Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምርያ ኃላፊ ታስረው የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መምርያ ኃላፊ ታስረው የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድጋፍና ምሥጋና በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ በተደረገ የቦምብ ውርወራ በመሳተፍ የተጠረጠሩ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር መምርያ ኃላፊ ታስረው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተወረወረ ቦምብ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ150 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ በደረሰው አካል ጉዳት ተሳትፈዋል በማለት የተጠረጠሩት የመምርያ ኃላፊው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ናቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ምስክሮች ተጠርጣሪውን እንዲመርጡ ማድረግ፣ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን መያዝ፣ በቦምብ ፍንዳታው የደረሰውን ጉዳት የሚገልጽ ዝርዝር የጉዳት መጠን የሚገልጽ ሰነድ ከሆስፒታል መሰብሰብ፣ የፈነዳውን ቦምብ የቴክኒክ ምርመራና የኤፍቢአይ የቴክኒክ ምርመራ ሰነድ መሰብሰብ፣ በክልል ያሉ ምስክሮችን ቃል መቀበልና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦች መኖራቸው ስለተረጋገጠ፣ ለባንኮች የተጻፈ ደብዳቤ መልስ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

- Advertisement -

ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ለ24 ዓመታት ያገለገሉ የሕግ አስከባሪ ናቸው፡፡ ለመታሰር ያበቃቸው የፈጸሙት ወንጀል ኖሮ ሳይሆን፣ በሐሰት በቀረበባቸው ውንጀላ ነው፡፡ አንድም እሳቸውን የሚመለከት ነገር አለመኖሩን፣ ከ20 ዓመታት በፊት የሠሩት ነገር ካለ ይጠየቁ እንጂ አንድም ያጠፉት ነገር እንደሌለ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን የተጠርጣሪውን ምላሽ በመቃወም ለችሎቱ እንደገለጸው፣ አቶ ተስፋዬ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ነበሩ፡፡ አሠራሩንና ዘዴውን የሚያውቁ በመሆናቸው ምስክሮችን ሊያባብሉበትና ሰነድም ሊያስጠፉ የሚችሉ በመሆናቸው ዋስትና መጠየቃቸውን መቃወሙን አስረድቷል፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ ናቸው የሚባለው የተጋነነ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ የመምርያ ኃላፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በግል የሚጠረጥሯቸው አንድና ሁለት ሰዎች ባደረጉት ነገር መታሰራቸውን ጠቁመው፣ እሳቸው ግን የአራት ልጆችና የቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ እንዲሁም የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን በማስረዳት ዋስትና እንዲጠበቅላቸው ችሎቱን በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን በማለፍ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

አቶ በየነ ቡላና አቶ አብዲሳ መገርሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ አቶ በየነ የፊቼ ነዋሪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ባደረገላቸው ይቅርታም በቅርቡ መፈታታቸውን አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪው የታሰሩት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የተፈጸመውን የቦምብ ፍንዳታ በስልክ ይመሩ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ በመግለጹ ነው፡፡ አቶ አብዲሳ የተጠረጠሩት ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት፣ እንዲሁም ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ለድርጊቱ ማስፈጸሚያ ሲቀበሉ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ምንም የሚውቁት ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር አመልክተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በርካታ ምርመራ ያደረገ ቢሆንም በርካታ ምርመራዎች እንደሚቀረው በማስረዳት፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዋስትና መብት ጥያቄውን በማለፍ 12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ከፍንዳታው ጋር በተገናኘ በዕለቱና በተከታታይ ቀናት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ለ34 ቀናት በእስር ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ አራት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በተሰጠው ሰባት ቀናት ጊዜ ውስጥ የሦስት ሰዎችን ምስክርነት ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ በወቅቱ ተሰማርቶ ከነበረው የሰው ኃይል ውስጥ ኃላፊነቱን ማን ይወስዳል የሚለውን መለየቱንና ለዓቃቤ ሕግም ማሳየቱን አስረድቷል፡፡ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን መያዝና የምርመራ ሒደቱን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ ለማስረከብ የሚያስችለው አሥር ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጡት አመልክቷል፡፡

ተጠርጣሪው ምክትል ኮሚሽነር ግርማ በጠበቃቸው አማካይነት ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ እየተጣራባቸው ያለው ነገር ከድርጊቱ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ የታሰሩት በሥራ አመራር ላይ ክፍተት ፈጥረዋል ተብለው መሆኑን፣ ከመርማሪ ጋር የተገናኙት በ34 ቀናት ውስጥ ከሦስት ቀናት እንደማይበልጥ፣ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ ውጤት እውነታን እንደሚያሳይና ይኼም በዋስትና ቢወጡ እንደማይቃወም የሚያሳይ አንድምታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በዕለቱ ያቀረበባቸው ነገር እንደሌለ የገለጹት የምክትል ኮሚሽነሩ ጠበቃ፣ በቀጣይ ቀናት የሚመረምራቸው ወይም በዋስ ቢለቀቁ የሚጠፉበት ምክንያት እንዳለ ባለመግለጹ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋትና መብታቸው ሊከበር እንደሚገባና ይኼ ጉዳይ የጠበቃና የፖሊስ ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ጥያቄን ሰምቶ ዝም ማለት ሳይሆን፣ የምርመራውን መዝገብ የማስቀረብና የመመልከት ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚችሉበት ምንም ምክንያት እንደሌለም አክለዋል፡፡

የምክትል ኮሚሽነር ግርማ ጠበቃ ደንበኛቸው ሊጠይቁ ይገባ የነበረው በዲሲፕሊን መሆኑን ጠቁመው፣ ወደፊት ሊቀጡ ቢችሉ እንኳን ሊቀጡ ከሚችሉበት በላይ እየተቀጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቅጣቱ ግን ከደመወዝ የማያልፍ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59(3) መሠረት ዋስትናቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል ለመርማሪ ቡድኑ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ምንድነው?›› በማለት ጠይቆት መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ ሰነድ ሊያስጠፉና የምስክሮችን ቃል ሊያስቀይሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡

የምክትል ኮሚሽነር ግርማ ጠበቃ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግና ሥርዓት የለም እንዴ? በፍርድ ቤትና በተቋማት ውስጥ እንደዚህ የወረደ ሥርዓት ያለ አይመስለኝም፡፡ ሰነድ ይቀየራል ከተባለ እዚህ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ውሳኔም ይቀየራል ማለት ነው፤›› በማለት የመርማሪ ቡድኑን መከራከሪያ ሐሳብ ውኃ የማያነሳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ምክንያት በማንኛውም መንገድ ምክንያታዊ ሊሆን እንደማይችልና በፖሊስ ፈቃድም ሊመሩ እንደማይገባ አክለዋል፡፡ ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች ‹‹እኛ እውነት ኢትዮጵያዊ ነን ወይ?›› በማለት ጥያቄ ውስጥ መግባታቸውን ለችሎት በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ኃላፊነታቸውን የተወጡና የሕዝብ አገልጋይ እንደሆኑ በማስረዳት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ በ2,100 ብር ደመወዝ በምርመራ ላይ ተፅዕኖ ያመጣሉ ማለት ቀልድ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸውም ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑም የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞ የጠየቀው አሥር ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሰምቶ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ምርመራ እንደሌለ መገንዘቡን በመግለጽ፣ አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ በአራት ቀናት ውስጥ እንዲያስረክብ የመጨረሻ ትዕዛዝ በመስጠት ለሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በአቶ አብዲሳ ቀነኔ መዝገብ የተካተቱ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ቡድኑ የሠራውን አስረድቶ ለሚቀረው ምርመራ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሰባት ቀናት ብቻ ፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ግን ቀደም ባለው ችሎት የተሰጠው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልተከበረላቸው አስረድተዋል፡፡ ለ24 ሰዓታት በጨለማ ቤት መታሰራቸውንና ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸውም አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲከበርና ተጠርጣሪዎቹ እያነሱት ያለው ጥያቄ እንዲሟላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ግን ሁሉም ነገር ሐሰት መሆኑንና እነሱ እንዳሉት እንዳልሆነ በማስረዳት ምላሽ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...