ወላጅ አባታቸው ሳይናዘዙላቸው እንደተናዘዙ በማስመሰል፣ ለሐሰተኛ የኑዛዜ ማረጋገጫ ሰነድ በማቅረብ 82.1 ሚሊዮን ብር ወስደዋል በመባል፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና በማታለል ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የዲአፍሪክ ሆቴል ባለቤት በነፃ ተሰናበቱ፡፡
የአባታቸው የኑዛዜ ቃል ሳይሆን እንደሆነ በመግለጽ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት በማቅረብ የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ክስ መሥርቶባቸው የነበሩት የሆቴሉ ባለቤት አቶ ብሥራት ሰይፉ ናቸው፡፡
አቶ ብሥራት ዓቃቤ ሕግ ተበዳዮች ናቸው ያላቸውን የዲአፍሪክ ሆቴል መሥራችና ባለቤት የነበሩትን የአቶ ሰይፉ ገብረ ዮሐንስ ወራሾችን አሳምነውና በሟች አባታቸው ያልተፈረመን የኑዛዜ ሰነድ ለፍርድ ቤት በማቅረብና ፍርድ ቤቱ ኑዛዜውን እንዲያፀድቅላቸው በማድረግ፣ ሌሎች ወራሾችን የሚጎዳ 82,160,000 ብር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን በክሱ አካቶ አቅርቦ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ከተገቢው የሕግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ የክስ መዝገቡን መመርመሩን ጠቁሞ፣ ተከሳሹ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ከ15 ዓመታት በፊት በ1992 ዓ.ም. ከመሆኑ አንፃር፣ በይርጋ የሚታገድ ወይም ቀሪ የሚሆን እንደሆነ መገንዘቡን በውሳኔው አስታውቋል፡፡
ተከሳሹ ለሥር ፍርድ ቤት አቀረቡት የተባለው ሐሰተኛ ኑዛዜ የተደረገው መስከረም 18 ቀን 1991 ዓ.ም. መሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ ኑዛዜ በሦስት መንገድ ሊቀርብ እንደሚችል የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጾችን ጠቅሶ አስቀምጧል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 881 መሠረት በግልጽ በሚደረግ ኑዛዜ፣ በፍ/ሐ/ብ/ሔ/ሕ/ቁ 884 መሠረት ተናዛዡ በጽሑፍ በሚያደርገው ኑዛዜና በፍ/ሐ/ብ/ሔ/ሕ/ቁ 892 በቃል የሚደረግ ኑዛዜ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በተጠቀሰው የሕግ አካሄድ መሠረት ኑዛዜ ከመደረጉ ውጪ በፍርድ ቤት ቀርቦ ሊፀድቅ ወይም የፍርድ ቤቱን ይሁንታ ሊያገኝ ስለሚችለበት ሁኔታ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ አንድም ቦታ ተደንግጎ እንደማይገኝ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አሳውቋል፡፡
በመሆኑም አቶ ሰይፉ ሳይናዘዙ በሐሰት የተዘጋጀ ነው የተባለው ኑዛዜ፣ ወደ መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሄዶ ፀድቋል መባሉን ማየት አስፈላጊ ባለመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ፍርድ ቤቱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተመሠረተው ክስ ሊያከራክር ይችላል ቢል እንኳን ጊዜውን መመልከት ግድ እንደሚለው ጠቁሞ፣ ክርክሩ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 217 (1ሐ) እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 226 (መ) መሠረት በይርጋ ቀሪ መሆኑን በመግለጽ ክርክሩ መዘጋቱን አስታውቋል፡፡