በአሁኑ ጊዜ በጣም እየከፉ ከመጡ ማኅበራዊ ችግሮች መካከል አንደኛውና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዜጐችን በእጅጉ ከሚያሳስቧቸው ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ ለኑሮ ተስማሚ ካልሆኑት ጎስቋላ መንደሮች አንስቶ በተለያዩ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች በኪራይ ቤቶች መከራቸውን እያዩ ያሉ ዜጎች፣ መንግሥት በስፋት አቅዶ በተለያዩ ፕሮጀክቶች እየገነባቸው ያሉ ቤቶችን በተስፋ ቢጠብቁም ጉም የመዝገን ያህል ሆኖባቸዋል፡፡ በ1996 ዓ.ም. የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ላለፉት 12 ዓመታት ባደረገው አዝጋሚ ጉዞ 103 ሺሕ ያህል ቤቶች ተገንብተው ለዕድለኞች ተላልፈዋል፡፡ በቅርቡም 35 ሺሕ ያህል ቤቶች ዕድሉ ለደረሳቸው በመዘዋወር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣሙም፡፡
በዚህ ዓይነቱ አዝጋሚ አካሄድ የተጓዘው መንግሥት በ2005 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን ለመሙላት ጥቂት የቀራቸው ዜጎችን መዝግቦ፣ ከጥቂቱ በስተቀር ብዙኃኑ በየወሩ ለ10/90፣ ለ20/80 እና ለ40/60 ፕሮጀክቶች እየቆጠቡ ነው፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ምዝገባ ባለመካሄዱ፣ ሌላ ዙር ምዝገባ ቢጀመር ያለጥርጥር የቤት ፈላጊዎች ቁጥር አሁን እየተጠባበቁ ካሉት በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ለወር ቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች፣ ለልጆች ትምህርት ቤትና ለመሳሰሉት ወገብ የሚያጎብጡ ክፍያዎችን የሚፈጽሙ ዜጎች፣ በተስፋ ለሚጠብቁዋቸው የመኖሪያ ቤቶች የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የኑሮ ጫና ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚደገፍ ቢሆንም፣ አካሄዱ ግን ዘገምተኛ በመሆኑ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ መፍትሔውም በጥናት ላይ የተመሠረተ ሆኖ የዜጎችን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት፡፡
አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት መንግሥት ዋነኛው አካል ቢሆንም፣ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከዕቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ድረስ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መንግሥት የተቆጣጣሪነት ኃላፊነቱን እየተወጣ የግንባታውን ሙሉ ኃላፊነት በጨረታ አማካይነት ብቃት ላላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መስጠት ይኖርበታል፡፡ በመላ አገሪቱ እየተገነቡ ያሉትንና የነበሩትን መንገዶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች በሚሰጠው አሠራር መሠረት፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም በዚህ መንገድ ካልተመራ ችግሩ ቀውስ ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተለያዩ ግብዓቶችን እያቀረበ በሥራ ተቋራጮች የሚያስገነባበት አሠራር ወጪ ቆጣቢ ካለመሆኑም በላይ ለሙስና የተጋለጠ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የጥራት መጓደልም ይፈጠራል፡፡ ይህም በተግባር እየታየ ነው፡፡ በመሆኑም በብዛት ቤቶችን ገንብተው መጠቀም የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጥንቃቄ ተመርጠው ሥራ ይሰጣቸው፡፡ ለዚህም ጠቃሚ ልምዶች ይገብዩ፡፡ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡
በሌላ በኩል በተለይ በ40/60 ፕሮጀክት ሙሉ ክፍያ ፈጽመው ላለፉት ሦስት ዓመታት እየተጠባበቁ ያሉ ዜጎችን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ያላቸውን ጥሪት በሙሉ አራግፈው በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ቢጠባበቁም ጠብ የሚል ነገር በመጥፋቱ በምሬት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ገንዘቡን ቢሠሩበት ወይም ባንክ ቢያስቀምጡት ኖሮ የተሻለ ተጠቃሚነት ያገኙ እንደነበር እያሰቡ ያማርራሉ፡፡ በተቻለ መጠን የቤቶቹን ግንባታ አፋጥኖ ማስረከብ በየወሩ የሚቆጥቡ ዜጎችን ከማትጋቱም በላይ፣ በዜጎችና በመንግሥት መካከል መተማመን ለመፍጠር ይረዳል፡፡ አለበለዚያ መነሻቸው ባልታወቁና ባልተረጋገጡ መረጃዎች ምክንያት ውዥንብር እየተፈጠረ መተማመኑን ያጠፋዋል፡፡ በእርግጥም ውዥንብር እየተፈጠረ ነው፡፡ በሌላ በኩል የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ የተመዘገቡ የ20/80 ፕሮጀክት ወረፋ ጠባቂዎችም በእጅጉ ተስፋ እየቆረጡ ነው፡፡ መፍትሔ ካልተበጀ ችግሩ ከሚገመተው በላይ ይሆናል፡፡
የመኖሪያ ቤት ችግር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ወጣቶችን ጭምር የሚፈታተን የዘመኑ ተግዳሮት ነው፡፡ በወጣትነታቸው ቤተሰብ ላይ ሸክም የሆኑ ዜጎች እየበዙ ነው፡፡ ፍቅረኞች በመኖሪያ ቤት ዕጦት ምክንያት ትዳር መመሥረት ተስኗቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው ከግማሽ የሚበልጠውን ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ቆጠራ ከተደረገ ወዲህ፣ በበርካታ ሳይቶች በአንድ ቤት ላይ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤቶች እየተመለሱ ጥገኝነት እየጠየቁ ነው፡፡ በቆጠራው ሳቢያ ሕገወጥ ድርጊቶች ቢጋለጡም፣ ለዓመታት ተገናኝተው የማያውቁ አከራዮች በደላሎች አማካይነት ባደረጉት ግንኙነት ያለምንም ምክንያት በተከራዮች ላይ ውርጅብኝ ፈጽመዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አስመራሪ ድርጊት ምክንያት ተከራዮች ካላሰቡት ዕዳ ጋር ለመጋፈጥ ተገደዋል፡፡ ይህ አነስተኛ ማሳያ የወቅቱን የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አንገብጋቢነት ያመላክታል፡፡
የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁን ባለው ሁኔታ አዝጋሚ ጉዞውን የሚቀጥል ከሆነ፣ ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁትን ብቻ ሳይሆን ነገን በተስፋ የሚጠባበቁ ታዳጊዎችን ጭምር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ደግሞ ከኪራይ ብዝበዛ ጀምሮ ኑሮን መቋቋም ሲያቅታቸው ቀውስ አይፈጠርም ብሎ አለመስጋት በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ በቅርቡ ለባለ ዕድለኞች በመተላለፍ ላይ የሚገኙ ቤቶች በሚገባ ባለመጠናቀቃቸው ሳቢያ ተጨማሪ ወጪ እያስወጡ ነው፡፡ ከኑሮ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከቁጠባና ከመሳሰሉት ምን ተርፎ ነው በአግባቡ ተጠናቆ መረከብ የሚገባን ቤት ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረጉበት? ይህ ዓይነቱ አሠራር በቀጠለ መጠን መሸማቀቁም አብሮ ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል ቤቶቹ በኩባንያ ቢገነቡ ግን ከዕቅድ፣ ከዲዛይን፣ ከወጪ ቆጣቢነት፣ ከጥራት፣ ከተጠያቂነትና ከመሳሰሉት አንፃር ብርቱ ቁጥጥር ስለሚኖር ይህ ዓይነቱ አካሄድ ተመራጭ ይሆናል፡፡ ይኼም አንዱ የመፍትሔ አመላካች ነው፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት በቤቶች ልማት ፕሮጀክት አማካይነት የጀመረው ጥረት በበጎ ቢወሳም፣ ስትራቴጂውን እየፈተሸና እየከለሰ ተመራጭ መፍትሔዎችን ካልፈለገ በመኖሪያ ቤት ችግር እየተፈተኑ ያሉ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ሊደርስላቸው አይችልም፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ዜጎች በየወሩ ስለሚቆጥቡ፣ ቢያንስ የመንግሥትን ጫና እየተጋሩ መሆናቸው ሊታሰብ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣውን የኑሮ ጫና እየተጋሩ ያሉ ዜጎች፣ በአከራዮቻቸው ማናለብኝነት የሚደርስባቸው ግፍ ከመጠን እያለፈ በመምጣቱ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር አማራጮችን በቅን ልቦና ማየት የግድ ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚሰማው የመኖሪያ ቤት ችግር እሮሮ አዳማጭ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ እሮሮም ቅድሚያ ይሰጥ!