Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቶታል ኢትዮጵያ የፈጠራ ውድድር በትምህርት አስጠኝነት የተሳተፈው አሸናፊ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቶታል ኢትዮጵያ ባዘጋጀውና ‹‹ስታርት አፐር›› በተሰኘው የፈጠራ ውድድር ላይ በማስጠናት ዘርፍ የተሰማራው ‹‹ሜክ አዲስ ቱቶር›› የፈጠራ ሐሳብ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንዲሁም እስከ ከፍተኛ ትምህርት ለሚማሩ ግለሰቦች የማስጠናት አገልግሎት በሚሰጥ የሥራ መስክ አሸናፊ ሆነ፡፡

የተቀናጀ የማስጠናት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም የመሠረቱትና ከጎረቤት አገር ኬንያ ወደ ኡጋንዳ የኦንላይን ሥርዓት በመጠቀም ተማሪዎችን በቀጥታ በማስጠናት እስከ ስምንት ሺሕ ለተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሥራ ለመሥራት የአሜሪካ መንግሥት ፕሮግራም ከሆነው ከ‹‹ያንግ አፍሪካን ሊደርስ ኢንሼቲቭ›› ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የውድድሩ አሸናፊና የፈጠራ ባለሙያው ዶ/ር ሔኖክ ወንድይራድ የዓመቱ የቶታል ኢትዮጵያ ‹‹ስታርት አፐር›› አሸናፊ ተብለው የ350 ሺሕ ብር ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በውድድሩ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የሞባይል ስልክ ቻርጀር የሠሩት አቶ ቢንያም ተስፋዬ ሁለተኛ ሲሆኑ፣ ሦስተኛው ተወዳዳሪ አቶ ቃለዳዊት እስመዓለም በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የትራፊክ መብራት፣ የሞባይል ቻርጀር፣ የቤት ውስጥ መብራት ከ0.7 ዋት እስከ 5 ኪሎ ዋት ድረስ ኃይል የሚያመነጭ ጀነሬተርና በአንድ ጊዜ እስከ መቶ ሃያ እንቁላል ለማስፈልፈል የሚያስችል የፀሐይ ኃይልን የሚጠቀም መሣሪያ በፈጠራ ማቅረብ ችለዋል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ቢንያም 200 ሺሕ ብር እንዲሁም አቶ ቃለዳዊት የ150 ሺሕ ብር የገንዘብ ሽልማት ከቶታል ኢትዮጵያ ተረክበዋል፡፡

የቶታል ‹‹ስታርት አፐር›› ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ኢብራሂም ማማ በሰጡት ገለጻ፣ በውድድሩ ከቀረቡት ዋነኛ መስፈርቶች መካከል በፈጠራ ሥራ ላይ የተመሠረተ፣ ሁለት ዓመት ሥራ ላይ የዋለ፣ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ፣ ከአገሪቱ ልማት ጋር የሚሄድ፣ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና ጥቅሙ አኳያ ጥናት የተደረገበት እንዲሁም የሥራ ፈጠራን የሚያበረታት የሚሉት ሐሳቦች መንጸባረቅ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል፡፡

የሜክ አዲስ ቱቶር ፈጠራ ባለመብት የሆኑት ዶ/ር ሔኖክ፣ የፈጠራ ሐሳባቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በቅድመ ኮሌጆች ውስጥ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ላይ ለማስጠናት እንደሚረዳ ገልጸው፣ ከእነዚህ በተጨማሪም በሙዚቃ በኩል ሁሉንም ዕድሜ ያማከለ፣ ከቋንቋ አኳያም ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ዓረብኛ፣ አማርኛና ኦሮምኛ ለማስጠናት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል፡፡

በውድድሩ ሁለተኛ የወጡት አቶ ቢኒያም፣ በፀሐይ ኃይል አማካይነት በማደግ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ገጠር ከተሞች ነዋሪዎችን ኪስ በማይጎዳ ዋጋ ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ ቻርጅ በማድረግ መጠቀም የሚያስችል ፈጠራ ማቅረብ ችለዋል፡፡

የፀሐይ ቻርጀሩ ማንኛውንም ዓይነት ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ቻርጅ ማድረግ የሚችልና ለውኃም በቀላሉ መጋለጥ እንደሚያስችል አረጋጋጠዋል፡፡ በአንድ ጊዜም አሥር ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ቻርጅ ያደርጋል፡፡ ሌላኛው ተወዳዳሪ አቶ ቃልዳዊት ሲሆኑ፣ ሦስተኛ የወጡት በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የትራፊክ መብራት፣ የሞባይል ቻርጀር፣ የቤት ውስጥ መብራትና እንቁላል ማስፈልፈያ ጀነሬተር በመፍጠራቸው ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ አኳያ ክስተቱን አደጋውን ከመከላከልና የተለያዩ ሥራዎችን ከማቀላጠፍ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ፈጠራ ማበርከታቸውን ይናገራሉ፡፡

በፈጠራ ውድድሩ የቀረቡት ፕሮጀክቶች ለሽልማት መብቃታቸው፣ የአገሪቱ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማነቃቃትና ለማበረታታት እንዲሁም የመፍጠር ችሎታን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡

የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት፣ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ያመጡና የራሳቸውን ተቋም ማቋቋም የቻሉ ወጣቶች ወደፊት ትልቅ የፈጠራ መንገድን መክፈት ይችላሉ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ቶታል ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚያከናውነው የፈጠራ ውድድር ሥነ ሥርዓት የሚበረታታና ሌሎችም ድርጅቶች በዚህ ዓይነት መንገድ መጓዝ ቢችሉ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ፈጠራ በሰላሳ አራት የአፍሪካ አገሮች በተካሄዱ የቶታል ‹‹ስታርት አፐር›› ውድድሮች አንደኛ ከወጡ ሌሎች ፈጠራዎች ጋር የሚወዳደር ሲሆን፣ ቀሪዎች ሁለት አሸናፊዎችና የመጨረሻዎቹ አሥር ተወዳዳሪዎችም የነበሩት ተጨማሪ ሥልጠና በቶታል እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡

ውድድሩ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ በየዓመቱም በተመሳሳይ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

ቶታል ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1950 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የነዳጅና የዘይት ምርቶችን ማከፋፈል የጀመረ ሲሆን፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮም ከ‹‹ሞቢል ኦይል ኢስት አፍሪካን›› ጋር በመዋሃድ እንቅስቃሴውን ማስፋት ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው 173 አገልግሎት የሚሰጡ ጣቢያዎች፣ አራት የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም በዱከም ከተማ ሁለት ተጨማሪ የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያዎችን በላሊበላና በሽሬ እየገነባ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች