Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጫትን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ ምሁራን ጠየቁ

ጫትን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ ምሁራን ጠየቁ

ቀን:

የጫት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የቃኙ አሥራ አምስት ጥናቶች በቀረቡበትና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) አዘጋጅነት ሚያዚያ 6 እና 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በተካሄደው ውይይት፣ ጫትን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

አምራች ገበሬውን ጨምሮ ጫት ለበርካቶች የገቢ ምንጭ ቢሆንም እያደረሰ ካለው ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር ማን ሊሸጥ ወይም ሊገዛ ይችላል? መቼና የት ቦታ ላይ መሸጥ አለበት? እንዲሁም የጫት ማስታወቂያስ ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሕግ ሊኖር እንደሚገባ ምሁራኑ ጠይቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ አቶ ደሳለኝ ራህመቶና ሌሎችም ምሁራን በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ ከጥናት አቅራቢዎች አንዱ የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ፣ ‹‹ጫት ላይ ገደብ አለመጣል የትም እንዲቃም መጋበዝ ሲሆን፣ ቁጥጥር ማድረግ ግን እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዶ/ር የራስወርቅ እንደሚሉት በአብዛኛው ስለጫት የሚንፀባረቀው ሐሳብ ፅንፍ የያዘ፣ ሙሉ በሙሉ ይታገድና ልቅ ይሁን የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁለቱም የመፍትሔ ሐሳቦች የትም የማያስኬዱ፣ ይልቁንም ጫት አምራቹና ሻጩ በምን ሁኔታ ለገበያ ማቅረብ አለበት የሚለውን በሚመለከት ሕግ ወጥቶ ቁጥጥር ማድረግ ትክክለኛው ዕርምጃ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ጫት ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ ቢሆንም፣ ትርፉ ከገንዘብ እሴት አንፃር ብቻ መታየት እንደሌለበትና በተቃራኒው አሉታዊ ተፅዕኖው ከጊዜ፣ ከዜጎች ጤና፣ ከምርታማነትና ከሌሎች በርካታ ጉዳዮች አንፃር መገምገም እንዳለትም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤት መምህርና የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ፣ የጫት ተፅዕኖ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ፡፡ ጫትን ማገድ ግን ለችግሩ መፍትሔም አዋጭ አካሄድም እንዳልሆነ በማስረዳት፣ ጫትን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዮሐንስ ገብረ ሚካኤል ያሉ አጥኚዎች ግን ውይይትና ተጨማሪ ጥናቶች የሚያስፈልጉበት እንጂ ጊዜው ሕግ የማውጣት እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡

ሕግ አስተማሪ ቢሆንም እየታየ ያለውን ቀውስ ግን በሕግ ብቻ መፍታት ስለማይታሰብ፣ ማስተማርና በጫት ሱስ ውስጥ ያሉትን ከሱስ ማውጣት የሚያስችል ሲስተም መዘርጋት በእኩል ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ምሕረት አየነው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከምሁራን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ስለጫት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ እየደረሰ ነው የተባለውን ጉዳት በሚመለከት ተጨባጭ ጥናት እስካልቀረበ ድረስ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ገልጸው ነበር፡፡ ይህን በሚመለከት የሚመሩት የምርምር ተቋም ምን እንደሚያስብ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ምሕረት፣ ‹‹ከቀረቡት ጥናቶች ለፒኤችዲ ምርምር የተሠሩ አሉ፡፡ በቀጣይም ሌሎች ጥናቶችን ሠርተን ያለውን ነገር እናሳያለን፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እሳቸው ይህን ቢሉም ጫት እያሳደረ ያለውን አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ በትክክል ማወቅ ከተፈለገ፣ ጥናት ይደረግ የሚለው ፍላጎት በመጀመሪያ መምጣት ያለበት ከመንግሥት ነው የሚል አስተያየት ያንፀባረቁም ነበሩ፡፡

በመድረኩ በተደጋጋሚ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ፖሊሲ ጥናት ክፍልም ተወካዮች ሊገኙ ይገባ እንደነበር በተሳታፊዎች ሲገለጽ ነበር፡፡ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስም ከተወካዮች ምክር ቤት በተለይም የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በመድረኩ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣንና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተው ነበር፡፡

የቀረቡ ጥናቶችን አጠቃላይ ሐሳብና የውይይት ጭብጦችን ሁሌም እንደሚያደርገው በአጭር ጊዜ አሳትሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሌሎች ተቋማትና ቤተ መጻሕፍት እንደሚያደርስ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ አስታውቋል፡፡

በ2006 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው የጫት ሲምፖዚየም በአጭር ጊዜ ማስታወቂያ መሰረዙን፣ የጫትና የሺሻ አቅርቦትና ሥርጭትን የሚገድብ ረቂቅም በፍትሕ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ እንደነበር ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...