Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክአገርን ለማረጋጋት የመንግሥት በሕግ የመመራትና የመምራት ኃላፊነት

አገርን ለማረጋጋት የመንግሥት በሕግ የመመራትና የመምራት ኃላፊነት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ከብዙ አቅጣጫዎች ብንመረምረው የሽግግር ጊዜ ላይ ያለች ትመስላለች፡፡ የሽግግር የሚያስመስለው መንግሥታዊ ተግባራቶቹ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት የሚሠራቸው፣ ማድረግ የሚጠበቅበት፣ ማከናወን የሚገባውን ኃላፊነት የረጋ ቅርፅና ሥርዓት መስያዝ የሚያንሰው ስለሚመስል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥርዓትና ሕግን ብቻ መሠረት አድርጎ ለመሥራት ይመች ዘንድ መንግሥት የሚጠቀማቸው ሥልቶች፣ የሚያደርጋቸው ተግባራት ጥብቅ በሆነ የሕግ አተገባበር ከመመራት ያለፈ ስለሆነ ነው፡፡

ሕግን ብቻ መሠረት በማድረግ መንግሥታዊ ግዴታንና ኃላፊነትን መወጣት አገራችን ያጋጠማትን ችግር ለመቅርፍ በቂ አይደለም የሚል እሳቤ የተያዘ ይመስላል፡፡ በመሆኑም፣ በይቅርታና ምሕረት በመሳሰሉት ተጨማሪ የችግር መፍቺያ መፍትሔዎችን መተግበር ተመርጧል፡፡

 በተለይ አጥብቆ ሕግን በመተግበር አገራችንን ያጋጠማትን ችግር በፍጥነት ዕልባት ለመስጠት አዳጋች ያደረገው የብሔር ዳራ የያዘ ውጥረት ስለተፈጠረ ነው፡፡ ይሁንና አገር ህልውናዋ የሚጠበቀው፣ አንድ አንድ አካል መኖሯ የሚቀጥለው አስተዳዳሪዋና ጠበቂዋ የሆነው መንግሥት ለመጠበቂያና ለማስተዳደር የሚጠቀምባቸውን ሕግጋት በመሥራት ነው፡፡ ሕግጋቱንም ቀድሞ ለአገሪቱ ሕዝብ ቀድሞ በማሳወቅ ነው፡፡

መንግሥት የትኛውንም ሥራ ሲያከናውን በታወቀ ሥርዓት መመራትና ሕግን መሠረት እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡ ይህ በሽግግር ላይ ባለች አገርም ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡ ይቅርታም በሕግ፣ ምሕረትም በሕግ፣ እርቅም በሕግ ሌሎችም ነገሮች እንዲሁ በሕግ መሆን መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

እንግዲህ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ገዥው ፓርቲ፣ ኢሕአዴግ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አስተዳደር በሕግ ብቻ ባለመወሰን የፈጸሟቸው ተግባራት አሉ፡፡ በመንግሥት መፈጸም ሲኖርባቸው በፓርቲ፣ በሕግ አማካይነት ሊከናወኑ ሲገባቸው በቃላዊ ትዕዛዝ ውሳኔ የተሰጠባቸው፣ ፓርላማ ሕግ ከወጣ በኋላ መደረግ ሲገባቸው አስፈጻሚው በራሱ ጊዜ የወሰናቸው ድርጊቶች ብዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ቆም ብሎ ላስተዋለ አመዛዛኝ ሰው አሁን ላይ ሕዝቡ ሕግም ጭምር ይከበር የሚል ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ያስተውላል፡፡ ይህንን ደግሞ በተለያዩ ሚዲያዎች ሰዎች የዚህ ዓይነት ይዘት ያለውን ሐሳባቸውን እየገለጹ ስለሆነ ከእንዲህ መሰሉ የመረጃ  ምንጮች መደምደሚያው ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

 በመሆኑም መንግሥት ባለፉት ስምንት ወራት በተለይም ዶክተር ዓቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ አገራችንን ወደ ተረጋጋና ሥርዓት ያለው፣ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ የመመለስ ተስፋ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ብዙ በጎ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ መንግሥት ከእስካሁኑ የሕግ ማስፈጸም የኃላፊነቱ ጉዞው ተምሮ ማስተካከል እንዳለበት የሚያመለክቱ ፍንጮች አሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ሕዝብ በተለያየ መልኩ እየጠየቀ በመሆኑ፡፡ ሕግን ያልተከተለ መንግሥታዊ አሠራር ምንም እንኳን ውጤቱ ሰናይ ቢሆንም፣ የሚያስከትለው ሌላ መዘዝ ሊኖር ስለሚችል፣ እያስከተለም ስለሆነ ሕግን ማስቀደም ይገባል፡፡ ይህንን ድምዳሜ ለማስረዳት የሕግን ፋይዳዎች አገራችን አሁን ላይ ካጋጠሟት ፈተናዎች አንፃር በማሰናሰል ማብራራት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

ሕግን የማሳወቅ ፋይዳና ያለማሳወቅ ፍዳ

መንግሥት አሠራሩን አስቀድሞ ለሕዝብ የሚያሳውቀው ሕግ በማውጣት ነው፡፡ በወጣው ሕግም መሠረት መንግሥት ተግባሩን ያከናውናል፡፡ ሕዝቡም እንዲሁ መብትና ግዴታውን አውቆ ኑሮውን ይቀጥላል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት ግን አንዳንድ መንግሥታዊ ሥራዎች ቀድሞ ሕግ ወጥቶ ሕዝቡ አውቆት የሚተገበሩ አልነበሩም፡፡

ፓርላማው ሕግ አውጥቶ ምሕረት ከሰጠ በኋላ መፈጸም የነበረባቸው ቢኖሩም ይህ ሳይሆን የተከናወኑ አሉ፡፡ በምሳሌነት ለመውሰድ ከተወሰነ መጠን በላይ የውጭ ምንዛሪ በግል ይዞ መገኘት የወንጀል ኃላፊነትን ያስከትላል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ወደ ባንክ በመሄድ ሰዎች በብር መንዝረዋል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነታቸውም ቀርቶላቸዋል፡፡

 በእርግጥ ከብሔራዊ ባንክ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሕግ ከሚያዘው በተቃራኒው የውጭ ገንዘብ ሕግ ከልክሎና ወንጀል አድርጎት ለዓመታት ሲመነዝሩ በወንጀል የተጠየቀ ሳይኖር፣ የውጭ ምንዛሪውም በግለሰቦች እጅ ገብቶ ሕግ አስከባሪው ሕጉን ማስፈጸም ባልፈለገበት ወይም ባልቻለበት አገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ወደ ባንክ ሊያስገቡ ሲሉ በወንጀል እንዲጠየቁ ማድረግ በምንም መልኩ ፍትሐዊና ተጠየቂም ሊሆን አይችልም፡፡

ይሁንና ሕግ አውጪው ያወጣው ሕግ ደግሞ መከበር አለበት፡፡ ይሄን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው በማሳወቅ ሕግ እንዲያወጣ በማድረግ ሊፈጽሙ ይችሉ ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ድርጊቱ ምሕረት የማድረግ ነው፡፡ ምሕረት የሚሰጠው ደግሞ ሕግ አውጪው ነው፡፡ ምሕረቱ እስከ መቼ ድረስ የውጭ ገንዝብ ወደ ባንክ ለሚያመጡት ብቻ እንደሚገለግል መታወጅ አለበት፡፡

 ይህ ካልሆነ ውሎ ሲያድር ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ዘወትር ሕግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን መወጣት በሚጀምሩበት ጊዜ ተመሳሳይ የወንጀል ተግባር ውስጥ ገብተው፣ ነገር ግን በተመሳሳይ ደረጃ ተጠያቂ ባለማድረጋቸው አድሏዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ መልክ በሕግ የተከለከሉ ተግባራትን ለበጎም ቢሆን ሕግን ሳይከተሉ ከመፈጸም ፓርላማው የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በፍጥነት ሕግ እንዲያወጣ በማድረግ ማከናወን የተሻለ ነው፡፡ እንዲሆን ሲሆን ኅብረተሰቡም ሕግ ላይ የሚኖረው አመኔታ እንዲጨምር ያግዛል፡፡

የሕግ ጠቀሜታዎች ብዙ ናቸው፡፡ የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ፣ የሞራል መሠረቶችንና ባህርያትን ለመቅረፅ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን፣ በሥርዓት የሚከናውን ልውጥን ለማሳለጥ፣ ለድርድር መሠረትና መነሻ ወይም የጨዋታ ሕግ ለመሆን፣ ቅዶችን ለመተግበር (ሥራ ላይ ለማዋል) ይጠቅማል፡፡

ፍትሕ ለማስፈን የተበደሉና የበደሉ ዜጎችን ግንኙነት ማስተካከል

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተላለፈው፣ ብዙ ሰውም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እንደሚያውቀው በርካታ እስረኞች በመንግሥት በተቀጠሩ ሠራተኞች (የፀጥታና ሠራተኞችና ፖሊሶች) ዘግናኝ የሆነ ስቃይ ደረሶባቸዋል፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን ተፈናቅለው አሰቃቂ ሕይወት በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት መፈጸም ወንጀል ነው፡፡ ማፈናቀልም ወንጀል ነው፡፡

እነዚህ ሁለቱን በምሳሌነት አነሳን እንጂ ሌሎችም አሉ፡፡ ሕግ ተጥሶ፣ ዜጎች ተበድለው፣ ሕጉ በሚለው መሠረት የተበደሉ ሰዎችን ፍትሕ ካላገኙ፣ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙት ሰዎችም ተጠያቂ ካልሆኑ ፍትሕ አልሰፈነም ማለት ነው፡፡ ሕግ የሚወጣው ፍትሕ ለማስፈን ነው፡፡ እንደ ሕጉ ሳይፈጸም አለበለዚያም ፍትሕ ለማስፈን ሌላ ዓይነት አማራጭ ሥራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በደልና ስቃይ የደረሰባቸው ዜጎች ፍትሕ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት እስከዛሬ የተፈጸመውን በመተው የተበደሉ ሰዎች የበደሏቸውን ይቅር እንዲሏቸው በማድረግ ፍትሕ ለማስፈን በአንድ በኩል የተጎጅዎች ፈቃድ ሲያስፈልግ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ የወንጀል ድርጊቶች መፈጸማቸው ከታወቀ ተጎጅዎች ክስ ባያቀርቡም ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ በራሳቸው አነሳሽነት የወንጀል ክስ የመመሥረት ግዴታ አለባቸው፡፡

በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቃይ ዜጎች ባለቡት አፈናቃዮቹ ግን ያለምንም ተጠያቂነት ሕይወታቸውን መምራታቸው፣ ለመስማት እንኳን የሚከብዱ እጅግ አሰቃቂ የስቃይ ተግባራት የተፈጸመባቸው ዜጎች ከእነስቃያቸው፣ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳታቸው ኅብረተሰቡም ይህንኑ አውቆት ሁኔታው እንዴት ዕልባት እንደሚሰጠው በማያውቅበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ በደለኛ ባለበት አገር ፍትሕ ሳይሰጡ ወይም እንዴት ፍትሕ እንደሚያገኙ መንግሥት ሳያሳውቅ መቀጠሉ የሕግን ፋይዳ ወደ ጎን መግፋት ነው የሚሆነው፡፡

 ሕግን ተግባራዊ በማድረግ ወይም ያልተተገበረበትን ምክንያት ሳያሳውቁ በለሆሳስ ማለፍመ ለፍትሕ ዋጋ አለመስጠት ነው፡፡ ተቀዳሚ ከሆነው የመንግሥት ኃላፊነት አንዱ ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ የበደለም ሳይጠየቅ ወይም በምን መንገድ እንዳልተጠየቀ ሳይታወቅ፣ የተበደለም ስለበደሉ ፍትሕ ሳያገኝ እንዲቀር ማድረግ ውሎ ሲያድር መንግሥት አገርን በሕግ የማስተዳደር የሞራል መሠረቱን እያጣ ይሄዳል፡፡

በሕግ አለመሥራት የመንግሥታዊ ተቋማትን ቅቡልነት ለማሳጣት

አገር እንዲተዳደርባቸው መንግሥትም እንዲያስተዳድርባቸው በሕግ የሚቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች መኖራቸው ግድ ነው፡፡ የእነዚህን ተቋማት ተግባርና ኃላፊነታቸው በሕግ ለይቶ ማሳወቅ የተለመደ ነው፡፡ እንደ ሕጉ ኃላፊነታቸውን መወጣትም ግዴታቸው ነው፡፡ እንደ ሕጉ የማይሠሩ ከሆነ ግን መንግሥትም በጥቅሉ፣ በተለይ ደግሞ ተቋማቶቹ በሕዝብ ዘንድ የሚኖራው ተቀባይነት እየመነመነ መሄዱ አይቀርም፡፡

አድሏዊ አሠራር ደንበኛው ልማዳቸው ከሆነ፣ በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ካልተወጡ፣ ወዘተ አሠራራቸው በሕግ አልሆነም አለበለዚያም ሕጉ በሚጠይቀው ልክ አልሆነም ማለት ነው፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆኑት የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት ናቸው፡፡ በእርግጥ ብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ሕዝብ አመኔታ አለው ማለት ይከብዳል፡፡ አሁን ላይ መንግሥትም ነገሩ ገብቶት ማሻሻያ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ ተቋማት ሕጉ የጣለባቸውን ግዴታ መወጣት፣ በሕግ መሥራት ሲጠበቅባቸው በተቃራኒው በመጓዛቸው ቅቡልነት ተሽመድምዷል፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሥታዊ ተቋማት እንዲያስፈጽሙ ግዴታ የተጣለባቸውን ሕግ ማናወን ካልቻሉ ሕዝብም አመኔታው ይጠፋል፡፡ መንግሥትም እነዚህን ተቋማት በመጠቀም ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው አስተዳደራዊ ሥራ ማከናወን ይከብደዋል፡፡

ሕግን አለማስከበር ሥርዓታዊነትንና ሰላማዊነት ማናጋት

ሕግ አንዱ ፋይዳው የሰው ልጅ ሥርዓት ባለው በታወቀ ድኅነቱ በተጠበቀ ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ለመኖር ነው፡፡ መንግሥትም ሕግን በማውጣት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት ሰላምና ፀጥታ እንዲኖር ነው፡፡ በሕግ አለመከበር ሥርዓት ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ሊጠፋ፣ ፀጥታ ሊደፈርስ፣ ሰላም ሊናጋ ይችላል፡፡

የመንግሥት መኖርም የሚታወቀው በየትኛውም አገሪቱ ክልል ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶችን፣ የሰዎች እንቅስቃሴ መቆጣጠር የሚችል ሲሆን ነው፡፡ የፀጥታና ሰላም መከበር እርግጥ የሚሆነው በየትኛው ቦታ ፀጥታን የሚያጠፋ፣ ሰላምን የሚያናጋ ድርጊት እንዳይፈጸም መቆጣጠር፣ ከተፈጸመም ሁኔታውን አጣርቶና መርምሮ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ዜጎች ዋስትና እንዲኖራቸውም እንዲሰማቸውም ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

አሁን ላይ አገራችን የፀጥታና የሰላም ሁኔታ አስተማማኝነት የጎደለው ስለሆነ ዜጎች ለሕይወታቸው፣ ለንብረታቸው፣ ለነፃነታቸው ዋስትና ያነሰበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ከባለፉት ሁለት ዓመታት አንፃር ሲለካ በጥቅሉ እየተሻሻለ ነው ማለት ቢቻልም ፍርኃትና ሥጋት ግን መልሶ እየነገሠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕግ ተጥሶ እያለ የጣሱት ሰዎች ለተሻለ አገራዊ መግባባት ሲባል ተጠያቂነታቸው ቀርቶም ከሆነ ለሕዝብ ይገባል፡፡

ሕግ እንደጣሱ ወንጀል እንደፈጸሙ ለሕዝብ እያሳወቁ ነገር ግን ለፍትሕ እንዲቀርቡ አለማድረግ ሌላ አለመረጋጋትን የፀጥታ መጓደልን የሰላም መደፍረስን መጋበዝ ነው ትርፉ፡፡ በወንጀል የተጠረጠረን ሰው ይፋ በራሱ ማስረጃ እንዲያጠፋ፣ እንዲሠውር አቅሙም ያለው ከሆነ ከዚያ ያለፈ ተግባር እንዲፈጽም ማበረታት ነው፡፡ ፖሊስ አንድን ተጠርጣሪ ይዞ በዋስ እንዳይለቀቅ የሚጠይቅበት ማንም የሚያውቀው ምክንያት ማስረጃ እንዳያጠፋ፣ ምስክሮች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ፣ ወዘተ ነው፡፡ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር መሥራት ማስረጃ ለማጥፋት፣ ምስክርን ለጉዳት ማጋለጥ፣ ካልሆነም ብሔርን እንደመደበቂያ ለማድረግ በተለያዩ ብሔሮች መካከል ውጥረትን የሚያስከትል መዘዝ ይኖረዋል፡፡

ስለሆነም ሕግን በአግባቡ መተግበር ካልሆነም ምክንያቱን ይፋ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ ሕግን የጣሱ ሰዎች እንዳሉ ለዚያውም ከባድ የሆኑ ወንጀሎች እንደፈጸሙ ለአደባባይ ማዋል ውጤቱ ፀጥታንና ሰላምን ለአደጋ ማጋለጥ ዜጎችን ዋስትና እንዳነሳቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ነው፡፡

ማኅበራዊና ግለሰባዊ ለውጥን ለማምጣት በሕግ መመራት

እዚህ ላይ ስለለውጥ ሲነሳ በመንግሥት ፊታውራሪነት የሚመራን ነው፡፡ ለውጥ ቀድሞ የነበረን አሠራር፣ ልማድ፣ አመራር፣ ወዘተ እንዲለወጥ የመሻቱ ሰፊ ነው፡፡ ለውጡ ሲተገበር የሚጠቅመውም የሚገዳውም መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለውጡ የሚጎዳው ማንገራገሩ፣ ለውጡን ለማስቀረት መጣሩ የሚጠበቅ ነው፡፡

የሆነ ሆነ መንግሥት የሚያደርጋቸው ለውጦች በሕግ የሚመሩ ሊሆኑ ግድ ነው፡፡ ቁም ነገሩ የሚመጣን ለውጥ ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ሕዝቡ ለውጡን ሲቀበለው አስፈላጊ የሆኑ ሕግጋትንም አብሮ የመቀበል ዕድሉ ይጨምራል፡፡ ለውጡን ለመተግበር የወጡ ሕግጋትን የሚጥሱ ለውጡን የሚያደናቅፉ ሰዎች ምን ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ቀድሞ ማሳወቅ ነው፡፡

ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት እስከዛሬ ብሔራዊ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ብዙ አገራዊ አጀንዳዎች ስላሉ፣ ኢኮኖሚያዊም ማኅበራዊም ለውጥ ለማምጣት መግባባቱ ቅድሚያ ይወስዳል፡፡ ይህንን የብሔራዊ መግባባት ፕሮጀክት ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልጉ ሕግጋት ይኖራሉ፡፡ ወይም ደግሞ ለጊዜው ሥራ ላይ መዋላቸው መቆም ያለበት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሁለቱም ሁኔታ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ በመንግሥት የሚመራ ለውጥን ለማሳካት አዳዲስ ሕግ ሊያስፈል ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜም ቀድሞ ሕግ ካልወጣ ለውጡ ሥጋት ላይ የሚጥላቸው ሰዎች ማኅበራዊ ለውጥ እንዳይመጣ ሊያሰናክሉ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም የሕግን ሚና በአግባቡ በመረዳት መንግሥታዊ ሥራ በሕግ እንጂ፣ በሌላ እንደማይመራ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ሕጉ ከሚለው በላይ ማድረግን ሕግ አይከለክልም፡፡ ‹‹ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው›› የሚባለውም ሕግ የመጨረሻው ዝቅተኛው በሰዎች መካከል ሥርዓት ያለው የታወቀ መስተጋብርና ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ ግቡም በተቻለ መጠን ማፋቀርና ማስማማት ስለሆነ ነው፡፡ ፍቅርና መስማማት ባይኖር ቢያንስ በሕግ ይኖራል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...