Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ክርክር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ

የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ክርክር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ

ቀን:

– የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ታገደ

መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ በማውጣት (በመጻፍ) ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው፣ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ አባል አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ክርክር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሶ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ታገደ፡፡

በተከሰሱበት በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ ማውጣት (መጻፍ) ወንጀል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የ600 ሺሕ ብር ዋስትና የፈቀደላቸው ቢሆንም፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ዋስትናውን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ዓርብ ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ክርክር አድርገዋል፡፡

ለምን ይግባኝ እንዳለ ዓቃቤ ሕግ እንዲያስረዳ ዳኛ ዳኜ መላኩ፣ ዳኛ ገበየሁ ፈለቀና ዳኛ ከድር ዓልይ የተሰየሙበት የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጠይቆት እንዳስረዳው፣ ተከሳሹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 693(1)ን በመተላለፍ የሚያዙበት በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ሳይኖራቸው፣ በድምሩ አምስት ሚሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ ለስድስት ግለሰቦች ጽፈዋል፡፡ በፈጸሙት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ በእያንዳንዱ ክስ የሚጣልባቸው ቅጣት እስከ አሥር ዓመት የሚያስቀጣቸው ከመሆኑ አንፃር ዋስትና ያስከለክላቸዋል፡፡ ይኼንኑ በመጥቀስ በሥር ፍርድ ቤት ተከራክሯል፡፡ በወንጀል መዝገብ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67(ሀ) መሠረትም አሳማኝ ምክንያት ያቀረበ ቢሆንም፣ ሕጉን ባላገናዘበ መንገድ የመከራከሪያ ነጥባቸውን ውድቅ በማድረግ ተከሳሹ በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠው ብይን ተገቢና አግባብነት ያለው አይደለም ብሏል፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን ተከሳሹ ከአገር እንዳይወጡ በሥር ፍርድ ቤት እግድ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ ከሚጣልባቸው የቅጣት ሁኔታ አንፃር በሕገወጥ መንገድም ሊወጡ ስለሚችሉ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግለት ዓቃቤ ሕግ አመልክቷል፡፡

ተከሳሹ ከዚህ ቀደምም ክስ ተመሥርቶባቸው ከወጡ በኋላ የተመለሱ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ዓቃቢያነ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋና አቶ ብርሃኑ ወንድምአገኘሁ በድጋሚ አመልክተዋል፡፡

የተከሳሹ አቶ ኤርሚያስ ጠበቆች አቶ ሞላ ዘገዬና አቶ መኮንን አርጋው በሰጡት ምላሽ ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ በቅድሚያ ዓቃቤ ሕግ በደንበኛቸው ላይ ይግባኝ ያቀረበው ማክበር ያለበትን ሕግ ጥሶ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ራሱ ሕግ ማክበር ሲገባው ደንበኛቸው ከእስር እንዲለቀቁ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ ጥሶ፣ በአጋጣሚ በእጁ የገቡትን እስረኛ ለሦስት ቀናት ከሕግ ውጪ አስሮ ለምን እንዳቆያቸው እንዲጠየቅላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በደንበኛቸው ላይ ተደራራቢ ክስ እንዳቀረበባቸው በመግለጽ ወንጀሉን ከባድ እንደሚያደርገው የገለጸውን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት ጠበቆቹ፣ የዓቃቤ ሕግ ክስ ከቃል ባለፈ በማስረጃ የተረጋገጠ አለመሆኑንና ግምት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በግምት ከሆነ ‹‹ደንበኛችን በነፃ ቢለቀቁስ?›› የሚለውም ግምት መወሰድ እንዳለበት ተከራክረዋል፡፡

ዋስትና ሕገ መንግሥቱ ያከበረው ግዙፍ መብት ከመሆኑ አንፃር፣ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ነፃ ሆነው የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንዲመረምርላቸው በማስረዳት፣ ገና ለገና ሊፈረድባቸው ይችላል ብሎ በመገመት ግዙፍ መብታቸውን መቃወም ሕገ መንግሥቱን መቃወም መሆኑን በመጠቆም የዓቃቤ ሕግን ክርክር ተቃውመዋል፡፡

የገንዘቡ መጠን 4.9 ሚሊዮን ብር መሆኑ ከፍተኛ ሊያስብለው እንደማይችል የገለጹት ጠበቆቹ፣ ከኩባንያ አንፃር ሲገመት እዚህ ግባ የማይባል ትንሽ ገንዘብ መሆኑን፣ ይኼም ቢሆን ደግሞ ዋስትና ሊያስከለክል እንደማይችልና በሕግ ያልተደገፈ ክርክር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቂ ምክንያት ሳይኖር ግምት ብቻውን ዋስትና እንዳማያስከለክል የሰበር ሰሚ ችሎት የወሰነው አስገዳጅ ውሳኔ መኖሩን የገለጹት ጠበቆቹ፣ የሥር ፍርድ ቤት ሕገ መንግሥቱንና የሰበር ውሳኔን አገናዝቦ የሰጠው ውሳኔ ሊነቀፍ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

የሰበር አስገዳጅ ውሳኔን አንቀጽ ሰባት የመዝገብ ቁጥር 31734 ላይ መመልከት እንደሚቻልም ጠበቆቹ አክለዋል፡፡ የቼክ ወንጀል በባህሪው ውስብስብና ከባድ የሚባል አለመሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ ደንበኛቸው ቤት፣ ንብረትና ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ብዙ ኢንቨስትመንቶችን ያቋቋሙና አዳዲስ የሥራ መስኮችን የፈጠሩ በመሆናቸው፣ ከአገር ይወጣሉ ብሎ መከራከር ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግ አቤቱታን ውድቅ በማድረግ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን እንዲያፀናላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ባቀረበው የመቃወሚያ ክርክር ቅጣቱ እስከ አሥር ዓመት ሊደርስ ይችላል እንጂ፣ የተጠቀሰው 4.9 ሚሊዮን ብር በራሱ ዋስትና ያስከለክላል ማለት አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ ወንጀለኛ ናቸው አለማለቱንና ንፁህ ሆነው የመገመት መብት እንዳላቸው እንደሚገነዘብ ዓቃቤ ሕግ ገልጾ፣ የሥር ፍርድ ቤት ያቀረበውን ክርክር በአግባቡ ስላልመዘነለት ውሳኔውን እንደሚቃወም በድጋሚ አስረድቷል፡፡ የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች በአጋጣሚ በእጁ የገባን እስረኛ ዓቃቤ ሕግ አለቅም ማለቱን በሚመለከት ላነሱት ጥያቄ፣ ‹‹እኛ እስር ቤት የለንም፣ ማሰር የፖሊስ ሥልጣን ነው፤›› በማለት እነሱን እንደማይመለከት በመግለጽ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የራሱን ማጣሪያ ጥያቄ ለሁለቱም ወገኖች አቅርቦ፣ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...