Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት ለመምህራን የመኖሪያ ቤትና ነፃ ትራንስፖርት ሊያቀርብ ነው

መንግሥት ለመምህራን የመኖሪያ ቤትና ነፃ ትራንስፖርት ሊያቀርብ ነው

ቀን:

– ከሐምሌ ጀምሮ የደመወዝ ማስተካከያ ታስቧል

– የፈተና ስርቆትና የዲግሪ ሽያጭ ማቆጥቆጡ ተገለጸ

መንግሥት ለመምህራን የመኖሪያ ቤት፣ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎትና የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሸጉጤ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የመምህራን ከሥራ መልቀቅ ለማስቀረትና የመምህርነት ሙያን ለማስከበር በመጀመሪያ ጥቅማ ጥቅሙን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ መታመኑን ተናግረዋል፡፡

ከታሰቡት ጥቅማ ጥቅሞች መካከል የመኖሪያ ቤት አንዱ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በገጠርም ሆነ በከተሞች ጊዜያዊ የመምህራን መኖሪያ ቤቶችን በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ማቅረብ የመጀመሪያው ተግባር እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በዘላቂነት ደግሞ በገጠርና በክልል ከተሞች መንግሥት መሬት ማቅረብ እንዳለበት፣ በገጠር ከሆነ ሰፊ መጠን ያለው መሬት ያለ ሊዝ ክፍያ ለማቅረብ መታቀዱን፣ በክልል ከተሞች ደግሞ በመነሻ የሊዝ ዋጋ መጠነኛ መሬት ለማቅረብ ዕቅድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እየገነባ በጊዜያዊነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመምህራን እንዲያከራይ፣ በዘላቂነት ደግሞ መምህራን እርስ በርስ እየተወዳደሩና እየቆጠቡ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ መታሰቡን ገልጸዋል፡፡

ትራንስፖርትን በተመለከተ ለጊዜው ነፃ የትራንስፖርት አቅርቦት በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመር እንደታቀደና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋርም ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመምህራን የትራንስፖርት ካርድ እንዲያዘጋጅና ይህንን ካርድ የያዘ ማንኛውም መምህር በማንኛውም የአንበሳ ከተማ አውቶብስ በነፃ፣ እንዲሁም ያለወረፋ የመሳፈር መብት እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህ አማራጭ ጊዜያዊ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ የትራንስፖርት አገልግሎት በመጀመሩ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ሥር ቆመው የሚገኙ በርካታ አውቶብሶችን ቢጫ ቀለም በመቀባት፣ ለተማሪዎችና ለመምህራን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የመኖሪያ ቤትና የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮችን በተመለከተ የተጠቀሱት አማራጮች ለመንግሥት ለውሳኔ መቅረባቸውንና ከሚያዝያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በኋላ ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ የደመወዝ ማስተካከያን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ኮሚቴ ጉዳዩን እያጤነ እንደሆነና ከመጪው ሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ መንግሥት በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ወጪ ያለበት በመሆኑ የመምህራንን የደመወዝ ማስተካከያ ወደ ሐምሌ ለመግፋት እንደተገደደም ጠቁመዋል፡፡

የመምህራን ጥቅማ ጥቅምን በማስከበር ሙያውም የተከበረ እንዲሆን ማድረግ የመንግሥት አቅጣጫ መሆኑን፣ ይህንንም ተሞክሮ ከሲንጋፖርና ከሩሲያ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በቅርቡ ወደ ሩሲያ ሄደን ነበር፡፡ በሩሲያ የመምህራን ከሥራ መልቀቅ ያሳሰባቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የአገሪቱን የደመወዝ ሁኔታ ካስጠኑ በኋላ፣ የመምህራን ደመወዝ በአገሪቱ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚያስገኙ የሙያ ዘርፎች አንዱ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በዚህም በአንድ ጊዜ የመምህራንን ፍልሰት ገቱ፡፡ ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችም በመምህርነት ሙያ ለመሰማራት ማመልከት ጀምረዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በትምህርት ዘርፍ ካለው የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ችግር ባለፈ ኩረጃ፣ የፈተና ስርቆትና የትምህርት ማስረጃ ሽያጭ ማቆጥቆጡንም ገልጸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ላሉ ታዳጊ ክልሎች የማበረታቻ ድጋፍ (Affirmative Action) ሲባል የመሰናዶ ትምህርትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ዝቅ እንደሚደረግ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ የድሬዳዋ ተማሪዎች ይህንን ለሶማሌ ክልል የተሰጠ ዕድል እንደሚመዘብሩ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ተማሪዎቹ ድሬዳዋ ላይ ዘጠነኛ ክፍል ይማሩና አሥረኛ ክፍልን ወደ ሽንሌ ዞን ሄደው ይማራሉ፡፡ 11ኛ ደግሞ ወደ ድሬዳዋ ይመለሳሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ 12ኛ ክፍልን ወደ ሽንሌ ዞን ተመልሰው ይማራሉ፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

በዚሁ በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳ የወረዳው ምክትል አስተዳደር ባለፈው ዓመት የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርን በማስገደድ ፈተና እንዲሰረቅ ማድረጉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ሁለቱም በሕግ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹እዚህ አዲስ አበባ ውስጥም በርካታ ደላሎች በትምህርት ተቋማት ዙሪያ ተሰማርተዋል፡፡ ሁሉንም የትምህርት ዓይነት በአንድ ሺሕ ብር፣ ለአንድ የትምህርት ዓይነት 200 ብር ከከፈላችሁ ፈተናውን እኛ እንሰጣችኋለን፤›› ብለው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል፡፡

የግል ተቋማት ሆነው ተወዳዳሪና ጥሩ ሥራ የሚሠሩ መኖራቸውን፣ ነገር ግን በአንድ ተቋም ውስጥ በትምህርት ውጤታቸው መቀጠል ያልቻሉ ተማሪዎች በተቋሙ ሲማሩ እንደቆዩ በማስመሰል፣ በምረቃው ዓመት ላይ ሦስት ሺሕ ብር እየከፈሉ ዲግሪ ሲሰጣቸው እንደተደረሰበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ልጅ ለቤተሰቡ እየተማርኩ ነው ይላል፡፡ የምረቃው ቀን ዲግሪ ገዝቶና ጋዋን ለብሶ ቤተሰብም ያስመረቀ መስሎት ይዞት ይሄዳል፡፡ ይህንን ተቋም በሕግ እንዲጠየቅ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡና ቤተሰቦች ካላገዙን መንግሥት ብቻውን የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...