አምባሳደር ሥዩም መስፍን፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር
አምባሳደር ሥዩም መስፍን ከአንጋፋ የኢሕአዴግ አመራሮች አንዱ ሲሆኑ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የቆዩባቸው ዓመታትም ለአገሪቱ ሪከርድ ነው፡፡ አምባሳደር ሥዩም አሁን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው፡፡ ኢሕአዴግን በመመሥረትም ሆነ በመምራት ጉልህ ሚና ያለውን ሕወሓትን ከመሠረቱት አባላትም አንዱ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ‹ኢንስቲትዩት ፎር አድቫንስድ ሪሰርች› የተሰኘ፣ ነፃና ገለልተኛ የጥናትና ምርምር ተቋም ይፋ ሆኗል፡፡ አምባሳደር ሥዩምም የተቋሙ የባለአደራዎች ቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ ተቋሙ በተጨማሪም እንደ አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙና አምባሳደር ተፈራ ሻውል ያሉ አንጋፋ ዲፕሎማቶችን በአመራርነት አቅፏል፡፡ ተቋሙ በአፍሪካ ቀንድ ባሉ የልማት፣ የዴሞክራሲ እንዲሁም የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የመሥራት ዓላማ አንግቧል፡፡ ይህንንም በዕውቀት ሥርጭት ሁኔታዎችና ሒደቶች ላይ ትንታኔ በማቅረብ ለማሳካት አቅዷል፡፡ አምባሳደር ሥዩም በተቋሙ ሚናና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከአሥራት ሥዩም ጋር ተነጋግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የተቋሙ ስም ‹ኢንስቲትዩት ፎር አድቫንስድ ሪሰርች› ነው፡፡ ይህን ስም ለምን መረጣችሁ? ከተለመዱ የምርምር ተቋማት ጥናቶች የእናንተን የሚለየው ምንድነው?
አምባሳደር ሥዩም፡- በነገራችን ላይ ይህን ስም ለማውጣት ክርክር አድርገናል፡፡ በዚህ ስም የሚጠሩ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሥር የሚገኙ የምርምር ተቋማት እንዳሉ ተረድተናል፡፡ እነዚህ ተቋማት በየዓመቱ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ቢያካሂዱም፣ የሆነ ሰው መጥቶ እስኪጠቀምባቸው መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን ነው ወይ መሥራት የምንፈልገው? በማለት ራሳችንን ጠይቀናል፡፡ ነገር ግን ውሳኔያችን የሆነው ጥናትና ምርምሮችን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተፈላጊ ጊዜ ማድረስ አለብን የሚል ነው፡፡ በጥናትና በምርምር ውጤቶቻችን የሁለትዮሽ ንግግር የመቆስቆስ ዓላማ አለን፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት በችግሮች ላይና በተጨባጭ መፍትሔዎች ላይ የጋራ አረዳድ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ እዚህም ላይ መቆም አንፈልግም፡፡ ስምምነት የተደረገባቸው መፍትሔዎችን ለመፈጸም በሚደረገው ተከታታይነት ያለው ሒደት ውስጥ እነዚህ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግም ዕቅዱ አለን፡፡ እነዚህ አካላት በአፈጻጸም ሒደት የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ድጋፍ በመስጠት ሚና እንደምንጫወትም እንጠብቃለን፡፡ ሊገጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ተመሥርተን ትንታኔ ወይም ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ልናደርግ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ከተለመደው የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር የእኛ ይለያል፡፡ ለዚህም ነው የተቋሙ የባለአደራዎች ቦርድ ስሙን ‹ሴንተር ፎር ዲያሎግ ሪሰርች ኤንድ ኮኦፕሬሽን› በሚል ለመቀየር የወሰነው፡፡ ይሁንና ይህ ውሳኔ ሌላ የተወሳሰበ ነገር ያመጣል፡፡ ውይይቱ መቼ ይደረጋል? ጥናትና ምርምሩስ? የሚል፡፡ ጥናቱ መደረግ ያለበት ከውይይቱ በፊት ነው ወይስ በኋላ? ወሳኙ ጥያቄ ነው፡፡ ውሳኔያችን ከጥናቱ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ስለጥናቱ ሒደት ምክክር ማድረግ አለብን የሚል ነው፡፡ መጀመርያ ችግሮችን ለመለየት ምክክር ማድረጉ ለጥናቱ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ይበልጥ በጥናትና በምርምር ለመለየት እንጥራለን፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼ በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚጋብዝ ነው፡፡ ከሰው ኃይልና ከሀብት አንፃር የሥራውን ሒደት እንዴት ነው ለመምራት ያቀዳችሁት?
አምባሳደር ሥዩም፡- ይህ ሥራ በእኛ ብቻ የሚፈጸም አይሆንም፡፡ የጥናትና የምርምራችን ዋነኛ ባለድርሻ የሆኑት መንግሥት፣ የንግድ ተቋማት፣ ሌሎች የጥናትና የምርምር ተቋማትና ሕዝቡ የራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ እነዚህ ባለድርሻዎች ጋር አብረን የምንሠራበትን አጋጣሚ ለመፍጠር እንጥራለን፡፡ የሰው ኃይልን በተመለከተ ከወጣት ተመራማሪዎች ጋር በብዛት ለመሥራት እንሞክራለን፡፡ ክህሎት ያላቸው በርካታ ወጣት ተመራማሪዎች አሉን፡፡ ተቋማችን ለእነዚህ ወጣቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያቀርባል፡፡ በአገር ውስጥ ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በውጭ ከሚገኙ ጥቂቶች ጋር የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር እየሞከርን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የተቋሙ አባላት መሆን ይችላሉ፡፡ አባላት ለወጉ ያህል መዋጮ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም፣ የተቋሙን ጥናትና ምርምሮች የመጠቀም ዕድል ይመቻችላቸዋል፡፡ ስለዚህ የንግድ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት፣ አርቲስቶችና ግለሰቦች ከእኛ ጋር እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ይህ ብዝኃነት ያለው የአባላት መሠረት በተወሰኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ላይ ጥገኛ እንዳንሆን ያደርጋል፡፡ ጥናትና ምርምራችን በገንዘብ ምንጫችን ላይ ጥገኛ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ ለኅብረተሰባችን ካላቸው ጠቀሜታ አንፃር እዚህ ግባ በማይባሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አንፈልግም፡፡ ሰፊ የአባላት መሠረት ካለን የአገሪቱን የውስጥ አቅም ለመገንባት አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምሮች የሚካሄዱበትን አሠራር ለመለወጥ እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የዚህ ተቋም የመጀመርያው ፈተና የሚሆነው ለደቡብ ሱዳን ግጭት መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ሒደት ተሳታፊ መሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በደቡብ ሱዳን ላይ ተቋማችሁ ምን ዓይነት ሥራዎችን ሠርቷል?
አምባሳደር ሥዩም፡- ተቋሙ በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ተሳታፊ መሆኑ ጠቃሚ ልምድ ለመቅሰም ረድቶታል፡፡ የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሒደት በግጭቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላትን አንድ ላይ ከማሰባሰቡ አንፃር ለየት ያለ ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን የተለያዩ ፍላጎት ያሏቸውና በመሬት ላይ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ቡድኖች በመላው ዓለም ይገኛሉ፡፡ እንኳን እነዚህ ቡድኖችና ሌሎች አገሮች የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባላት ሳይቀሩ በጉዳዩ ላይ የተከፋፈለ ፍላጎት ነው ያንፀባረቁት፡፡ እንደምታስታውሱት ኡጋንዳ በግጭቱ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ከራሳቸው ስትራቴጂካዊ ፍላጎት በመነሳት ሌሎች አገሮችና ቡድኖች ያንፀባረቁት አቋምም ግጭቱን በደቡብ ሱዳን የሚያስቀጥል ነበር፡፡ በደቡብ ሱዳን የሚገኙና በዚያች አገር ሰላም እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብቻዋን አደራዳሪ በመሆኗ የምታሳካው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ የውጭ ባለድርሻ አካላት የተከፋፈለ አቋም መያዛቸው በደቡብ ሱዳን የሚገኙትንና ሰላም የማይፈልጉትን ኃይሎች ጠቅሟል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ታንዛኒያ፣ አንጎላና ግብፅ አስታራቂ እንዲሆኑ ጠይቀው ሁሉ ነበር፡፡
መጀመርያ ማድረግ የነበረባቸው የኢጋድ አገሮችን ማሳተፍና የደቡብ ሱዳን ግጭት የአካባቢውን አገሮች ማለቂያ ወደሌለውና ለአሥር ዓመታት ሊቀጥል ወደሚል ግጭት ሊገፋቸው እንደሚችል ማሳየት ነበር፡፡ እኛ ይህን አደጋ በማሳየት የኢጋድ ዓላማ አንድነት እንዲኖረው በማድረግ በኩል ተሳክቶልናል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩሲያ፣ አውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ኅብረት ያሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ያላቸውን አካላት ወደ አንድ ጠረጴዛ ማሰባሰብም ችለናል፡፡ ለዚህም ነው ይህን የሰላም ተነሳሽነት ኢጋድ ፕላስ ሒደት ብለን የጠራነው፡፡ ይህ አማራጭ ገላጋይ ኃይል ለመፈለግ የሚደረገውን ሩጫ የሚዘጋ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የሰላም ድርድር ሒደቱ ጉልበት እያገኘ የመጣው፡፡ ለዚህም ነው በጣም አውዳሚና ጥልቀት ያለውን ግጭት በ22 ወራት ውስጥ ማስቆም የቻልነው፡፡ ማንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግጭቱ ይቆማል ብሎ አልጠበቀም፡፡ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ራሳቸው ይኼ እምነት ስለነበራቸው ሒደቱን በጣም እንድናጣድፈው ይነግሩን ነበር፡፡ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ያልተፈጸመ ቢሆንም፣ ከሞላ ጎደል አሁን በደቡብ ሱዳን ግጭቱ ቆሟል፡፡ ይኼ ልምድ በየትኛውም ቦታ ግጭትን ለማቆም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ያገኛችኋቸው ዋነኛ ትምህርቶች ምንድናቸው?
አምባሳደር ሥዩም፡- በአካባቢውና በመላው ዓለም መሰል ግጭቶች ቢከሰቱ ምን ዓይነት አቀራረብ መከተል እንዳለብን ትልቅ ትምህርት ሰጥቶን አልፏል፡፡ የመጀመርያው ዋነኛ ትምህርት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዓላማ አንድነት ኖሮት በጣም አውዳሚ ለነበረው ግጭት በፍጥነት መፍትሔ እንዲሻ ለማድረግ የተሄደበት አቀራረብ ነው፡፡ እርግጥ ነው ከአፈጻጸም አንፃር ይኼ መቶ በመቶ የተሳካ አይደለም፡፡ የሰላም ማስፈን ሒደቱና የተቋማት ግንባታ ጉዳዮች በጣም አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በወረቀት ከሚቀረው ከሰላም ድርድሩ በተቃራኒ ሰላምን መሬት ላይ ማስፈን ፈታኝና ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ እውነት ነው የሰላም ሒደቱን አንድ ወሳኝ ዕርምጃ ወደፊት የሚወስድ ስምምነት ወረቀት ላይ እንዲፈረም አድርገናል፡፡ በቅርቡ የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል፡፡ ነገር ግን ነገሮች ቀላል አልሆኑም፡፡ ይሁንና የደቡብ ሱዳን ተዋጊ ወገኖች የነበሩት አካላት አሁን በሰላም መኖር ጀምረዋል፡፡ ወደነበሩበት ግጭትም መመለስ አይፈልጉም፡፡ አሁን የተቃዋሚው ቡድን መሪዎች ጁባ ነው ያሉት፡፡ ይኼ ለሰላም ግንባታ ሒደቱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዕርምጃ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ አካላት ስምምነቱን ለመፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዝ አኳያ ያልጨረሳቸው ጉዳዮች ግን አሉ፡፡
ሌላው ከዚህ የደቡብ ሱዳን ግጭት የተማርነው ዋነኛ ትምህርት ግጭትን ለመከላከል መውሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር በደቡብ ሱዳን ግጭት ሲቀሰቀስ በአካባቢው ያሉ አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አልተገረሙም፡፡ ያልተገመተ ግጭት አልነበረም፡፡ የሆነ ወቅት ላይ የሚነሳ ግጭት ስለመኖሩ ለሁላችንም ይታይ ነበር፡፡ ከኢጋድ ሥርዓት ጀምሮ አፍሪካ ኅብረትም ሆነ ተመድ በአገሪቱ ሊነሳ ስለሚችለው ግጭት በቂ ዕውቀት ነበራቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትም አላቸው፡፡ በጁባ የነበሩት የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት በአገሪቱ እየተጠናከረ ስለመጣው ውጥረት ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀዋል፡፡ ይሁንና ማንም ግጭቱ እንዳይፈጠር አልተከላከለም፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፉ የፀጥታና የደኅንነት መዋቅር የግጭት መከላከያ ዘዴና አሠራር አልነበረውም፡፡ ግጭት እንደሚፈጠር እያወቁ ዝም ብለው ካለፉ በኋላ የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም መሞከር የማይጨበጠውን ለመያዝ እንደመሞከር ነው፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ግጭት ለማቆም ብዙ ሚሊዮኖችን አውጥቷል፡፡ ይኼ ወጪ ግጭቱን ለመከላከል ቢውል ኖሮ ረዥም መንገድ ይወስደን ነበር፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን ይህ ጥረት ግጭቱን ለማቆም በማስቻሉ ግቡን መቷል፡፡ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ከመቀጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከመፈናቀል እናድን ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ የምንማረው ወደ ግጭት የመቀየር አቅም ያላቸው ሁኔታዎችን በተመለከተ ያለን አቀራብ መቀየር እንዳለበት ነው፡፡ ግጭት ሱናሚ ስላልሆነ ቀድሞ ማስወገድ ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተጋጩ የነበሩትን አካላት ተጠያቂ ማድረግና ግጭቱን እንዲያስወግዱ ምክር ሊለግሳቸው ይችል ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ከኢጋድ አንፃርስ?
አምባሳደር ሥዩም፡- ለኢጋድና ለአባል አገሮችም ተፈጻሚ የሚሆኑ ነጥቦች ናቸው፡፡ መጀመርያ ላይ ሁኔታው በኢጋድ አባል አገሮች መካከል የዓላማ አንድነት እንዳይኖር አድርጎ ነበር፡፡ ይኼ እርግጥ ነው ለአካባቢው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እጅግ የከፋ መሆኑ የተለየ ያደርገው ነበር፡፡ ይህን ከግንዛቤ ውስጥ የከተቱት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች አጋጣሚውን በመጠቀም የሰላም ድርድሩን ለመጎተት ጥረዋል፡፡ ይኼ የመከፋፈል አዝማሚያ በአካባቢውና በአባል አገሮቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉና የልማት አጀንዳውንም መጉዳቱ አይቀርም ነበር፡፡ በጥሩ ጎኑ የሚነሳው ነገር እነዚህ አገሮች እየተከናወነ ያለው ነገርና ብጥብጡ በራሳቸው ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እየተረዱ መምጣታቸው ነው፡፡ ይህ አካሄዳቸውን በፍጥነት እንዲቀይሩና በአንድ ግብ ሥር እንዲሰባሰቡ አድርጓቸዋል፡፡ ዋናው ነጥብ ዛሬ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ነገር ነገ በአካባቢው በምንገኝ በማንኛችንም ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ከዚህ ነፃ የሚሆን አካል የለም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መማር ያለብን ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በደቡብ ሱዳን አሁንም በተወሰነ ሁኔታ ግጭቶች እየተከሰቱ እንደሆነና ከሚቀርቡት ሪፖርቶች አኳያ ተቃናቃኝ ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ሥዩም፡- አዎ ይፈጸማል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ሰፊ መሠረት የነበረውና አውዳሚ የነበረው ግጭት የሰላም ስምምነት ስለተፈረመ ብቻ ሁሉም ነገር ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈረመ ማለት ሁሉም ነገር ወደነበረበት ይመለሳል ማለት አይደለም፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን ግጭት ውሰድ፡፡ በ1990 ዓ.ም. ጀምሮ በ1992 ዓ.ም. ቆሟል፡፡ በወቅቱ ሁለቱ አገሮች የሰላም ስምምነት ፈርመዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ሁኔታ ሁሉም ማየት ይችላል፡፡ ሻዕቢያ ምን እየሠራ እንደሆነ ማንም ማየት ይችላል፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ሁለቱ አገሮች እንደ ጎረቤታሞች በትብብር ይኖራሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እዚህም እዚያም ትንኮሳዎች ሲካሄዱ ነው የሚታየው፡፡ እያወራን ያለነው ስለሁለት አገሮች ሥርዓት ያላቸው ብሔራዊ ጦሮች ነው፡፡ በአንፃሩ ስለደቡብ ሱዳን ስናነሳ እያወራን ያለነው ሥርዓትና ማዕከላዊ ዕዝ ስለሌላቸው የተከፋፈሉ ታጣቂ ኃይሎች ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የተለያዩ ግጭቶች እዚህም እዚያም መከሰታቸው አይቀርም፡፡ ነገር ግን ይኼ በማንኛውም መንገድ የሰላም ግንባታ ሒደቱን የሚያደናቅፍ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ሁኔታው ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ከነበረበት ሲነፃፀር አሁን የሚነሱት መጠነኛ ግጭቶች ተናጠላዊና ሒደቱ ሥር እስኪሰድ ድረስ ብቻ የሚከሰቱ ዓይነት ናቸው፡፡ አሁን በታላቁ የላይኛው ዓባይ ክልል የሚገኙት ሦስቱ አገሮች አንፃራዊ የሆነ ሰላም አግኝተዋል፡፡ ይሁንና እዚህም እዚያም መጠነኛ ግጭቶች አሉ፡፡ በአካባቢው በአንድ ጊዜ ከአንድ ሰዓት በላይ የቆየ አንድ ግጭት መጥቀስ አይቻልም፡፡ ምናልባት ከዚህ በፊት ግጭት ባልተከሰተባቸው እንደ ባህል አልጋዛልና ኢኳቶሪያ ክልሎች ነፃ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ያላቸውን ግጭት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች ለየትኛውም ኃይል ተጠሪ አይደሉም፡፡
ሪፖርተር፡- በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ክትትልና ግምገማ እንዲያካሂድ የተቋቋመው ኮሚሽን በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ግጭት እንዳለና ሰብዓዊ ቀውሱም ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነ በመግለጽ ሥጋቶች እንዳሉት አስታውቋል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አምባሳደር ሥዩም፡- ቡድኑ በመሬት ላይ ያለውን አፈጻጸም ሒደት እየታዘበና እየተከታተለ ሪፖርት ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ ሒደቱን ለማጓተት እየሞከሩ ስላሉ አካላት እንቅስቃሴም ሁኔታ ሪፖርት እያደረገ ነው፡፡ አገሮች፣ ተመድና የአፍሪካ ኅብረት ሒደቱን በጥንቃቄ እየመረመሩ ነው፡፡ አሁን ሒደቱን ለማደናቀፍ እየሞከሩ ባሉ አካላት ላይ ሊወሰድ ስለሚችለው ዕርምጃ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ከመርህ አኳያ በቅድሚያ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይሁና የትኞቹ ቡድኖች ማስጠንቀቂያው ይሰጣቸው? የሚለውን መለየት አለብን፡፡ በአገሪቱ ድንበር አካባቢ ተበታትነው የሚገኙት ታጣቂ ቡድኖች ናቸው አብዛኛውን ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ይሁንና ዋነኞቹ ተቀናቃኝ ወገኖች ወደሌላ ግጭት እንዳይገቡ ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡ የአማፂያን ኃይሎች መሪ ዶ/ር ሪክ ማቻር በቅርቡ ወደ ጁባ እንደሚሄዱ አስታውቀዋል፡፡ በጁባ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለን እናምናለን፡፡ ጁባ ሁለቱ ወገኖች ለሰላም ግንባታ ሒደቱ በጋራ እንዲሠሩ የተረጋጋች መሆን አለባት፡፡ የሽግግር መንግሥቱ እስኪቋቋም ድረስ አሁን ያለው መንግሥት ይህን ለመፈጸም ኃላፊነት እንደሚሰማውም እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአካባቢያዊ ደኅንነት አንፃር በርካታ ምሁራን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የበላይነት ሚና ከመጫወት ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም ይላሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች የአንዱን የሰላም ድርድር እንደመምራትዎ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?
አምባሳደር ሥዩም፡- እንዲህ ዓይነት እሳቤዎች የሚቀርቡት ከምሁራን አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ ድምዳሜዎች በመሬት ላይ በትክክል እውነት መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ስለሌለባቸው በነፃነት ይናገሯቸዋል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ተዓማኒነት ያተረፈች አገርና ተዓማኒ ሕዝብና ተዓማኒ መንግሥት ያላት መሆኗ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ያለባት ኃፊነት በራሷ ግዛት ተጀምሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በአፍሪካ በተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነችውም፡፡ ይህን የምናደርገው ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ስላለን አይደለም፡፡ ኃላፊነት ስለሚሰማን ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የምታጣው ብዙ ነገር ነው፡፡ የልማት ጥረታችን በኢትዮጵያም ሆነ በአጎራባች አገሮች ከሰላምና ደኅንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጎረቤት አገሮች ሰላም ከሌላቸው እኛም አይኖረንም፡፡ ይህ ደግሞ ልማቱንም ይጎዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያ በሕዝቦቿና በጎረቤት አገሮች ሕዝብ መካከል አርቲፊሻል ግድግዳ አትገነባም፡፡ የበላይነት ሚና የወደቀ ሞዴል ነው፡፡ አሜሪካ ይህን በመጠቀም በዓለም ላይ ሰላም ለማስፈን ሞክራ አልተሳካላትም፡፡ አውሮፓዎችም ቢሆኑ ኔቶን እንደ መሣሪያ ተጠቅመው ሞክረውት አልተሳካላቸውም፡፡ በሊቢያ ምን እንደሠሩ ማየት እንችላለን፡፡ በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሶሪያም የሆነው ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ችግር የመጣው ምዕራባውያን ራሳቸውን የዓለም ፖሊስ አድርገው በመውሰዳቸውና ለሌሎች አገሮች ዴሞክራሲና ነፃነት እናመጣለን በማለታቸው ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም ላይ ኃያል የሚባሉት አገሮች ሞክረውት ያልሠራን ሞዴል እኛ እናሠራዋለን የሚል ህልም የለንም፡፡ ኢትዮጵያ ሌላ አቀራረብ እየተከተለች ነው፡፡ ትኩረታችን በፖለቲካና በኢኮኖሚው ትብብር መፍጠር ላይ ነው፡፡