Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አስመራ አዲስ

አዲስ አስመራ አዲስ

ቀን:

መነሻ

ረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ታሪካዊ የኢትዮ ኤርትራ የዳግም ግንኙነት አብሳሪ ፀሐያዊት ዕለት፡፡ ከአዲስ አበባ አስመራ፣ ለሁለት አሠርታት ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዕውን ሊሆን፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ኤርትራዊቷ መዲና አስመራ በበረራ ቁጥር ET 312 የሚደረገው በረራ በሰዓት ምናልባትም በደቂቃዎች የሚቆጠር ጊዜ ብቻ ቀርቷል፡፡ ድብልቅልቅ ስሜት! ሐዘንና ደስታ፣ እንባና ሳቅ፣ ሁሉም ዓይነት ስሜት የሚንፀባረቅበት ልዩ ትዕይንት ይስተዋላል፡፡

በርካታ ሰው በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት በቪአይፒ ሳሎን ተሰብስቧል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከነባለቤታቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የተለያዩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እዚህም እዚያም  ይታያሉ:: ድባቡ እጅግ በጣም የተሟሟቀ ሲሆን ሁሉም ፊት ላይ የግርምት፣ የአድናቆትና የጉጉት ስሜት ይነበባል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ልክ ሰዓቱ ከረፋዱ አራት ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ ሲሆን፣ ሁሉም ሰው ቦርዲንግ ማለፊያውን እየተቀበለ ወደ ውስጥ መዝለቅ ጀመረ፡፡ አምስት ሰዓት ሲል መንገደኞች በቀጥታ ወደ ቦይንግ 787 በማምራት በህልምም በዕውንም ወዳልታሰበው ወደ አስመራ ኤርትራ ለመጓዝ ወደ አውሮፕላኑ ገቡ፡፡

ሁሉም ሰው በደስታና በሐሴት የእኔ የእኔ ሳይባባል ያገኘው መቀመጫ ላይ ተቀመጠ፣ እኔም በአውሮፕላኑ ወደ ኋላ ካሉት ወንበሮች የወንበር ቁጥር 34L ላይ ተቀመጥኩ፡፡ የበረራ አስተናጋጆች ቀያይ ጽጌረዳ አበባዎች ለሁላችንም ተሳፋሪዎች በማበርከት የእንኳን ደህና መጣችሁና የመልካም መንገድ ምኞታቸውን ገልጸውልን፣ አውሮፕላኑ ተንደርድሮ አዲስ አበባን ለቆ ተነሳ፡፡

ሁሉም ተሳፋሪ ካጠገቡ ካለው ሰው ጋር ማውራትና መጫወት ጀመረ፣ እኔም ካጠገቤ ካሉት እናትና ልጅ ጋር ጨዋታ ጀመርኩ፡፡ ‹‹የመጀመሪያ ጊዜህ ነው?›› በሚል ጥያቄያቸው ነው ወጋችንን የጀመርነው፤ ‹‹አዎን የመጀመሪያዬ ነው››  አልኳቸው፡፡  ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረብኩኝ፤  በጣም ሐዘን በተሞላበት አንደበት እኛ የዛሬ 20 ዓመት በመጨረሻው በረራ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣነው፣ ከዚያ በኋላ ከአስመራ የተነሳ አውሮፕላን የለም አሉኝ፡፡ በጣም ደስ የሚለው ግን  በመጀመሪያው  በረራ ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ መሄዱ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል ሲሉ ገለጹልኝ፡፡

የአውሮፕላኑ ካፒቴን ተሳፋሪዎችን  በአሁኗ ሰዓት ለ20 ዓመት የተዘጋውን የአየር ክልል እያለፍነው ነው ሲል ተሳፋሪው በከፍተኛ ድምፅ ጩኸትና እልልታ አውሮፕላኑን አቀለጠው፤ ወዲያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የደስታውን ሻምፓኝና ኬክ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በመቋደስ ጽዋቸውን አንስተው ተሳፋሪውን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት አበሰሩ፡፡

ከመቀመጫችን ፊት ለፊት ያለው የምሥል መመልከቻ የአስመራ አየር ማረፊያ መድረሳችንን እያሳየን ነው፡፡ ካፒቴኑም አስመራ ለማረፍ መቃረባችንን ካበሰሩን ከደቂቃዎች በኋላ አውሮፕላናችን የኤርትራን ምድር ረገጠ፣ ከፍተኛ ደስታ እልልታና ፌሽታ ሆነ፡፡ ሁሉም ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ በአውሮፕላኑ መስኮት ወደ ውጪ ማየት ጀመረ፣ እኔም ካሜራዬን በማስተካከል ከውጭ የሚጠብቀንን አቀባበል በካሜራዬ ለታሪክ ለማስቀመጥ መዘጋጀት ጀመርኩ፡፡

አውሮፕላን ውስጥ ካወራኋቸው ሦስት ሴቶች መሀል አንድዋ ከቤተሰቦቿ ጋር ከ20 ዓመት በኋላ እንደምትገናኝ የነገረችኝ ልጅ ላይ ዓይኔን ጣልኩ፡፡ የአውሮፕላኑ በሮች ተከፈቱ፣ ኤርፖርቱ ውስጥ በርካታ ሕዝብ ጽጌረዳ አበባ፣  የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በናፍቆት በተጠሙ እናትና አባት፣ እህትና ወንድም ተሞልቷል፡፡

ሕዝቡ የእኔ ቤተሰብ ሳይል የመጣውን ሰው ሁሉ እያቀፈ ይስማል፣ እንኳን ለዚህ አበቃን ይላል፡፡ ከአጠገቤ ድንገት ያቺ ከ20 ዓመት በኋላ የተመለሰችው ወጣት እናቴ ያቻትና እያለች መሮጥ ጀመረች፤ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቀፉ፡፡

የአስመራ ኤርፖርት በደስታ፣ በሐዘን፣ በናፍቶትና በተደበላለቀ ስሜት ተተራመሰ፤ እኛም ያመጣነውን ቦርሳና የመግቢያ ቪዛችንን ለመቀበል ወደ ኤርፖርት ተመለስን፤ በመሀል የተወሰነው ፓስፖርት ለጊዜው ስለጠፋ ትንሽ ለመጠበቅ ተገደን ነበር፡፡ በዚህ መሀል ከእኔ ጋር ሦስት ጋዜጠኞች አብረን እየጠበቅን የልዑኩን  ቡድን ይዞ የሚሄደው አውቶቡስ ተንቀሳቀሰ፣ በዚህ መሀል እኛም ትንሽ ተጨነቅን፤ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን፣ አንድ መልከ መልካም ወጣት ሁኔታችንን በማየት ሊረዳን ፍላጐቱን አሳየን፡፡ እኛም የተፈጠረውን ነግረነው ትብብሩን ቀጠለ፤ ከኤርፖርት ሠራተኞች ጋር በቋንቋው በመነጋገር ፓስፖርታችንን እንድናገኝ አደረጉ፡፡ ወጣቱም ስለ ትራንስፖርት እንዳታስቡ እኔ አደርሳችኋለሁ በማለት የያዝነውን ሻንጣ ወደ መኪናው ላይ በመጫን ወደምናርፍበት ሆቴል ማቅናት ጀመርን፡፡

የተባበረን መልከ መልካሙ ወጣት ጌድዮን ይባላል፡፡ ከአየር ማረፊያው እንደወጣን ስለ አስመራ ከተማ ማስተዋወቅ ጀመረ፡፡ ስለተፈጠረውም ሰላም እንደተደሰተ እያወራን ድንገት መኪናውን በማቆም ወርዶ ከመንገድ ላይ ብርቱካን ከሚሸጡ ነጋዴዎች ሁለት ኪሎ ብርቱካን ገዝቶ አንድ አንድ ልጦ ሰጠን፣ የከረን ብርቱካን በጣም ጣፋጭ እንደሆነ እየነገረን ጭምር፡፡ እኛም ብርቱካኑን ካጣጣምን በኋላ በእርግጥም አረጋግጠናል፡፡

ሆቴላችን ደርሰን ከትንሽ ዕረፍት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወዳዘጋጀው የእራት ግብዣ ለመታደም ወደ ፒኮሎ ሮማ ሆቴል አመራን፡፡ ትልቅ ድግስ ተዘጋጅቷል፣ ውጭው ዳስ ተጥሏል፣ አዳራሹም በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን ተሞልቷል፡፡ የክብር እንግዶች ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፣ የእራት ድግሱም በደማቁ ተጀምሯል፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በተዘጋጀው ቡፌ ላይ ይታያሉ፡፡ እነ ክትፎ፣ ቆጮ፣ ዓይብና የመሳሰሉት ምግቦችን እየተመገበ አስመራ ቢራና ሐበሻ ቢራ በደስታ እያጋጨ፣ ጨዋታውን ከዮድ አቢሲኒያ የባህል ቡድን ሙዚቃ ጋር አዳምሮ ከመቀመጫው ተነስቶ መጨፈር ጀምሯል፣ ይህ ትዕይንት እስከ እኩለ ሌሊት በተለያየ ሙዚቃ ደምቆና ታጅቦ ጭፈራው ደርቶ ዘለቀ፡፡ ከሙዚቃዎቹ አሁንም አንድ ዘፈን በአዕምሮዬ ያቃጭላል፣ የሒሩት በቀለን ኢትዮጵያ . . . አገራችን . . . ኤርትራ . . . አገራችን . . .፣ በማከል ታዳሚው በከፍተኛ ስሜትና በአንድ ላይ  ሲዘፍን የነበረው፡፡       

ሐሙስ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም.

ሁለተኛ ቀን በአስመራ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ገደማ ሰው ማስተናገድ የማይሰለቸው የአንድ ቀን ውድ ጓደኛችን ጌድዮን፣ ከእንግዳ ተቀባይ ክፍል ስልክ አስደውሎና ከየመኝታችን አስቀስቅሶ ከቆረስን በኋላ የቀኑን ፕሮግራም አውጥቶ የት የት መሄድ እንዳለብን በሰዓት በሰዓት ከፋፍሎ አስቀመጠው፡፡

ጉዞ ታይታ የማትጠገበው ጽዱዋና ታሪካዊቷ ሰሜናዊት ከተማ አስመራን መጎብኘት ተጀመረ፡፡ አስመራ ከሕንፃዋ አንስቶ የመንገዶቿ ቅያስ ፕላኖች፣ የፎቆቿ ምሕንድስና ውበት ከመኪና ወርዶ በእግር ለመሄድ ያጓጓል፣ በከተማው የሚታዩት መኪኖች የተሠሩበት ዓመተ ምሕረት ትንሽ ወደ ኋላ የቀሩ ቢሆንም፣ ከነውበታቸው  በደንብ የተያዙ ናቸው፡፡ በጎዳና ላይ ብዙም የትራፊክ ፍሰት ባለመኖሩ ከተማዋን እጅግ ሰላማዊ አድርጓታል፡፡

በከተማዎቹ ያሉ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች ልክ አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ያሉትን እነ ኤንሪኮ፣ ገብረትንሣዔ፣ ኦሮስኮፖ በአጠቃላይ የፒያሳን ገጽታ ያስታውሳሉ፡፡  በጌዲዮን አስጎብኝነት የአስመራን ዋና ዋና መንገዶች፣ ካቴድራሎች፣ መስጊዶችና ቤተክርስቲያኖች ከጎበኘን በኋላ ቀጣዩን የአስመራ ክፍል ከምፅዋ መልስ ብለን ከሰዓት ፀሐዩን በረድ አድርገን  ጉዞ ባፅዕ እየተባለችም ወደ ምትጠራው ምፅዋ አብራን ከነበረች የሥራ ባልደረባ ዘመዶች ጋር አመራን፡፡

ከባዱንና ጠመዝማዛውን የባፅዕን ጎዳና በቶዮታ ኮብራ መኪናችን 120 ኪሎ ሜትር ወደሚደርሰው ቁልቁለታማ መንገድ ተያያዝነው፣ ትንሽ ቆይተን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የበለስ ፍሬ ሲበሉ ከታዩበት ቦታ ደረስን፣ ሰዓት ስላልነበረን ከመኪናችን አልወረድንም፣ መኪናውን የሚያሽከረክረው ወዳጃችን ስለምፅዋ እንደዚህ እያለ ያወራን ጀመር፡፡

ከአስመራ ምፅዋ ያለው መንገድ ባለ ሦስት ዓይነት የአየር ሁኔታ የሚታይበት ነው ሲል ገለጻውን ቀጥሏል፡፡  ይህም ከፍተኛ፣ መካከለኛና በጣም ዝቅተኛ  የሆነ ቦታ ነው፡፡  የሙቀቱም መጠን ከ37 እስከ 50 ዲግሪ ሴልሸስ ድረስ  የሚደርስ  ሲሆን በ120 ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚገርም ልዩነት እንዳለው በስፋት አስረዳን፡፡

በመሀል ለዕረፍት ባህር ኃይል በመባል የሚጠራ ቦታ ላይ ”ባር ሓየት” የምትባል አንዲት አረቄ መሸጫ ቦታ ላይ አረፍ አልን፣ የአረቄ ቤቷ ባለቤት ከአስመራ ወዳጆቻችን ጋር ተቃቅፈው ሰላም ከተባባሉ በኋላ የአስመራ አረቄ የሚል አንድ ጠርሙስ  ጋበዙን፡፡ ወደ ሙቀት ስለምትሄዱ ጥሩ ነው ጠጡ አሉን፤ እኛም በስኒ መጠጣት ጀመርን፤ በጣም ለስላሳ ነው ብዙም አይረብሽም፤ ባለቤታቸው አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ይኖሩ እንደነበረና ከዚያም ተመልሰው ወደዚህ እንደመጡ ነገሩን፡፡

ከባህር ኃይል አንድ ሰዓት መንገድ ከተጓዝን በኋላ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ምፅዋ ዳህላክ ሆቴል ገብተን አረፍን፡፡ ውጩን ወጥቶ ለማየት ጨለማ ስለሆነ እራታችንን የባህር ዳርቻ ወደሚገኙ ምግብ ቤቶች አምርተን ተቋደስን፡፡ የባህሩ የውኃ ድምፅ ለእይታ እንጂ የማያስታውቅ ቦታ ላይ ሆነን  ስንጫወት አመሸን፡፡ 

ዓርብ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም.

ከጠዋቱ በ2፡00 ሰዓት ሁላችንም በሩጫ ወደ ባህር ዳርቻው ሄድን፡፡ ላላየው ሰው እጅግ በጣም ውብና ለዓይን ልዩ መስህብ የሆነ በውኃ የተከበበ ጥንታዊና አርጀት  ያለ  ቅርሳዊ ገጽታ ካላት ምፅዋ ጋር ፊት ለፊት ተያየን፡፡

የሆቴሉ ባለቤቶች በድንገት የመጡባቸውን እንግዶች ለማስተናገድ በጣም ተጨንቀው ይታያሉ፣ መልካም መስተንግዶ ለማድረግ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ሆኖም በእንግድነት የመጣው ሕዝብ ፍሪጅ በመክፈት ራሱንና ሌላውንም ማስተናገድና ማገዝ  ተያያዘ፣  እጅግ በርካታ የባህር አሳ ዓይነት የያዘ የምግብ ዝርዝር (ሜኑ)  አቀረቡልን፡፡ እኛም የባህር ዓሳዎችን አዘን መመገብ ጀመርን፣ ተስተናግደን እንደጨረስን ፊት ለፊታችን ደረቱን ወደ ምሥራቅ በሰጠው የቀይ ባህር ላይ በጀልባ ለመሳፈር ጥያቄ አቀረብን፣ እንደ ዕድል ሆኖ አንድ በቡድን ሆነው ከመጡ ሰዎች ጋር አብረን በጀልባ ቀይ ባህር ላይ ተሳፈርን፡፡

ጉዞ ወደ ዳህላክ ደሴቶች አንዷ በሆነችው ‹ግሪን አይላንድ› በጀልባ የአንድ ሰዓት ተኩል ያህል የባህር ላይ ጉዞ ካደረግን በኋላ፣ እጅግ በጣም ያማረና የአሸዋው ንጣት፣ የውኃው ንጹህነት በዓይን እስከ መጨረሻው ወደ ውስጥ የሚያሳይ በአጠቃላይ ሰው የደረሰበት የማይመስል ምንም ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ  ነገር የሌለበት ደሴት ላይ ካፕቴናችን መልህቁን ወርውሮ የሞተር ጀልባውን አቆመ፡፡ ሁሉም ሰው  እየተወረወረ ወደ ደሴቱ መሮጥ ጀመረ፤ ይዘነው የመጣነውን የለስላሳ መጠጥና የታሸጉ ምግቦች ዋና የማንችለው ቀስ ብለን ይዘን ወረድን፣ ግማሹ መዋኘት ጀመረ፤ ግማሾቻችን ከባለጀልባው ጋር ለጥላ የሚሆን ድንኳን መጣል ጀመርን፡፡ የጀልባው ባለቤት ከአምስት ሰዓት በፊት መመለስ እንዳለብን አሳወቀን፣ ምክንያቱም ከአምስት ሰዓት በኋላ ውኃው ማዕበል እንደሚኖረው አሳወቀን፡፡ ሁሉም ሰው ብዙም ባይሰማውም እሺ እሺ በማለት መዝናናት ተጀመረ፡፡ በአካፋ አሸዋው ውስጥ መቀባበር፣ መዋኘት፣ መረጫጨት ተጀመረ፣ ሰዓቱም ደረሰ፤ ባለ ጀልባውም እባካችሁ እንሂድ ማለት ጀመረ የሚሰማው ጠፋ፡፡  70፡00 ሰዓት ሲሆን ሰዉም በግድ ወደ ጀልባው መውጣት ጀመረ፤ ካፕቴናችን እንዳለውም የመልስ ጉዟችን በማዕበል የታጀበና አስፈሪ ሆነ፡፡ ሁሉም ሰው ኧረ ቀስ በል በሚሉ የሥጋት ድምጾች ያሰማ፣ የዛሬን አውጣኝ ብሎም የሚጸልይ አይጠፋም፡፡ ማዕበሉ ብዙም ባይሆን ከጀልባው ማነስ አኳያ በጣም ያስፈራል፡፡ በአጠቃላይ ጉዞው ከመዝናናት ወደ ስደት ወደሚመስል የጉዞ ድባብ ተቀየረ፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንዱ የተሳፋሪዎችን ጭንቀት ለማባረር በመሀል ይቀልዳል፣ አንዱ አንዱን ለማጽናናት ይሞክራል፤ በዚህ ሁኔታ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጨናነቅን በኋላ በሰላም ወደ ምፅዋ ወደብ ደረስን፡፡ ሁሉም ተነፈሰ፣ ካፒቴናችንን በጣም በማድነቅ እየዘለልን ወደ መሬት ወረድን፡፡

የምፅዋ ቆይታችን በዚህ አላበቃም፣ በዳህላክ ሆቴል ምሳችንን ከበላን በኋላ  ጉዞ ወደ ጉርጉሱም ደሴት ሆነ፡፡ ጉርጉሱም በጣም ሰፊ የባህር ዳርቻ ያለው ሲሆን፣ በጣም ብዙ ሰው ሲዝናና ደረስን፡፡ እኛም ከነቁምጣችን ተጠጋን፣ በአጠቃላይ አዲስ አበባ ያለሁ ነው የመሰለኝ፤ በርካታ የምናውቃቸው ሰዎች በሁለተኛውና በሦስተኛው በረራ ግልብጥ ብለው መጥተዋል፡፡ በጣም ደስ የሚል ድባብ ነው የሚታየው፣ ከእነቤተሰቡ የመጣም አለ፡፡ በአጠቃላይ ጉርጉሱም በሰው ተሞልታለች፣ መስተንግዶው ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ወደ አስመራ ጉዞ ተጀመረ፣ አስመራ አዳር ሆነ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን 2010 ዓ.ም.

ቅዳሜ ጠዋት እንደተለመደው ለቁርስ ተነሳን፣ ያው የተለመደው ውድ ወንድማችን ጌዲ የምንለው ጌዲዮን በሰዓቱ መጥቷል፡፡ የቀኑን ፕሮግራም አዘጋጅቶ አቀረበ፣ እኛም ተስማማን፣ ከፕሮግራሙ መካከል ከአራት ቀን በፊት ወንድ ልጅ የተገላገለችውን ባለቤቱን መጠየቅ የመጀመሪያው መርሐ ግብር ነው፡፡ እኛም አላንገራገርንም፣ ወደቤቱ ሄድን፤ አነስ ያለች ሁለት ክፍል ወዳላትና በጣም ንጹህ ወደ ሆነችው ቤቱ ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ›› እያልን ገባን፡፡ እሷም በፈገግታ ተቀበለችን፣ በጣም ቆንጆ ናት፣ ተቀመጥን የጌዲ ጓደኞች መጡ ገንፎ በርጎ ቀረበ፣ ተያያዝነው፣ ጨዋታ ተጀመረ፣ የጌዲ ጓደኞች በጣም ተጫዋቾች ናቸው፡፡  በመሀል ‹‹እኔ እንኳን በ12 ዓመቴ ነው ከአዲስ አበባ የመጣሁት፣ የመገናኛ ልጅ ነኝ አለ››፣ አንዱ ደግሞ  ‹‹የልደታ ልጅ ነኝ››፣ ሌላው ‹‹የፍልውኃ ነኝ›› ማለት ጀመረ፣ ‹‹በአጠቃላይ አምቼ ነው የምንባለው›› ብለው አሳቁን፡፡

ስለቆይታችን ጠየቁን፣ እኛም በጣም ደስተኞች እንደነበርን ነገርናቸው፡፡ ከእኛ መሀል አንዱ ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ፣ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ፖሊስ እንዳላየን  ነገራቸው፤ አንዱ አምቼ ቀበል አድርጐ እዚህ አገር ፖሊስ ያልሆነው ይሄ አራስ ልጅ ብቻ ነው ሲል በሳቅ ገደለን፡፡

ነገሩ ሁሉም ሰው የሠለጠነ ነው ለማለት መሰለኝ፡፡ ለማንኛውም በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ከጌዲ ቤት ወጣን፡፡ በቀጣይ የጌዲ ጓደኞች በተራቸው የአስጎብኚነቱን ተራ ተረከቡ፤ ጌዲም በአደራም አስረከበን፡፡

የቀረችውን የአስመራ ክፍል ለመዳሰስ ተስማማን፤ በአንደኛው ማርሴዲስ ግማሻችን፣ ግማሹ ቶዮታ ኮሮላ መኪና ሆነን መጎብኘት ጀመርን፡፡ የእኛ አስጎብኚ የኋላ ታሪኩን ሲያጫውተን በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተወዛዋዥ እንደነበረም ተረከልን፡፡ እናም በዘፈን የምናውቀውን አባ ሻውል የሚባለውን ቦታ ማየት አለብን ሲል፣ አባ ሻውል ማለት በብዙ መጻሕፍት ላይ የተጠቀሰ ቦታ እንደሆነና ጥበብ በብዛት ያለበት፣  ነፍሷን ይማረውና የተወዳጅዋ ፀሐይቱ ባራኪ ሰፈር እንደሆነ፣ እናም ትንሽ ዝቅተኛ ኑሮ ከሚኖሩባት የአስመራ መንደሮች አንዷ እንደሆነች ለማየት ቻልን፡፡ ወደ ውስጥም ገባን፣ ልክ እንደ አዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች የሰፈር ጐረምሶች ከበው ዋይፋይ በመጠቀም ከበው ኢንተርኔት እንደሚያስሱ በአባ ሻውል ደግሞ ከበው አንዱ ክራር ይያዝና እንደጉድ ይዘፈናል፡፡  እኛም ወደ ዘፈኑ ተጠጋን፣ ልጆቹም እንግዳ መሆናችንን አውቀው የምናውቀውን ዘፈን ይዘፍኑ ጀመር፡፡ የአብርሃም ገብረመድህንን ‹‹ንገርዋ ንገርዋ›› ማለት ጀመሩ፡፡ እኛም ግድ የለም ደስ ያላችሁን ተጫወቱ አልናቸው፡፡ እንደዛ ከሆነ ወረድ ብለን ጠላ ቤቶች አሉ እዛው አንድ ሁለት እያልን እንጨዋወት አሉን፣ እኛም በደስታ ብለን ወደ ጠላ ቤቶቹ ገባን፣ ግራና ቀኝ እንደ ድሮው አራት ኪሎ ቱሪስት አካባቢ የሚመስል ድባብ አለው፤ ሴቶቹ ፎቶ ለመነሳት ፈቃደኛ ቢሆንም ለማንሳት አልፈለግንም ጠላ ቤቱ ተገባ ዘፈኑ ቀለጠ እነ ወይዘሮ ሃና… አባ ሻውል ተዘፈኑ፣ ጠላ ተጠጣ በጣም ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍን፡፡ ለመውጣት ስንነሳ አንድ ዘፈን በአማርኛ ተጀመረ የሰሞኑ የአንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ጊዜ የማይሽረው ‹‹ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም፣ ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ››… እናንተም ሰላም ሁኑልኝ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...