የአበባ ዘርፍ በአነስተኛ የእርሻ ማሳዎች ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ከቡና የሚገኘውን ገቢ በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችል ይነገርለታል፡፡ በአገሪቱ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ማለትም አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ኸርብስ የመሳሰሉትን ያቀፈው ዘርፍ ለእርሻ የተከለለለት ጠቅላላ የመሬት ስፋት 13 ሺሕ ሔክታር ገደማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለአበባ እርሻ ብቻ የዋለው ከ1,500 ሔክታር የማይበልጠው መሬት ነው፡፡ በዚህ መጠን እርሻው የሚከናወነው አበባ ያስገኘው ገቢ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በአንፃሩ ለቡና እርሻ የዋለው የመሬት መጠን ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ያላነሰ ነው፡፡ ከዚህ ዘርፍ ሲገኝ የቆየው ከ800 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አበባ ከቡና የላቀ ጥቅም የማስገኘት አቅም እንዳለው የሚስማሙት መንግሥትም፣ የአበባ ዘርፍ ተዋናዮችም ናቸው፡፡
አቶ ዓለም ወልደገሪማ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ተጨማሪ መሬት ቢሰጥ፣ አሁን ከሚገኘው እጥፍ ለማግኘት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ በርካታ የእርሻ ማስፋፊያ ሥራዎችን ለመሥራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች መሬት ቢያገኙ ዘርፉ አሁን እያደገበት ካለው የ17 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በላይ የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት አቅሙ፣ ሥራ የመፍጠር ዕድሉና ሌላውም ሁሉ ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም እንደሚሆን ተንትነዋል፡፡
የአበባ እርሻዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው በደርግ መንግሥት ማብቂያ ዓመታት ጀምሮ እንደነበር በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ በሆኑት በአቶ ግሩም አበበና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን የዶክትሬት ዲግሪ ዕጩ በሆኑት ፍሎሪያን ሼፈር አምና ይፋ የወጣው ጥናት ይጠቁማል፡፡ በጥናቱ መሠረት ከድኅረ ደርግ በኋላ በ2005 ዓ.ም. የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከግሉ ዘርፍ አልሚዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ለአበባ ዘርፍ ከሚጠቀሱ ምዕራፎች ውስጥ ፈር ቀዳጁ ነበር፡፡ ይህንን ተክትሎም የወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና 12 የካቢኔ አባላት የተካተቱበት ቡድን በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የለማውን የአበባ እርሻ ተዘዋውሮ ጎበኘ፡፡ የአበባ ዘርፍ የወደፊት ትንሳዔውም በዚሁ ስለመጀመሩ የተመራማሪዎቹ ጥናት ይጠቁማል፡፡
ከጅምሩ አበባ የሚያስፈልገውን የመሬት አቅርቦት፣ የብድር አገልግሎት፣ የአየር ትራንስፖርትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ እንዲያገኝ መንግሥት ቀዳሚውን ድርሻ ስለመወስዱ ባለሀብቶች የሚገልጹት ሐቅ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፋቸውም መንግሥት በሚከተለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አማካይነትና ባደረገለት ድጋፍ ከጥንስሱ ጀምሮ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ሒሳብ ውስጥ በወሳኝ ደረጃ መጠቀስ እስከቻለበት ድረስ መንግሥት አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡ ይባስ ብሎም መንግሥት የአበባውን፣ የአትክልትና ፍራፍሬውን፣ ብሎም ሌሎች በሆርቲካልቸር መስክ የሚካተቱትን እንቅስቃሴዎች የሚደግፍ ተቋም መሠረተ፡፡ ስሙንም የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ አለው፡፡ ኤጀንሲውም በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥልጠና፣ በገበያና በመሬት ማቅረብ በኩል ድጋፍ ሰጪ ሆኖ የአበባ እርሻዎችን ለማገዝ ተሰማራ፡፡
በዚህ መንገድ ከየአቅጣጫው ድጋፍ ተደርጎለት ኢትዮጵያን በዓለም የአበባ አምራች አገሮች ተርታ ማሰለፍ የቻለው ይህ ዘርፍ፣ እንደተጠበቀው ተዓምር ፈጣሪነቱ ሳይሳካለት የእንቅርፍፍ መጓዝ ከጀመረ ግን ሰነባብቷል፡፡
የአበባው ዘርፍ ራስ ምታቶች
የአበባ መስክ ብዙ ሲባልለትና ብዙ ሲጠበቅበት ቢቆይም ወደ ማቆርቆዙ እያዘገመ ይገኛል፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከአበባ የወጪ ንግድ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ150 ሺሕ ዶላር ብዙም ፈቅ እንደማይል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ግን ይህ ዘርፍ 245 ሚሊዮን ዶላር ለማስገኘት የበቃበት ወቅት ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በአበባው ወርቃማዎቹ ዓመታት ወቅት ከተገኘው ገቢ ባሻገር ለ50 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ 120 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች አበባ ያለሙ ነበር፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ከመቀዛቀዝ አልፎ ህልውናው አስጊ የሆነበት ደረጃ ላይ ስለመድረሱ የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ፡፡ በዘርፉ ባለድርሻ የሆኑ አካላት መንግሥትን ጨምሮ የተለያየ ምልከታ ያንፀባርቃሉ፡፡ አልሚዎቹ መንግሥት ዘርፉን እስከጭራሹ እንደተወው፣ ቀድሞ ይሰጠው የነበረውን ድጋፍና ክትትል እንደረሳው ይገልጻሉ፡፡ በጠቅላላው ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ሁለቱም ወገን ለአበባው ዘርፍ መጎሳቆል አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በየፊናቸው ያብራራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ለአበባ ይሰጥ የነበረው የመሬት አቅርቦት አሁን ላይ መቋረጡ፣ ለማስፋፊያ የሚሰጥ መሬት አለመኖሩና ሲኖርም ለአንዱ ካሳ እየተከፈለለት ለሌላው እስከ አራት እጥፍ ራሱ አልሚው ከባንክ እየተበደረ እንዲከፍል የሚደረግበት የሁለት ቤት አሠራር መፈጠሩን በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው፣ አንጋፋዎቹ አልሚዎች የሚገልጹት ነው፡፡ ውስጣዊ ከሚባሉት ችግሮች መካከል በመንግሥት ላይ የሚቀርበው የአልሚዎች ትችት ሚዛን ይደፋል፡፡ ‹‹ባለቤት አጥቷል፡፡ ዘርፉን የሚደግፈው ኤጀንሲም ቢሆን የድጋፍ ደብዳቤ ያውም በስንት የተንዛዛ ቢሮክራሲ ከመጻፍ በቀር እርባን ያለው ሥራ መሥራት አቁሟል፤›› ሲሉ የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲን በክፉ ያብጠለጥሉታል፡፡
አቶ አበበ ገብረሕይወት ከ38 ዓመታት የውጭ አገር ኑሮ በኋላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረበው ጥሪ መሠረት በሙያቸው ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ቀድሞውኑ በአገሪቱ አዋጭ ከሆኑ ዘርፎች ሆርቲካልቸር አንዱ በመሆኑ በዚህ መስክ ቢሰማሩ የተሻለ እንደሚሆን ስለተገለጸላቸው ከአጋራቸው ጋር ወደ ኤጀንሲው ቢያቀኑም፣ ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ኤጀንሲው ያደረሰባቸውን ውጤት አልባ መጉላላት የገለጹት በምሬት ነበር፡፡
ለኤጀንሲው በአቶ አበበና በአጋራቸው የቀረበለት ትልመ ሐሳብ በዘቢብና በገበታ ወይን ልማት ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ትልም ቢሆንም ኤጀንሲው ውድቅ አደረገው፡፡ ኮሚቴ ተቋቁሞ በድጋሚ ሐሳቡ ቢታይም ከ20 እስከ 50 ሔክታር ለሚያፈልገው ፕሮጀክት በሔክታር 250 ሺሕ ብር ካፒታል እንዲሁም 30 ሰዎች መቅጠር እንደሚጠበቅባቸው ኤጀንሲውን ጠይቆናል ያሉት አቶ አበበ፣ ነገሩ በአግባቡ እንዲታይ ቢጠይቁም መፍትሔ ሳያገኝ በእንጥልጥል መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡
ቆይቶ ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጠራው የዳያስፖራ ስብሰባ ላይ ይህንን ሐሳብ በማንሳታቸው ሚኒስቴሩ የድጋፍ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ በዚሁ መሠረትም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለፕሮጀክቱ መሬት የሚሰጥበት አግባብ መኖሩን ቢገልጹላቸውም ምንም ውጤት ሳይታይ ተጨማሪ ሦስት ወራት ጠብቀናል ይላሉ፡፡ ከዚህ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በላይ ያለ ውጤት መጉላላታቸውን የገለጹት አቶ አበበ፣ ተጨማሪ ስምንት ወራትን አክሎበት ኤጀንሲው ማድረግ የቻለው ነገር ቢኖር የቀደመውን የፕሮጀክት ሐሳብ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲቀይሩ በመጠየቅ ይህም ከሆነ በኋላ ለክልሎች የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ ብቻ ነበር፡፡
የድጋፍ ደብዳቤውን ለማግኘት አንድ ዓመት ከስምንት ወራት ቢፈጅም አማራ ክልል ግን ፕሮጀክቱን አይቶ መሬት ለመስጠት ጊዜ አልፈጀበትም ያሉት አቶ አበበ፣ በሚቀጥለው ዓመት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የፍራፍሬና አትክትል ምርቶችን ለመላክ እርሻቸው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባህር ዳር የካርጎ አገልግሎት የሚጀምር መሆኑ ከአማራ ክልል መስተንግዶና አቀባበል ጋር ተዳምሮ እንደ አቶ አበበ ያሉትን ጨምሮ ከኬንያም ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ እንዲያቀኑ ዕድል መፍጠሩ እየታየ ነው፡፡
ለአበባ ዘርፍ መዳከም ከሚጠቀሱ ችግሮች ጎላ ያለ ትችት የሚቀርብበት የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ በቢሮክራሲ ማንዛዛት የሚወገዘው በአቶ አበበ ብቻም አይደለም፡፡ መሬት ለማግኘት ጥያቄ ሲጠባበቁ መቆየታቸውን፤ ከአራት ዓመት እንግልት በኋላ ከጠየቁት 200 ሔክታር የፍራፍሬና አትልክት እርሻ መሬት ግማሹን ብቻ ካገኙ ገና ስድስት ወር መሆኑን የገለጹት የዕድገት ኢትዮጵያ አትክትልና ፍራፍሬ እርሻ ልማት ባለቤት አቶ ኃይለሚካኤል አሰፋ ናቸው፡፡
አቶ ኃይለሚካኤል በኤጀንሲው በኩል የሚታየውን ቢሮክራሲ ከመተቸት ባሻገር ድጋፍ ለመስጠት የሚያሳየውን ዳተኝነት በእጅጉ ኮንነዋል፡፡ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ሥራ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መንግሥት የሚሰጠው የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት በቢሮክራሲ መንዛዛት ሳቢያ ገና ሥራ ላይ ሳይውል ባለሀብቶችን ተጠያቂ እያደረገ እንደሚገኝ፣ ባለሀብቱ ዋስትና በማጣት ከዚህ ዘርፍ በማፈግፈግ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ባፈራው ጥሪት ሳቢያ ሰላሙንና ልማቱን የሚጠብቀው ባለሀብቱ ነው፡፡ ኤክስፖርት የማድረግ ጉጉት ያለው ባለሀብቱ ነው፡፡ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሌቦች ግን ሥርዓቱን እያበላሹ ነው፡፡ እነሱ አሸንፈውን እኛ እንንበረከካለን፡፡ አለበለዚያ ግን እኛ ታግለን እናንበረክካቸውና ወደ ጥሩ ጎዳና እንሄዳለን ብለን እየታገልን ነው፤›› በማለት የተሰማቸውን አቶ ኃይለሚካኤል እንዲህ ተንፍሰዋል፡፡
ኤጀንሲው ቢሮክራሲ አብዝቷል፣ የድጋፍ ደብዳቤ ከመጻፍ በቀር ሌላ ሚና የለውም ከሚለው ወቀሳ ባሻገር በዘርፉ ላይ ከአነጋጋሪነት አልፎ ‹‹አገሪቱን ለጉዳት ዳርጓል፤›› በማለት ጫን ያለ ነቀፋ በተደጋጋሚ ያስከተለበትን መመርያ መተግበር መጀመሩ ነበር፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም በዘንግ ይላክ የነበረውን አበባ በኪሎ ግራም እንዲሆን ማድረጉን በመቃወም የሚሰነዘር ነቀፋ ነው፡፡
አገሪቱ በዘንግ ይላክ በነበረው የአበባ መጠን ተጠቃሚ ነበረች የሚሉት አልሚዎችም ሆኑ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች መከራከሪያ አላቸው፡፡ በዘንግ የሚላከው አበባ መጠን ምን ያህል እንደነበር ሲያስረዱም አበባው የሚላክበት መደበኛ ማሸጊያ ካርቶን 13 ኪሎ ግራም አበባ የሚይዝ ሲሆን፣ ከ450 እስከ 500 የሚቆጠር የአበባ ዘንግ በአማካይ እንደሚይዝ ያብራራሉ፡፡ አቶ ተክላይ ገብረክርስቶስ የኢኮኖሚ ባለሙያና የቀድሞ የኤጀንሲው ሠራተኛ ናቸው፡፡ በእሳቸው ማብራሪያና ስሌት መሠረት የቆላማ አበባዎች በኪሎ ግራም እስከ 52 የአበባ ዘንግ ይይዛሉ፡፡ አማካዩ ሲወሰድ በኪሎ ግራም 40 የአበባ ዘንግ መላክ ያስችላሉ፡፡ ይህም ካላቸው አነስተኛ እርጥበት መጠንና ካላቸው አነስተኛ የጭንቅላት መጠን ወይም ፍካት አኳያ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ በአንፃሩ የደጋማ አበባዎች በስፋትና በእርጥበት ይዘታቸው ከቆላማዎቹ የበለጡ ስለሆኑ በኪሎ ሲሸጡ ከቆላማዎቹ ያነሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡
ይህንን ይበልጥ ለማስረዳት እንዲረዳ በዚህ አኳኋን መመልከቱ ይበጃል፡፡ ኤጀንሲው በኪሎ ግራም ተለክቶ እንዲላክ በሚያዘው መመርያ መሠረት በኪሎ ግራም እስከ 3.68 ዶላር ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ያዛል፡፡ በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር መግለጫ መሠረት ይህ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተሻሽሎ አሁን ላይ 3.86 ዶላር በኪሎ ግራም የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ዝቅተኛ ዋጋ ሁሉንም ወጪዎች የሚሸፍን ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ከዚህ ቀደም በአንድ የአበባ ዘንግ ይገኝ የነበረው የቀደመው ገቢ በአሁኑ የኪሎ አሠራር ምክንያት 0.742 ዶላር እንዲሆን ሲገደድ፣ ከ60 ከመቶ በላይ የአበባ ኤክስፖርቱን የሚሸፍነው የቆላው አካበቢ ምርት የሚያስገኘው ገቢ ይልቁን ወደ 0.1286 ዝቅ እንዲል ማድረጉን አስልተው አቶ ተክላይ አብራርተዋል፡፡
ይሁንና ከዚህ በፊት በዘንግ ሲላክ የነበረበትን አሠራር በተመለከተ የሚቀርቡ የሁለት ወገን መከራከሪያዎች ላይ ክፍተት መኖሩ አልቀረም፡፡ ኤጀንሲው በዘንግ ሲላክ እያንዳንዱን ዘንግ መንግሥት መቁጠር ስለማይችል በላኪው ሐቀኛነትና መተማመን ላይ የተመሠረተ አሠራር እንደነበረ ይሟገታል፡፡ ዘንግ ይሻል ነበር የሚሉት ወገኖችም ቢሆኑ እያንዳንዱ ዘንግ ይቆጠር ነበር ወይ ለሚለው ምላሽ የላቸውም፡፡ ይልቁንም ማሸጊያው ውስጥ የሚገባው የአበባ ዘንግ መጠን በደጋና በቆላ አካባቢ አበባዎች ባህርይ ተለይቶ ስለሚታወቅ በኪሎ ግራም ምን ያህል ዘንግ እንደሚኖር መገመት ቀላል መሆኑን ገልጸው ይከራከራሉ፡፡
የሆርቲካልቸር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለም ግን ፈጽሞ አይቀበሉትም፡፡ በመመርያው ምክንያት አገሪቱ ለጉዳት ተዳርጋለች የሚለውን ስሞታም እንዲሁ፡፡
‹‹እኔ ማወቅ የምፈልገው በዘንግ መላክ ይሻል ነበር ካሉ ማስረጃቸው ምን እንደሆነ ነው፡፡ እያንዳንዷ ካርቶን ተቆጥራ ይሠራ ቢባል አስቸጋሪ አይሆንም ወይ? ተግባራዊነቱ እንዴት ነው? መቶ ነው ያልከው ዘንግ 150 ስላለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድን ነው? በኪሎ ግን ሁለቱም ወገን ይተማመናል፡፡ የዘንግ አሠራር ወደ ግላዊ አሠራርና ወዳልተገባ ጥቅም ውስጥ ሰዎችን የሚከት ነው፡፡ በደመ ነፍስ ይሁን ከማለት ይልቅ ማስረጃውና መለኪያው ይቅረብ፡፡ የሚዛን አሠራር ለጉምሩክ፣ ለባንክ፣ ለቆጠራም ሆነ ለየትኛውም አካል የሚመች ቀላል አሠራር ብለን አስቀምጠናል፡፡››
ከኤጀንሲው ባሻገር ከ80 በመቶ በላይ የአገሪቱ ምርት መዳረሻ የሆነው የአውሮፓ ገበያ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና የዩሮ ከዶላር አኳያ እያሳየ የመጣው የመግዛት አቅም መዳከም፣ ለአበባው ዘርፍ መቀዛቀዝ በውጫዊ ምክንያትነት እንደሚጠቀስ ኤጀንሲውም አልሚዎችና ባለሙያዎችም ያምኑበታል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የገበያ መዳረሻው ከኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ገበያ ይልቅ ወደ ሌሎች ሊስፋፋ አለመቻሉም እንዲሁ አበባውን ካዳከሙ መካከል በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት እጅግ የተዳከሙት የአበባ እርሻዎችን ለመታደግ የነበረባቸውን ዕዳ በማራዘም የማገገሚያ ጊዜ በመስጠት ሲደግፍ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ 42 እርሻዎችን ለማስተዳደር ታግዶ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በልማት ባንክ እጅ የሚገኝ የአበባ እርሻ እንደሌላ ቢገለጽም፣ በአፈጻጸማቸው ዝቅተኛነት ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው 25 እርሻዎች እንዳሉ አቶ ዓለም አስታውሰዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሆርቲካልቸር በጻፈው ደብዳቤ መሠረት 16 ኩባንያዎች ኪሳራና ሐራጅ ቀጣና ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቆ ነበር፡፡ በተለይ በፓርላማው ደብዳቤ መሠረት ችግር ውስጥ ከሚገኙ 16 ኩባንያዎች ውስጥ አራት ኩባንያዎች ብቻ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው ኤክስፖርት ማድረግ መቻላቸውን፣ በተቀረው ግን 14 ኩባንያዎች አሁንም ችግር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሶ መጻፉ ይታወሳል፡፡
ከ120 ያላነሱ ኩባንያዎች በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በኸርብስ አምራችነት ሲሰማሩ ከዚህ ውስጥ ከ90 ያላነሱት አበባ እርሻዎች እንደነበሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችነት ፊታቸውን እያዞሩ እንደሚገኙ አቶ ዓለምም ሆኑ ባለሀብቶች ይናገራሉ፡፡
የአበባ ዘርፍን ጨምሮ በየወሩ የአገሪቱን የወጪ ንግድ በሚመለከት በየዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ያለውን እንቅስቃሴ የሚገመግም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ የወጪ ንግድ አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ይህ ኮሚቴ በተለይ በ2006 ዓ.ም. በኅዳር ወር 32 ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትሎቻቸው በተገኙበት በተካሄደ የኮሚቴው ስብሰባ ላይ ለአበባ ዘርፍ ይሰጥ የነበረው ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ የዘርፉ ኤክስፖርት አፈጻጸም እየተዳከመ መምጣቱን በአቶ አርከበ ዕቁባይ አስተባባሪነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የተካሄደው ስብሰባ ቃለ ጉባዔ አስፍሯል፡፡
‹‹በተለይ ዘርፉ ወደ ግብርና ሚኒስቴር እንዲዛወር ከተደረገ ወዲህ የክትትልና የድጋፍ አግባቡ በተገቢው መንገድ ባለመሰጠቱ የሥራ እንቅስቃሴው እየቀዘቀዘ እንደመጣ ግንዛቤ እንዲወሰድ፤›› በማለት ኮሚቴው የወቅቱን ግብርና ሚኒስቴር፣ የአሁኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በበኩሉ አበባን በሚመለከት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለልማቱ ከተለዩት ኮሪደሮች ለሆርቲካልቸር የሚሆን መሬት ለማግኘት እንዳልተቻለ፣ በዚህም አዳዲስ ባለሀብቶችን ለመሳብ እንዳልተቻለ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የማስፋፊያ ጥያቄን በካሳ ክፍያና በሊዝ ዋጋ ከፍተኛነት ከመጥቀስ ባሻገር፣ በክልል ከተሞች ውስጥ ለዚህ ዘርፍ የሚሆን መሬት ለመስጠት መወሰን አልቻሉም ይላል፡፡
የአበባ ዘርፍ የቱንም ያህል ቢዳከም አሁንም ድረስ ተስፋ እንዳለው ባለሀብቶቹ ያምናሉ፡፡ ተስፋው የሚለመልመው ግን መንግሥት ጉዳዬ ሲለውና በዘርፉ የሚነሱትን ችግሮች ሲፈታ፣ ቀርቦም ባለሀብቱን ሲያወያይ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችም ከሚቀርብላቸው የአፈጻጸም ሪፖርት ይልቅ ምን እንደተሠራና ምን እንደጎደለ በአካል እየወረዱ እርሻዎችን ሲጎበኙ፣ ባለሀብቱም ሲያነጋግሩ የአበባ ወርቃማ ዓመታት መልሰው እንደሚመጡ ይገልጻሉ፡፡
ብርሃኑ ፈቃደ እና አሥራት ሥዩም