የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በኢትዮጵያ ሊያደርጉት የነበረው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ መጪው ሐምሌ ወር መራዘሙን ምንጮች ገለጹ፡፡
የሪፖርተር ዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ በይፋ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ፕሮግራም ወደ መጪው ሐምሌ ወር እንዲራዘም ማድረጋቸውንና ይህንንም ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳውቀዋል፡፡
ዴቪድ ካሜሮን በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርጉት በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን የፀጥታና የደኅንነት ትብብር ለማጠናከር መሆኑን የዲፕሎሚቲክ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ አገሮች በፀጥታና በደኅንነት ጉዳዮች የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያስረዱት እነዚህ ምንጮች፣ በተለይ የኢትዮጵያ ደኅንነት ተቋም አመራሮች በእንግሊዝ መንግሥት ወጪ እንግሊዝ አገር ውስጥ የማስትሬት ዲግሪ በሙያ ዘርፋቸው እንደሚከታተሉ ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ጉብኝት ውስጥ ይካተታሉ ተብሎ ከተጠቀሱት የልዑኩ አባላት መካከልም፣ የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊው ይገኙበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ጉብኝታቸውን ያራዘሙበት ምክንያትን በተመለከተ ግን ምንጮች ያሉት ነገር የለም፡፡
ዴቪድ ካሜሮን ሰሞኑን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ በአገራቸው እንደገጠማቸውና ከሥልጣን እንዲለቁም ግፊት እየቀረበባቸው መሆኑን፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከሰሞኑ በፓናማ ከሚገኝ ሞሳክ ፎንሴካ ከተሰኘ የሕግ ኩባንያ አፈትልኮ የወጣውና ‹‹ፓናማ ፔፐርስ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሚስጥራዊ ሰነድ፣ ታዋቂ ፖለቲከኞችንና ግለሰቦችን ከሙስና ጋር የሚያስጠረጥራቸው ወይም ጥያቄ የሚያስነሳባቸው የቢዝነስ ድርድር መረጃዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይህ የፓናማ ፔፐርስ መረጃ የዴቪድ ካሜሮን አባት ከእንግሊዝ ውጭ የኢንቨስትመንት ኩባንያ እንዳላቸው፣ ኩባንያውም ለእንግሊዝ መንግሥት ታክስ እንደማይከፍል ከመግለጹ በተጨማሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ ሀብት ተጋሪ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡ በዚህ የተነሳም ከፍተኛ ትችት በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ገጥሟቸዋል፡፡ ከዚህ አልፎም ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠየቁ ሠልፈኞች ታይተዋል፡፡
በሌላ በኩል እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነቷ ትውጣ ወይም አትውጣ የሚለውን ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ ለመጪው ሰኔ ተቀጥሯል፡፡ ዴቪድ ካሜሮን እንግሊዝ በአውሮፓ ኅብረት መቆየት አለባት የሚል አቋማቸውን ዕውን ለማድረግ፣ የፖለቲካ ትግሉን የማሸነፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡