Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል አየር መንገዶች ማኅበር መሠረቱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችለናል ያሉትን ማኅበር መመሥረታቸውን አስታወቁ፡፡

ማኅበሩ የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ማኅበር የሚል መጠሪያ ተሰጥቷል፡፡ የማኅበሩ አስተባባሪና የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመዝግቧል፡፡ ሁሉም አገሮች የአየር መንገዶች ማኅበራት እንዳሉዋቸው የገለጹት ካፒቴን አበራ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገዶች እስካሁን የሚወክላቸው ማኅበር ሳያቋቁሙ መዘግየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የግል አየር መንገዶች የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው የተናገሩት ካፒቴን አበራ፣ ማኅበሩ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ በመምከር ጉዳዩን ለመንግሥት እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ የበረራ ደኅንነት ለማሻሻል ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር ተባብሮ እንደሠራ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ማኅበሩ በደኅንነት ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ትልልቅ አየር መንገዶች አስፈላጊ የኤርፖርት አገልግሎት ወደ ተሟላበት ትልልቅ ኤርፖርቶች ነው የሚበሩት፡፡ አነስተኛ የግል አየር መንገዶች ርቀት ባለው ኤርፖርት በሌለበት ሜዳ ላይ ያርፋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ለደኅንነት ሥጋት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ማኅበሩ የግል አየር መንገዶች እርስ በርስ የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያበረታታል፡፡ የደኅንነት ሥጋት በሚኖርበት ወቅትም ለመንግሥት ያሳውቃል፤›› ብለዋል፡፡

በፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም በአጠቃላይ ለጄኔራል አቪዬሽን ዕድገት ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ ጉዳዮቹ ለሚመለከቱዋቸው የመንግሥት አካላት እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ካፒቴን አበራ ማኅበሩ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ከብሔራዊ ደኅንነት መረጃ አገልግሎት ኤጀንሲ ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ የጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የበለፀገ መሆኑን የሚናገሩት ካፒቴን አበራ፣ በኢትዮጵያ ዘርፍ ትኩረት ተነፍጎት እንደቆየ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 13 ያህል የግል አየር መንገዶች ሲኖሩ፣ የሚሰጡት አገልግሎት የቻርተር በረራ ነው፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በርካታ የግል አየር መንገዶች ከቻርተር በረራ አልፈው መደበኛ የአገር ውስጥና ክልላዊ (Regional) የበረራ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ የግል አየር መንገድ የለም፡፡ ትራንስኔሽን ኤርዌይስ አንድ ሰሞን ወደ ባህር ዳር ጎንደር ከተሞች መደበኛ በረራ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ብዙም ሳይቆይ አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ብትሆንም የግል የጄት በረራ አገልግሎት የሚሰጥ አንድም ኩባንያ እንደሌለ የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ የተመዘገበ አንድም የግል ጄት አውሮፕላን አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በአንፃራዊ ሁኔታ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጄኔራል አቪዬሽን የተሻለ ዕድገት ላይ እንደነበር፣ በወቅቱ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የግል አውሮፕላኖች እንደነበሩ የገለጹት ካፒቴን አበራ፣ የደርግ ሥርዓት የነበሩትን የግል አውሮፕላኖችን በመውረሱ ጄኔራል አቪዬሽን መጥፋቱን አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ ጠንካራ የጄኔራል አቪዬሽን ኢንዱስትሪ እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘርፉ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፤›› ያሉት ካፒቴን አበራ፣ ማኅበሩ ለጄኔራል አቪዬሽን ዕድገት እንደሚታገል ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች