Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንጂነር ስመኘው በቀለ 1958 - 2010

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ 1958 – 2010

ቀን:

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲነሳ የእሳቸው ስም፣ የእሳቸው ስም ሲነሳም የህዳሴው ግድብ በመነሳቱ የሚታወቁት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር)፣ ሐሙስ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ በመስቀል አደባባይ ሞተው መገኘታቸው አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡

በመሀል አዲስ አበባ የሕዝብ መናኸሪያ በሆነው መስቀል አደባባይ ከጠዋቱ ከንጋቱ 2፡20 ሰዓት (መንግሥት እንደገለጸው) በቪኤይት መኪናቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር)፣ በግራ ጆሯቸው ሥር በኮልት ሽጉጥ ጥይት መመታታቸው ተነግሯል፡፡ በተቀመጡበት የሾፌር መቀመጫ ወንበር ላይ ያደረጉት ባርኔጣ እንኳን ሳይወልቅ፣ ወደ ቀኝ ዘንበል ብለውና ሽጉጡ ደግሞ በቀኝ በኩል ባለው ወንበር ላይ መገኘቱ አሟሟታቸውን ግራ የሚያጋባ አድርጎታል፡፡

የእሳቸውን አሟሟት ግራ እንዲያጋባ ያደረገው፣ ሞተው የተገኙበት መኪናቸው በሮች ተቆልፈው መገኘታቸው ነው፡፡ ሞተው በተገኙበት ዕለት በመስቀል አደባባይ የተገኘው ሕዝብና መሞታቸው በድረ ገጾች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተሠራጨ በኋላ የሰማው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለአሟሟታቸው የተለያዩ ግምቶችን እንዲሰጡ ተገደዋል፡፡ አንዳንዶች፣ ‹‹ራሱን በራሱ አጥፍቶ ነው፤›› ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ፣ ‹‹ራሱን ለማጥፋት መስቀል አደባባይ ድረስ ምን ያስመጣዋል? ሆን ብለው ገድለው አምጥተው ጥለውት ሄደው ነው፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡ ‹‹በሌላ አካል ተገድሎ ነው፤›› የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች በምክንያትነት የሚያቀርቡት፣ ‹‹ራሱን ከገደለ ብዙ ደም ሊፈሰው ይችላል፡፡ በቀኝ እጁ ተጠማዞ በግራ ጆሮው ሥር ከተኮሰ ደግሞ የመታው ጥይት ወደ ውጭ ሊወጣ ይችል ነበር፡፡ ሽጉጡም ወይ ወደ ኋላ ወይም ወንበሩ ሥር ተወርውሮ ሊወድቅ ይችል ነበር፤›› የሚል ነው፡፡

የእሳቸውን አሟሟትን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ዝርዝር እውነታውን ለማወቅ ሁሉም የፎረንሲክና ሌሎች የምርመራ ሒደቶች በትብብር እየተሠሩ መሆናቸውን፣ ሕይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመትተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀኝ እጃቸው በኩል ኮልት ሽጉጥ እንደነበር ለመታዘብ መቻላቸውንና በአካባቢ የነበሩና ማስረጃ ይሰጣሉ የተባሉ ግለሰቦች ተይዘው እየተረመሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በስንት ጥይት እንደተመቱና ሌሎች ዝርዝር ማስረጃዎችን በማካተት ፖሊስ ግዴታውንና ኃላፊነቱን ተወጥቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ  1958 - 2010

 

ስመኘው (ኢንጂነር) ሞተው በተገኙበት ዕለት ጠዋት 1፡30 ሰዓት አካባቢ ቢሮ ገብተው መውጣታቸውንና ከጸሐፊያቸውም ጋር በስልክ መነጋገራቸውን፣ እንዲሁም ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሥራ እንቅስቃሴ ለመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሦስት ሰዓት ላይ ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ የእሳቸው ቢሮዎች መታሸጋቸውንና ሌሎች ከእሳቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ እንደሚጠበቁም አክለዋል፡፡

እሳቸው መቼና ለምን ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ እንደቻሉ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ የታላቁ ህዳሴ ግንባታ መዘግየትንና የሚፈጥንበትን ሁኔታ በሚመለከት ከሥራ ተቋራጮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥልቅና ግልጽ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ የግድቡ ሲቪል ሥራ በጥሩ ሁኔታ የተሠራ ቢሆንም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታው ዘግይቷል፡፡

በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ውሳኔዎች በመተላለፋቸው፣ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር ውይይት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አስደንጋጭ የሆነውንና ጥልቅ ሐዘን ውስጥ የከተተውን የዋና ሥራ አስኪያጁን ሞት ሲሰሙ፣ እጅግ ማዘናቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ባለበት በረሃ ውስጥ በሚገኘው ጉባ ወረዳ የሚገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብን፣ ከመሠረቱ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት 65 በመቶ ድረስ በመቆጣጠርና በመምራት ላይ እያሉ፣ በ52 ዓመታቸው በአሰቃቂና አስደንጋጭ ሁኔታ ሕይወታቸው ያለፈው ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር)፣ የተወለዱት በአማራ ክልል በጎንደር አካባቢ ነው፡፡ መስከረም 3 ቀን 1958 ዓ.ም. ጎንደር ቀጣይ ወረዳ ማክሰኝት ቀበሌ ውስጥ የተወለዱት ስመኘው (ኢንጂነር)፣ የመጀመርያና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቅዳሜ ገበያና እንፍራንስ ትምህርት ቤቶች ተምረው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወልዲያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡

ለወላጆቻቸው ብቸኛ ልጅ የሆኑት ስመኘው (ኢንጂነር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1989 ዓ.ም. በምሕንድስና የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ፣ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማሠልጠኛ ተቋም ከ1990 ዓ.ም. እስከ 1991 ዓ.ም. ድረስ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1992 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት በኮርፖሬሽኑ የኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ ከሠሩ በኋላ፣ ከ1993 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ በተገነባው ግልገል ጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ አስተባባሪ መሐንዲስ ሆነው መሥራታቸውን፣ ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ የተገነባው ግልገል ጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ ሥራ አስኪያጅ ሆነው አሠርተዋል፡፡ ከመጋቢት 2003 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያ ሕዝብ ምልክት ይሆናል በተባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እያሠሩ ነበር፡፡

ድንገት ሳይታሰብ ሞተው የተገኙት ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር)፣ ባለትዳርና የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም እሑድ ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙበት ለአንድ የልማት አርበኛ ጀግና በሚደረግ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚፈጸም፣ ብሔራዊ የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...