በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሦስት ዓመታት በፊት በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. የታሰሩት የቀድሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ ከእህታቸውና ከወንድማቸው ጋር ተመሥርቶባቸው የነበረውን ክስ በብቃት አለመከላከላቸው ተገልጾ፣ ዓርብ ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ 12 ክሶችን ያቀረበ ሲሆን፣ ተከሳቹም አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ ወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ወልደ ሚካኤልና እህታቸው ወ/ሮ ትርሐስ ወልደ ሚካኤል፣ እንዲሁም የቅርብ ጓደኛቸውና በንግድ ሥራ ይተዳደራሉ የተባሉት አቶ ከበደ ዱሪ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ውሳኔ እንደገለጸው፣ አቶ ወልደ ሥሳሌ ሥልጣናቸውን ያላግባብ መጠቀም፣ የገቢ ግብርን በጊዜው አሳውቆ አለመክፈል፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራትና ታክስ ሥወራ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ወንድማቸውና እህታቸውም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራት በድምሩ በሰባት ክሶች ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
አቶ ከበደ ዱሪ ግን ተመሥርቶባቸው የነበረውን በወንጀል የተገኘ ስድስት ሚሊዮን ብር መሰወር ወንጀልን በአግባቡና በተገቢ ሁኔታ ማስተባበላቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡
አቶ ወልደ ሥላሴ ጥፋተኛ የተባሉባቸው ክሶች ‹‹Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa›› በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ ኅትመት ጋር በተያያዘ ፈጽመዋቸዋል በተባሉ ድርጊቶች ነው፡፡ ይኼውም መጽሐፉን ለማሳተም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ በየነ ገብረ መስቀልን በማነጋገርና መጽሐፉ እሳቸው በሚመሩት ተቋም ስም መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ አቶ ገብረ መስቀል በሚመሩዋቸው ማተሚያ ቤቶች ትብብር እንዲታተም በማድረግ ያላግባብ በልፅገዋል የሚል መሆኑ ይታወሳል፡፡ ቦሌ፣ ብርሃንና ሰላምና አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅቶች በጋራ 3,000 መጽሐፍትን ማሳተማቸውም በክሱ ተካቶ ነበር፡፡
አቶ ወልደ ሥላሴ የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች መጽሐፉን በግዳጅ እንዲገዙ በማድረግ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ መጠቀማቸውን፣ ከመጽሐፉ ሽያጭ ካገኙት ገቢ ለመንግሥት መክፈል ይገባቸው የነበረውን የገቢ ግብር ባለመክፈላቸውና ያልከፈሉበትን ምክንያት በመከላከያ ምስክሮቻቸው ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
አቶ ወልደ ሥላሴ ነፃ የሆኑበት ክስ ለ26 ተቋማት መጽሐፉን ከሸጡና ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ፣ መጻሕፍቱን አስገድደው አስመልሰዋል ከሚለው ክስ ነው፡፡ ከሌሎች ሁለት ክሶችም ነፃ ሆነዋል፡፡
አቶ ዘርዓይ ከአቶ ወልደ ሥላሴ ውክልና ወስደው ቤታቸውን ከመኖሪያ ቤት ውጪ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል አድርገው፣ በ14 ወራት 790 ሺሕ ብር ገቢ በማግኘታቸውና ባለማሳወቃቸው ጥፋተኛ መባላቸው ተገልጿል፡፡
እህታቸው ወ/ሪት ትርሐስ ከመጽሐፉ ሽያጭ ለመንግሥት ገቢ መደረግ የሚገባው ሳይደረግ በአካውንታቸው 399 ሺሕ ብር ስለተገኘና በሌሎችም ክሶች ጥፋተኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከሁለቱም ወገኖች የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡