Tuesday, July 23, 2024

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በታሪክና በትውልድ ይዘከራሉ!

ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ የተሰማው መርዶ ለመላ ኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሕልፈት ሲሰማ የሚሊዮኖች ልብ ተሰብሯል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን፡፡ መላ የአገሪቱን ሕዝብ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ የከተተው የኢንጂነር ስመኘው ድንገተኛ ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት፣ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ ውጤቱ እስኪገለጽ ድረስ በእርጋታ መጠባበቅ ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ጀግና የነበሩት ደከመኝ፣ ሰለቸኝና ታከተኝ የማያውቁት ኢንጂነር ስመኘው ጥለውልን ያለፉት ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅር፣ ወደር የሌለው የሥራ ተነሳሽነትና የዓላማ ሰው መሆን ነው፡፡ ለሕይወት እጅግ ፈታኝ በሆነ የአየር ንብረት ውስጥ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከፍተኛ ሙቀት ተቋቁመው ለሰባት ዓመታት ታላቁን ብሔራዊ ፕሮጀክት ሲመሩ መቆየታቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትልቅ ተምሳሌት ነው፡፡ ታሪክና ትውልድም ሲዘክሩት ይኖራሉ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን መሆኑ ከተበሰረበት ከመጋቢት 23 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎችን በማስተባበር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ታላቅ ክብር አግኝተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ግድቡን ለመጎብኘት ወደ ሥፍራው ላቀኑ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች በሚሰጡት አንጀት አርስ ማብራሪያ የሚታወቁት ኢንጂነር ስመኘው፣ ትልቁ ህልማቸው የሚወዷት አገራቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድህነት ተላቃ ማየት ነበር፡፡ እኝህ በአገር ፍቅር ስሜት ሥራቸውን ያለመታከት ሲያከናውኑ የነበሩ ብሔራዊ ጀግና፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፊት በጊቤ አንድና ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ግንባታዎችና በተያያዥ ሥራዎች የታወቁ ነበሩ፡፡ የአገርና የሕዝብን ታሪካዊ አደራ ተሸክመው ከቤተሰባቸው ይልቅ አገር ያስቀደሙ ታላቅ ሰው፣ ባልታሰበ ሁኔታ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ያስደነግጣል፡፡ ነገር ግን አንድ ስመኘው ቢያልፉም ሚሊዮኖች በእሳቸው አርዓያነት የግድቡን ግንባታ ዳር እንደሚያደርሱት ጥርጥር አይኖርም፡፡

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከሚቆጩባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የዓባይ ግድብ ነው፡፡ በዓባይ ምክንያት ብዙዎች በብዕራቸው አንብተዋል፡፡ ብዙዎች በእንጉርጉሮ ተብሰልስለዋል፡፡ ብዙዎች በግጥሞችና በሐተታዎች ቁጭታቸውን ከትበዋል፡፡ ዓባይ በዜማና በእንጉርጉሮ የእልህ ማስተንፈሻ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እነዚህን የዘመናት መከፋቶች ወደ ታላቅ ተስፋ የቀየረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ሲጣል፣ ለመጀመርያ ጊዜ በሚያስብል ሁኔታ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠሪያ ምዕራፍ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ የተፈጠረውን መከፋፈል ገታ በማድረግ አማካይ ሥፍራ እንዲኖር ጥረት የተደረገው፣ በዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት አማካይነት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህንን የሕዝብ ታላቅና አስመኪ ብሔራዊ ፕሮጀክት ኢንጂነር ስመኘው መምራት ከጀመሩ በኋላ ደግሞ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተገኘው ውጤት ቀላል አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የውጭ ኃይሎችን ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ እዚህ መድረስ የተቻለው እሳቸውን የመሰሉ ብርቱ የሥራ መሪና አገር ወዳድ ጀግና ማግኘት በመቻሉ እንደሆነ በፍፁም መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህንንም ታሪክና ትውልድ ይዘክሩታል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ዓባይን በደፈረችበት በዚህ ታላቅ ፕሮጀክት አማካይነት 6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችላት ቢሆንም፣ ይህ ፕሮጀክት በሕዝብ ላይ የፈጠረው የባለቤትነት ስሜትና አገርን ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ዓላማው ደግሞ ትልቅ ነው፡፡ ኢንጂነር ስመኘው በአንድ ወቅት፣ ‹‹. . . ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የአብሮነት ስሜትን በእጅጉ የፈጠረ፣ የዘመናት የድህነት ቁጭትን በልማት የመቀበል ስሜትን በላቀ ሁኔታ ያመጣ፣ በአደራ የተሰጡንን የቤት ሥራዎቻችንን በብቃት ሠርተን እንድንወጣ የትልቅነት መንፈስና አስተሳሰብ ያመጣልንና ያጎናፀፈን ብሔራዊ መኩሪያ ፕሮጀክታችን ነው፤›› በማለት እጅግ ማራኪ አስተያየት የሰጡ ባለ ራዕይ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ይህንን ታላቅ ብሔራዊ ፕሮጀክት ከግብ ለማድረስ ደፋ ቀና ሲሉ በድንገት መቀጨታቸው ልብ የሚሰብር ቢሆንም፣ የእሳቸውን አደራ ተረክቦ በታላቅ ወኔ ግድቡን ማጠናቀቅ የእዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ በታሪክና በመጪው ትውልድም ያስጠይቃል፡፡

ኢንጂነር ስመኘውን ስንዘክር ማስታወስ ያለብን ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅር ምን ያህል እንደሚያስከብር ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት በረሃ ለበረሃ እያንከራተተ መስዋዕትነት ከማስከፈሉም በተጨማሪ፣ ቤተሰብንና ከአብራክ የወጡ ልጆችን ጭምር የመስዋዕትነቱ ተካፋይ ያደርጋል፡፡ የእኝህን ታላቅ ሰው የዓመታት ሕይወት ከራሱ ሕይወት ጋር የሚያነፃፅር ማንም ቅን ዜጋ ይህንን ታላቅ መስዋዕትነት ይረዳዋል፡፡ ለአገር ክብርና ዝና ደንታ የሌላቸው ወፍ ዘራሾች በየቦታው እንደ እንጉዳይ በፈሉበት በዚህ ዘመን፣ ለአገሩና ለወገኑ እንቅልፍ አጥቶ የሚሠራ የተከበረ ጀግና ማጣት ሕመሙ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን የእንዲህ ዓይነቱ ወደር የሌለው ጀግና ተምሳሌትነት ብዙ ጀግኖች ስለሚፈጥር ያፅናናል፡፡ የአገር ተስፋና አለኝታ የነበሩ የቁርጥ ቀን ልጅ በአስደንጋጭ ሁኔታ በድንገት ሲያልፉ አገር ማቅ ብትለብስም፣ አርዓያነታቸው ግን ለዘለዓለም እንደ አብሪ ኮከብ ሲያንፀባርቅ ይኖራል፡፡ የሥራ ባህል እንደነገሩ በሆነበት አገር ውስጥ ሠርቶ የሚያሠራ ግንባር ቀደም ጀግና ሰማዕት ቢሆንም፣ እሱ ጥሎት የሚያልፈው አሻራ ሚሊዮኖችን በቁጭት በማንቀሳቀስ ዓላማውን ለማሳካት ትልቅ መነሳሻ ይሆናል፡፡  ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ እንዳልሆነ በተግባር ያሳዩት ብሔራዊ የልማት ጀግና የሆኑት ኢንጂነር ስመኘው ከሚፈለግባቸው በላይ ታሪካዊ ግዴታቸውን ተወጥተው ሲያልፉ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ይህንን አንፀባራቂ ታሪክ ለማስቀጠል ተግተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት የሚፈለገውም ይኼ ነው፡፡

አገር መውደድ ማለት ያለ ስስት ራስን መስዋዕት ማድረግ መሆኑን ከኢንጂነር ስመኘው ታላቅ ትምህርት ተወስዷል፡፡ በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከኤክስፐርትነት እስከ ዋና መሐንዲስነትና ሥራ አስኪያጅነት የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪክ የወርቅ ቀለም ይጻፋል፡፡ ይህ አንፀባራቂ ተምሳሌትነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥም ታትሟል፡፡ እሳቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት የግድቡን ግንባታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹. . . ተቋማዊና አገራዊ አስተሳሰብን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሄድ የላቀ የአንድነት ስሜትን በማጠንከር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በጋራ እያረጋገጥን ሁሌም በሁሉም መስክ የተሻለ ነገር ለማየት በርትተን፣ ተሰባስበንና ተጋግዘን መሥራት ችለናል፡፡ ማስቀጠልና ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ደግሞ የዚህ ተውልድ ትልቅ አደራ ነው፤›› ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ሰባተኛ ዓመት ዘክረው ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን በሙሉ በየትኛውም ዘመንና አገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ አገርን በጋራ ለማሳደግና የመላውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻልና ለማበልፀግ ቆርጠው እንዲነሱ መተኪያ የሌለው ኃይል መሆኑንም ገልጸው ነበር፡፡ እሳቸው አደራቸውን እጅግ በጣም አኩሪ በሆነ የሥራ አፈጻጸም አጠናቀው ተለይተውናል፡፡ አደራውንም በሕይወት እያሉ ነግረውናል፡፡ ቀሪው ታሪክ የባለ አደራው ትውልድ ይሆናል፡፡ እሳቸውን ግን በታሪክና በትውልድ ሲዘከሩ ይኖራሉ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...