላይ አነጣጥሮ ዝም አለ። ምን ሊለኝ እንደፈለገ አልገባኝም።

እናስ ስለው፣ ‹‹መንግሥት የሕዝብ ተወካይ ነው። ሕዝብ ነው የሾመው። እናም ያላግባብ የሚባክን ሀብትን እየተከታተለ ሥርዓት ማስያዝና ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት። ለዚህ ነው ሕዝብ መንግሥትን ወክለኝ ያለው። የእዚህ ሰው አባባል ከዚህ ተወካይነቱ ውረድ ማለት አይመስልህም?›› ሲለኝ የፈራሁት መጣ አልኩ። በፍጥነት ያጠቀስነው አዋዜ ማለቁን አየና አዋዜ ጭማሪ ጠይቆ፣ ‹‹እንዲህ የቁርጥ ፍቅር ላይ የጣለን እኮ አዋዜ የተባለው ማጣፈጫ ነው። ቆንጠጥ ሲያደርገን ጣዕሙ ይታወቀናል፤›› ብሎኝ ዝም ሲል ከጥያቄው ጋራ የአዋዜ ትንታኔውን እንዳገናኘው የፈለገ መሰለኝ። ጭማሪ አዋዜው እስኪመጣ ትንሽ ካረፍን በኋላ ሲመጣ እውነትም ጣዕሙ የበለጠ ሆነ። ‘ያለ አዋዜ ቁርጥ ያለ መንግሥት አገር’ እንደማይታሰብ ገባኝ። መንግሥት እንግዲህ ሕግ ሲያስከብር ማለት ነው፡፡

ማወራረጃ ፍለጋ የተለመደችው ግሮሰሪ ስንደርስ የሐበሻ ልጆች ነገን የረሱ እስኪመስሉ ድረስ ያንቆረቁሩታል፡፡ ከጂን እስከ ቢራ፣ ከቢራ እስከ ቮድካ፣ ሁሉም እንደቅሙ ይቀመቅማል፡፡ ወጉም ከኳስ ጨዋታ እስከ ፖለቲካ ድረስ ጦፏል፡፡ የዓለም  አቀፍ ወሬም ደርቷል፡፡ ወደ አገር ወስጥ ስንመለስ ከገበያው ውጣ ውረድ እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ድረስ የማይባል የለም፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሞቅ ያላቸው ከተከፈተው የሙዚቃ ቅኝታ ጋር ድምፃቸውን ሞርደው ያንጎራጉራሉ፡፡ የባሻዬ ልጅ ይኼንን ትዕይንት በተመስጦ እያየ፣ ‹‹ምነው ሁሉም ሰው በመረጠውና በፈለገው መንገድ ሕይወቱን እንዲመራ ቢደረግ?›› አለኝ፡፡ ምን ለማለት ፈልጎ ይሆን በማለት፣ ‹‹አልገባኝም?›› ስለው፣ ‹‹አንበርብር አባባሌ ግልጽ ነው፡፡ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር የፈለገውን የመደገፍ፣ ያልመሰለውን በሰላማዊ መንገድ የመቃወም፣ የሚፈልገውን አመለካከት የመያዝ መብቱ ቢከበርለት፤›› ሲለኝ በውስጤ ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር አልኩ፡፡ አዎን! ሰው ለሙዚቃ፣ ለቀለም፣ ለውበት ብቻ ሳይሆን ለፈለገው ነገር መብቱ ካልተከበረለት ምኑን ሰው ሆነው? መኖር እኮ መብት ነው፡፡ መኖር ደስ የሚለው ደግሞ ሰው የፈለገውን ሲያስብ፣ ሲጽፍ፣ ሲናገርና ስሜቱን ሲገልጽ ነው፡፡ ውስጡ ተወጥሮ ሲኖር ይደብራል፡፡ ያለ ዕድሜው ሲቀጭ ደግሞ ያበሳጫል፡፡ እኔ አሁን የሚሰማኝ ስሜት የሐዘን ነው፡፡ ይህ ሐዘን ደግሞ ድርብ ነው፡፡ ለእኔም ለአገሬም! አገሬ ኢትዮጵያ ሐዘንሽን ያቅልለው! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት