የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለወራት የዘለቀውን ደም አፍሳሽ ግጭት በማብረድ አንፃራዊ ሰላም ካሰፈነ በኋላ፣ ለችግሩ መንስዔ በተባሉና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ክልሉ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንቅፋት ሆነዋል ያላቸውን 829 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ከሥራ የማገድና ከደረጃ ዝቅ የማድረግ ዕርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ ቁጥራቸውን ከመግለጽ ውጪ ማንነታቸውን አላሳወቀም፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊና የካቢኔ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ዘግይቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በዚህ መሠረት ለመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥረዋል የተባሉ 708 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ 121 የወረዳ፣ የዞንና የከተማ አመራሮች ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የተወሰደው ዕርምጃ አስተዳደራዊ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሚደረግ ማጣራት የሚጠየቁ ካሉ የሕግ ሒደትን ተከትሎ ተፈጻሚ ይሆናል፤›› በማለት አቶ ፈቃደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በፌዴራል መንግሥት አነሳሽነት በሁሉም ክልሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ወደዚህ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት በክልሉ መጠነ ሰፊ ደም አፍሳሽ ግጭት በመነሳቱ፣ የመልካም አስተዳደር ሥራው ሊዘገይ መቻሉን አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ ከበረደ በኋላ በክልሉ የተለያዩ የሰላም ኮንፈረንሶች በተካሄዱበት ወቅት፣ ኅብረተሰቡ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሲያነሳ ቆይቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከኅብረተሰቡ የሰበሰባቸውን ግኝቶች በመመርመር ችግር ፈጣሪ ባላቸው አመራሮች ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ፣ ለኢንቨስትመንት የተሰጡና ታጥረው ያለግንባታ የተቀመጡ 2,897 ሔክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ሲያስገባ፣ 1,661 የሚሆኑ ሕገወጥ የተባሉ ግንባታዎችን ማፍረሱን አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡
ክልሉ የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማፋጠንና ለድርቅ የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች ጐን ለጐን፣ በተለይ በክልሉ ለተነሳው ግጭት ምክንያት ነበሩ በተባሉት ላይ መሠረታዊ ዕርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቋል፡፡
የመጀመሪያው በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ነው፡፡ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል በጋራ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በማደራጀት ወጥ የሆነ ልማት ማምጣት ያስችላል፣ ለጋራ ጥቅምም ወሳኝ ምዕራፍ ነው ያሉትን ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ላይ በነበሩበት ወቅት፣ ከተለያዩ ወገኖች የዚህ ፕሮጀክት አሉታዊ ጐን በስፋት ሲናፈስ ሰንብቷል፡፡ በመጨረሻ ክልሉ የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ግጭት በማስነሳቱ እንዲቀር ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ከዚህ ማስተር ፕላን ጐን ለጐን በተለይ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጨፌ ኦሮሚያ ያፀደቀው የከተሞች አዋጅ ከማስተር ፕላኑ ባልተናነሰ ተቃራኒ ሐሳብ ባላቸው ወገኖች አሉታዊ ጐኑ በሰፊው ተሠራጭቷል፡፡
የከተሞች አዋጅ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ቢፀድቅም፣ አዋጁ በአሉታዊ መንገድ እየተነሳ በመሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በድጋሚ ሊመረመር ይገባል በማለት አዋጁን በይደር እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህ መሠረት አዋጁ በድጋሚ ሲታይ ቆይቶ በቅርቡ ቅሬታ ጐልቶ የተነሳባቸው ሦስት አንቀጾች በመሰረዝ ጨፌው አዋጁን ማፅደቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ማስተር ፕላኑና እነዚህ ሦስት አንቀጾች በጥቅሉ የተነሳባቸው ቅሬታ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ከአዲስ አበባ ጋር ለመቀላቀል ያለመ ነው የሚል ነው፡፡
ነገር ግን አቶ ፈቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች ከፍተኛ ጥቅም እንጂ ጉዳት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ጽንፍ ይዘው የቆሙ አካላት አሉታዊ ጐኑን በስፋት በማናፈሳቸውና ክልሉ የሚናፈሰውን ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ተቀባይነት እንዳይኖረው በመሥራት በኩል ክፍተት ነበረበት ብለዋል፡፡
‹‹በዚህ ምክንያት እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች እንዲታገዱ አድርገናል፤›› በማለት አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡