Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 126ኛ የልደት በዓል በተከበረበት ሰሞን አንዳንድ ትዝታዎችንና አጋጣሚዎችን ማንሳቱ የግድ ይሆናል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብርቱ ጥረትና ያላሰለሰ ትግል የዛሬ 53 ዓመት የተመሠረተው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጀት፣ የዛሬ 14 ዓመት ገደማ ለተመሠረተው የአፍሪካ ኅብረት መሠረት መሆኑን ዓለም በእርግጠኝነት ያውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኃያል አገር በነበረችው ወራሪዋ ጣሊያን ላይ ዓድዋ ላይ በተጎናፀፈችው አንፀባራቂ ድል ምክንያት፣ ለአፍሪካ ማዕከልነትና መሰባሰቢያነት መታጨቷን በታሪክ ድርሳናት ላይ ሠፍሯል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ጥቁሮች የነፃነት ትግል መነሳሳት ያበረከተችው በመስዋዕትነት የተፈተነ ድል፣ ለአፍሪካውያን ግርማ ሞገስ አድርጓት እንደነበረም የተረጋገጠ ማስረጃ ነው፡፡ ማንም ሊክደው የማይችል!

ከጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከየጎራው እየተጠራሩ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫን ወደ ሌላ ሥፍራ ሊያዘዋውሩ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት፣ እንዲሁም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟቸውን ፈተናዎች ተጋፍጠው እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁንም አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የአፍሪካውያን መናኸሪያነቷ ቀጥሏል፡፡ አዲስ አበባችንም ከታላላቅ የዓለም ከተሞች ተርታ ተሠልፋ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ናት፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ግን አሁንም ፈታኝ የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህ መሰናክሎች በጥበብና በብልኃት ይታለፉ ዘንድ ደግሞ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በታላቅ አገራዊ ፍቅርና በባለቤትነት ስሜት በእኩልነት ልናስብበት ይገባናል፡፡ 

በሰሜን አፍሪካ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አብዮት ምክንያት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኰሎኔል ሙአመር ጋዳፊ፣ ታላቁ ምኞታቸውና ሕልማቸው አፍሪካን በማዋሀድ ንጉሠ ነገሥት መሆን ነበር፡፡ ይኼንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሊቢያውያን በሕዝባዊ አብዮታቸው ውጊያ ወደ ትቢያ የለወጧትን ሶርትን የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለማድረግ ብዙ ጥረው ነበር፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በመከስከስ ለአፍሪካ መሪዎች ቪላዎችን ከመገንባታቸውም በላይ፣ የትውልድ ከተማቸውን ሶርት የምድር ገነት በማድረግ የአፍሪካ ኅብረትን ወደዚያ ለመውሰድ ከፍተኛ ሴራ ሠርተዋል፡፡ ‹‹እባብ የልቡን ዓይቶ እግር ነሳው›› እንደተባለው እሳቸውም እንዳይሆኑ ሆነው አለፉ፡፡ የ42 ዓመታት ግዛታቸው በወራት ሕዝባዊ ትግል ወደ ትቢያነት ተለወጠ፡፡ ዛሬ ታሪክ አቅጣጫውን ለውጦ የነበረው እንዳልነበረ ሆናል፡፡

በዓባይ ውኃ የተነሳ ዘወትር እምነት የማይጣልባት ግብፅ አምባገነን ገዥ ሆስኒ ሙባረክ በይፋ ወጥተው ዘመቻ ባያደርጉም፣ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ተቀባይነት እንዳይኖራትና የግጭትና የብጥብጥ ማዕከል ናት ለማሰኘት በሥውር በርካታ አስከፊ ተግባራት አከናውነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ለኃይድሮ ፓወር ኤሌክትሪክ ግንባታ የምታውለውን የብድርና የዕርዳታ እንቅስቃሴ በተለያዩ መንገዶች ያደናቅፉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ከፈረጠመች ከ85 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ በምታደርግበት ዓባይ ላይ ተፅዕኖ ትፈጥራለች በማለት፣ የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ግብፅ በሚስጥር ታሴር ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ ሲሰደድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ይቀዘቅዛል፣ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ሊኖራት አይችልም በሚል እሳቤ ብዙ ደባዎች ተሠርተዋል፡፡ ለጊዜው ደባዎቹ ሳይሳኩ ‹‹የግብፁ ፈርኦን›› ከሥልጣናቸው በሕዝባዊው አብዮት ተባረሩ፡፡ ለጊዜው ዕፎይታ ቢሰማንም ውሎ አድሮ የሚመጣው ስለማይታወቅ መመካከሩ አይከፋም፡፡ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ብዙ ጥረት አሉና፡፡

የአፍሪካና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መቀመጫ በሆነች አገር አሁንም በቂ መንገዶች የሉም፡፡ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የኢንተርኔትና የመሳሰሉት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ አገሪቱ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥታ ካልሠራች ነገ የሚነሱ አዳዲስ ኃይሎች ወደ ካይሮ፣ አቡጃ፣ አክራ፣ ደርባን፣ ኬፕታውን፣ ወዘተ. . .  እንሂድ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ምቹና አስተማማኝ ሆቴሎች ፀጥታ፣ መስተንግዶ፣ የትራንስፖርት አቅርቦትና የከተሞች ፅዳት ደግሞ መታሰብ አለባቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከቱሪዝም ጋር የሚያያዙ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ በርካታ ፍላጎቶች ከጊዜ ጋር እየተቀናበሩ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ ደግሞ ብቃትና ውጤታማነትን መላበስ ያስፈልጋል፡፡  

ዘመናዊውን የአፍሪካ ኅብረት ዘመናዊ ሕንፃ እያየሁ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ እንቅልፋቸውን አጥተው የሚሠሩ የሕዝብ ልጆችን ናፈቅኩ፡፡ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚመሩንን የዘመኑን ‹‹ሙሴዎች›› ፈለኩ፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ የነፃነትና የአርነት አርዓያነቷ ናፈቀኝ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ፍላጎት በዚህ ዘመን ዕውን የሚሆንበት ምልክት እየታየ ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የገነባችውን ዝና መቼም ቢሆን መካድ አይቻልም፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት በዚህ ክብር ላይ በመመሥረት ለእናት ኢትዮጵያ ትንሳዔ የምናስብም ሆነ በተግባር የምንማስን፣ የትናንቱን ድካምና መስዋዕትነት ለዛሬው ጥረታችን ዕርሾ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መቀመጫ መሆን የቻለችው ለፓን አፍሪካኒዝም መሠረት በሆነው የታላቁ ዓድዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል ምክንያት መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን? ይኼንን ታላቅ ድል ለማስመዝገብ የተከፈለው መስዋዕትነትስ? ይኼንን ገድል በመዘከር ታሪክ የማይረሳው ሥራ ያከናወኑትን ንጉሠ ነገሥት መርሳትስ ይቻላል? ታላቅ መሆን የሚቻለው በአንድነትና በፅናት የመቆም አቅም ሲገነባ በመሆኑ፣ በዘመናችን ከከፋፋይና ከበታኝ ተግባራት በመታቀብ አገራችንን እናስቀድም፣ ከዘረኝነትና ከጠባብነት እንታቀብ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚታወሱባቸው አሉታዊ ድርጊቶች ቢኖሩም እንኳ፣ በዓለም የሚታወቁባቸው በርካታ አንፀባራቁ ተግባራት እንዳሉ እናስታውስ፡፡ ታላቅ ለመሆን የሚፈልግ ታላላቆቹን ማክበር ግድ ይለዋል፡፡ በየመንደሩና በየጎጡ እየተበላሉ ታላቅ መሆን አይቻልም፡፡

(ዓምደ ወርቅ ያፌት፣ ከበቅሎ ቤት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...