Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየቀድሞው ሠራዊት አባላትም የይቅርታው ተቋዳሽ ቢደረጉ

የቀድሞው ሠራዊት አባላትም የይቅርታው ተቋዳሽ ቢደረጉ

ቀን:

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በ3,000 ዘመናት ስትኖር በየጊዜያቱ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በሀቀኛ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች እየተመራች የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ችግሮችን በማስወገድና በድል እየተረማመደች አሁን ለደረስንበት ጊዜ ደርሳለች፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ የለውጥ ማዕከል፣ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን በመሸነፍ ሳይሆን በማሸነፍ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ማዕበሉን ያናወጠው በእርስዎ አንደበት እንደተገለጸው የይቅርታ፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመደመር ውጤት ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ ለዚህም ቋሚ ምስክሩ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያን በመስቀል አደባባይ ያሳዩት ሰላማዊ የድጋፍ ሠልፍ ለዘመናት የማይፋቅና የማይረሳ ቋሚ ምስክር ነው፡፡

ይሁንና በዚህ ዕለት በጠራራ ፀሐይ የሰላሙን ዜማ ለማዜም የአንድነትና የፍቅር አለኝታነቱን ለመግለጽ በተሠለፈው ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ኢትዮጵያዊነትን ከውስጣቸው አንቅረው በተፉ ፀረ ሕዝቦች የተፈጸመ መሆኑ ገሃድ የወጣ ጉዳይ ሲሆን፣ ምንም ይሁን ምን ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከትግሉ የሚገታ አንዳች ኃይል እንደማይኖር ግን አመካቷል፡፡ ይልቁንስ ድርጊቱ የበለጠ ቁጭትን በመፍጠር የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያጠናክር ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ ደግመው ደጋግመው እንደሚሉት ወቅቱ የይቅርታ ጊዜ ነው፡፡ የትናንቱን ትተን በአንድነት በመጣመር የአገራችንን የዕድገት ዕጣ ፈንታ እንወስን ማለት ወንጀል አይደለም፡፡ ከመበታተን እንደማመር ማለት የአውሬነት አመለካከት አይደለም፡፡ አውሬነት ግን ብቻዬን ካልበላሁ በማለት የሰውን ነፍስ የሚያጠፋና ደም የሚያፈስ የሰይጣን ተልዕኮ ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሕዝብ በ27 ዓመታት ውስጥ በርካታ ጉዳዮችን ዓይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ተጨማሪ የመከራ ቀንበር የሚሸከምበት ጫንቃም ጊዜም የለውም፡፡ በመሆኑም በእርስዎ የተጀመረው የሀቅ፣ የትግልና የአንድነት ጉዞ ሳይቀዘቅዝ ግለቱን ጠብቆ መቀጠል አለበት፡፡ በሌላ በኩል መሪ እንደ ንብ አውራ ሆኖ ያገለግላል እንጂ ብቻውን የትግል ጀማሪና ፈጻሚ መሆን ስለማይችል፣ ለጀመሩት ብሩህ ተስፋ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎንዎ የቆመ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ስለኢትዮጵያ ታሪክ ለመግለጽ በእኔ ደረጃ አቅም ስለማይኖረኝ ጉዳዩን ለባለሙያዎች በመተው ቀሪ ሐሳቦቼን እገልጻለሁ፡፡ ይቅርታ ከምንም በላይ ከባድ ዋጋ ያለው ቁም ነገር ነው፡፡ ይቅርታ መለኪያ የሌለው የችግር መፍቻ መሣሪያ ነው፡፡ በይቅርታ የታጀበ አገርና ሕዝብ የብረት ማዕዘን ይሆናል፡፡ ይቅርታ ባለበት አገር መተማመንና ፍቅር ይዳብራል፡፡

በዚሁ መሠረት ትናንት በውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች በአመራርነትዎ ጊዜ ይቅርታ ስለተደረገላቸው፣ ከእስር የተፈቱና አገራቸውን ሲናፍቁ የኖሩ ፖለቲከኞች በይቅርታው ተጠቅመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ማየት ከዚህ የበለጠ ልቡን በደስታ የሚሞላ ነገር የለም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን የተጀመረው የይቅርታ ቱሩፋት የበለጠ ሰፍቶ በመሄድ በይቅርታው ተጠቃሚ የሚሆኑትን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚዳስስ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ቢሆኑ የተጀመረውን ይቅርታ የተሟላ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት ባልተለመደ መልኩ በመንግሥት ለውጥ የፈረሰ ቢሆንም፣ ይህ ሠራዊት የኃይለ ሥላሴ ወይም የደርግ ሠራዊት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠራዊት ነበር፡፡ በመሆኑም ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረውን ፊውዳላዊ ሥርዓት ከሥሩ መንግሎ የጣለው አንዱ የኢትዮጵያ ሠራዊት መሆኑ ታሪክ አይዘነጋም፡፡ ይህ ሠራዊት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሠራዊት ጭቁን ሕዝቦች ከባርነት ባልተናነሰ መንገድ የገዥዎች አገልጋይ ሆኖ የኖረ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ ሠራዊት በለውጡ ምክንያት ሲወድቅ አይዞህ ባይ ቢያጣም ኢትዮጵያዊነቱን በመካድ በወንጀል ድርጊት ከመሳተፍ ይልቅ በቀሰመው ሙያ በመታገስ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋም ውስጥ በደኅንነት ሥራ በቢሮ አስተዳደር፣ በመካኒክነት፣ በሹፍርና፣ በግብርና ሥራዎችና ብሎም በሕንፃ ግንባታና በመንገድ ኮንስትራክሽን መስክ እየተሠለፈ ኢትዮጵያዊነትን እንደተላበሰ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ለዚህ ሠራዊት ይቅርታ ተደርጎለት፣ ለጡረታ የበቁት መብታቸው ተከብሮ ቢሰናበቱ፣ የአካል ብቃት ያላቸውና ለጡረታ ያልደረሱትም አሁን ካለው ወንድም ሠራዊት ጋር ተቀላቅለው አገራዊ ግዳጃቸውን ቢወጡ ለጡረታም፣ ለሠራዊቱም አገልግሎት የማይበቁት ደግሞ በአካባቢያቸው ተደራጅተው አገራዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ቢሆን፣ ይቅርታው የዘመኑ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ለዘመናት ሲታወስ የሚኖር ከመሆኑም በላይ አሁን ያለው ሠራዊትም ቢሆን ለወደፊቱ ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው በር ይዘጋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

 (መ/አ አስፋው እንዳለ፣ ቡራዮ ከተማ)

* * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...