Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉስለሚታየው ብቻ ሳይሆን ስለማይታየውም እንነጋገር

ስለሚታየው ብቻ ሳይሆን ስለማይታየውም እንነጋገር

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

በአሜሪካውያንና በዓለም ሕዝብ እጅግ ተወዳጅና ታዋቂ የሆኑት ከሃምሳ ዓመታት በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ ‹‹አገርህ ምን እንድትሠራልህ ሳይሆን ለአገርህ ምን እንደምትሠራላት አስብ፤›› ብለው ከአሜሪካውያን ልብ ውስጥ የማይጠፋ ንግግር ተናግረዋል፡፡ ሐኪም እንደ ሐኪምነቱ፣ መሐንዲስ እንደ መሐንዲስነቱ፣ ጋዜጠኛው እንደ ጋዜጠኝነቱ፣ ኢኮኖሚስት እንደ ኢኮኖሚስትነቱ ሌላውም እንደየሙያው ለአገር መሥራት የሚገባቸው ሥራዎች አሉ፡፡

ኢኮኖሚስቶች እንደ ሌሎች ሙያዎች ቢሮ ተቀምጦ በመሥራት ብቻ የሕዝብን ኑሮ ማሻሻል ይችላሉ? ወይስ ሙያቸውን በመጠኑም ቢሆን ለሕዝብ በማጋራት ነው የኑሮ ደረጃን ማሻሻል የሚቻለው? የሚለው ጉዳይ ሁል ጊዜ ያሳስበኛል፡፡ ሁሉም ሰው ኢኮኖሚስት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ በገበያ ውስጥ አዋቂ ተገበያይ ለመሆን ግን መሠረታዊ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሐሳቦችን ማወቅ ይጠቅማል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገም ቢሆን በገበያ ውጥንቅጥ ምክንያት ታማሚ እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ታማሚ እንደነበረም ግልጽ ነው፡፡ ስለማደጉ ብቻ እየተነጋገርን ስለመታመሙ አልተነጋገርንም፡፡ ሕመሙ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለን ሰዎች ለአገራችን ምን እንደምንሠራ ሳይሆን፣ አገራችን ምን እንደምትሠራልን ብቻ ስለምናስብ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ከሕመሙ እንዲያገግም ኢኮኖሚስቶች በሙያቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሊነግሩት የሚችሉትና የሚገባቸውም ዕውቀት አላቸው፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቁ በሽታ ውድድር የጎደለበት የተዛባ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ነው፡፡ ሕዝቡ ግን የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት መዛባት ኪራይ ሰብሳቢነትን እንደሚፈጥር ስለማያውቅ፣ ከመንግሥት አገልግሎት ጋር የተያያዘ ሙስናን ብቻ ነው ኪራይ ሰብሳቢነት ብሎ የሚጠራው፡፡ ያየውንና ያወቀውን ሕዝቡ ጠርቷል፡፡ ያላየውንና ያላወቀውን አይቶና አውቆ እንዲጠራ ኢኮኖሚስቶች ስለሚታየው ብቻ ሳይሆን ስለማይታየውም መናገር አለባቸው፡፡

በሌጣ ዓይን ብቻ ዓይተው ሊገነዘቧቸው ከማይችሉት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ የግብይይት ባህሪያት ይገኙበታል፡፡ ሰዎች የራሳቸውንና የሌሎች ሰዎችን እንቅስቃሴዎች ሊረዱ ከሚችሉት በላይ ገበያዎች ሳያስተውሉና ሳይገነዘቡ ኑሯቸውን ያወዛግባሉ፡፡ እነኚህን ጉዳዮች ማየትና ማስተዋል ለተሳናቸው ተገበያዮች የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በጽንሰ ሐሳብ ተንትነው ካላስረዱ በቀር የማኅበራዊ ኑሮ ቀውስ ውስጥ ሊከቱም የሚችሉ ናቸው፡፡

በኢኮኖሚክስ ኪራይ ሰብሳቢነት በገበያ ውስጥ የውድድር አለመኖርን የሚያመለክት የገበያ ጉድለት ትርጉም ያለው ቃል ሲሆን፣ ሳናውቀውና ሳንገነዘብ ሁላችንም ለአገሪቱ መሥራት የሚገባንን ሳንሠራ አገሪቱ ልትሰጠን ከምትችለው በላይ ለማግኘት ሽሚያ ውስጥ ገብተን ኪራይ ሰብሳቢዎች ሆነናል፡፡ የእዚህን ሚስጥር ተንትኖ መናገር ስለሚታየው ሳይሆን ስለማይታየው መነጋገር ነው፡፡

ኪራይ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢኮኖሚስ መዝገበ ቃል የገባው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች (Classical Economists) መሀል ስለመሬት አያያዝና አጠቃቀም ጥናት ያደረገው ዴቪድ ሪካርዶ፣ ለመሬት የሚከፈል የአገልግሎት ዋጋ አድርጎ መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡  ዴቪድ ሪካርዶ መሬት በእግዚአብሔር የተፈጠረ የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ እያለ፣ ሰው በቅድሚያ ስለያዘ ብቻ ዋጋ የሚያገኝበት ስለሆነ ኪራይ ያልተለፋበት ዋጋ ነው ብሎ ተርጉሟል፡፡

      ከመሬት ዋጋነት ሌላ ኪራይ ሰብሳቢነት በገበያ ውስጥ እንዴት እንደሚፈጠር ለመረዳት የዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ዴቪድ ሪካርዶን የመሳሰሉ ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች የዋጋ አወሳሰንን የሚረዱት በፈሰሰ ጉልበት ልክ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ ኮት ለመሥራት የሁለት ሰዓት የሰው ጉልበት ቢፈልግና አንድ ሸሚዝ ለመሥራት የአራት ሰዓት የሰው ጉልበት ቢፈልግ፣ የአንድ ኮት ዋጋ የሁለት ሸሚዝ ዋጋን ያክላል፡፡

ካርል ማርክስም የዴቪድ ሪካርዶን የፈሰሰ ጉልበት የዋጋ አወሳሰን ፍልስፍና ወስዶ በካፒታሊስት ሥርዓት ሀብት የሚፈጠረው ካፒታሊስቱ በሠራተኛው የፈሰሰን ጉልበት በዝብዞ ነው በማለት፣ ፊውዳሊዝም በካፒታሊዝም እንደተተካው ሁሉ ካፒታሊዝምም በሶሻሊዝም ይተካል የሚለውን በሶሻሊዝም አድርጎ ወደ ኮሙዩኒዝም ፍልስፍናውን ተነተነ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ካፒታሊስቶች ሶሻሊዝም ዕድገትና ብልፅግናን አያመጣም ብለው ቢጥሉትም፣ የማርክስን የጉልበት ብዝበዛ ፍልስፍና ግን መቃረን አልቻሉም፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተነሱት የካፒታሊዝም ደጋፊ ተሃድሶ ጥንታውያን (Neoclassical) ኢኮኖሚስቶች ግን ለየት ያለ የዋጋ አወሳሰን ኢኮኖሚያዊ ጽንሰ ሐሳብ ተንትነዋል፡፡ አልፍሬድ፣ ማርሻል ሰታንሌ፣ ጄቨንስን ልዮን ዎልራስን የመሳሰሉ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚስቶች ዋጋዎች የሚወሰኑት የምርት ፍላጎትን በሚወስነው የምርቱን ጠቀሜታ በመለካትና የምርት አቅርቦትን በሚወስነው ምርታማነትን በመለካት መሆኑን በኢኮኖሚክስ ተነተኑ፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት የሚፈጠረውና የሚስፋፋው በምርት ጠቀሜታ ላይ ተመሥርቶ ፍላጎቱን የላቀ ለማድረግ የሚጥር ሸማችና በምርታማነት ላይ በተመሠረተ ትርፋማነት አቅርቦቱን የላቀ ለማድረግ የሚጣጣር አምራች ባለመኖሩ፣ እያንዳንዱ ሰው ከአገሩ ምን መውሰድ እንዳለበት እንጂ ለአገሩ ምን መስጠት እንዳለበት ማሰብ ሲሳነው ነው፡፡

ታላላቅና ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ ኢኮኖሚስቶች የሰውን ኢኮኖሚያዊ አኗኗር ዘይቤና የግብይይት ችሎታ ጥበብ በመለካት፣ ለአዋቂ ተገበያይ ኢኮኖሚያዊ ሰው (Economic Man) በማለት የቅጽል ስም እስከ መስጠት ደርሰዋል፡፡ የእኛ አገር ኢኮኖሚስቶችም ይኼንን የኑሮ ዘይቤ ዕውቀትና የግብይይት ችሎታ ጥበብ ለሕዝባቸው አጋርተው ኢኮኖሚያዊ ሰው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢኮኖሚስት መሆን ሳያስፈልግ ሁሉም ሰው የኢኮኖሚያዊ ሰው አኗኗር ዘይቤን ቢያውቅ፣ እያንዳንዱ ሰው ለአገሩ ምን መስጠት እንዳለበትና ከአገሩ ምን መውሰድ እንዳለበት ይረዳል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ሰው ማለት በሚያወጣው ወጪ ልክ ከሸመታው የላቀ ጠቀሜታ ለማግኘት የሚጥር ሸማችና በምርታማነቱ ልክ ከምርቱ የላቀ ትርፍ ለማግኘት የሚጥር አምራች ማለት ሲሆን፣ ኢኮኖሚስቶች ሰው በቂ የገበያ መረጃ አግኝቶ ከተገበያየ በተፈጥሮው አዋቂ (Rational) ነው ብለውም ያምናሉ፡፡ እንደ ሸማች ከወጪያቸው በላይ ጠቀሜታ ለማግኘት የሚስገበገቡና እንደ አምራች በምርታማነት ከተለካ ዋጋ በላይ ሸጠው ለማትረፍ የሚሯሯጡ ሰዎች፣ አዋቂ ለመባል በቂ መረጃ የሌለውን ሰው አታለው ለመክበር የሚሹ በኢኮኖሚያዊ አጠራር ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡

ግብርና ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአየር ንብረት ሁኔታ ላይ ጥገኛ እንደሆነ ብናውቅም ዝናብ ኖረም፣ አልኖረ በድርቅ ተመታንም አልተመታንም በየዓመቱ እየለካን በ11 በመቶ አደገ የምንለው የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት የምንለው ብሔራዊ ኢኮኖሚ እንዳለ የማያውቅ ሰው አለ ብዬ አልገምትም፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት ማለት ለዚህ የምርት ዕድገት በቂ አስተዋጽኦ ሳያደርጉ፣ በክፍፍሉ ሌሎች ለዕድገቱ ካደረጉት አስተዋጽኦ ውስጥ የራስን ድርሻ ለማተለቅ መሻማት ነው፡፡ በዚህ ሽሚያ ውስጥ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ እያንዳንዳችን ገብተንበታል፡፡ በመንግሥት ፖሊሲ ድክመትም ሆነ በገበያ አለመጥራት ምክንያት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለ ሰው ከዕድገቱ ውስጥ የማይገባውን የሌሎች ልፋት ለመጋራት ጥረት ያደርጋል፡፡

በፖሊሲ ድክመት ምክንያት መንግሥት ሠራተኞች ሲቀጥር ለመዋቅር በማያስፈልጉ ቦታዎች ሲመድብም ሆነ ሰውን በሙስና ያለቦታው ሲያስቀምጥ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ለሕዝብ በሚሰጡት አገልግሎት በግብር መልክ ተሰብስቦ በሕጋዊ መልክ ከሚከፈላቸው በላይ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ዋጋ ሲጠይቁም ኪራይ ሰብሳቢነት ይፈጠራል፡፡ በአቅርቦት እጥረትና በፍላጎት መብዛት ምክንያት በገበያ የዋጋዎች አወሳሰን ሥርዓት ሲዛባና ነጋዴዎች ከልፋታቸው በላይ ገቢ ሲያገኙም ኪራይ ሰብሳቢነት ይፈጠራል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በሰዎች ላይ ራስን የመውደድ ተፈጥሯዊ ባህሪ የሚፈጠር ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓቶችም የማባባስ ሚና አላቸው፡፡       በሊበራል የገበያ ኢኮኖሚ ጉድለት ኪራይ ሰብሳቢነት ምን መልክ አለው? የልማታዊ መንግሥት ሥርዓት ኪራይ ሰብሳቢነትን ጨመረ ወይስ ቀነሰ? የሚለውን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንፃር ብንተነትን ለችግሮቻችን መፍትሔ እናገኛለን፡፡ የታመመውን ኢኮኖሚም እናክማለን፡፡ የሊበራል ገበያ ኢኮኖሚና የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚን ጉዳትና ጥቅም ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመጨመርና ከመቀነስ አንፃር ብንተነትን፣ ከሁለቱም ለኢኮኖሚያችን ዕድገት ጉዳቶችን አስወግደን ጥቅሞችን የምንወስድበትን መንገድ መከተል እንችላለን፡፡

የጠቀሜታና የምርታማነት በፍላጎትና በአቅርቦት ብሎም በዋጋ አወሳሰን ላይ ተፅዕኖ አደራረግን አለመለካት፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዋጋ አወሳሰን መዘበራረቅ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ያልፈቱትን እንቆቅልሾች መፍታት የሚችሉም ናቸው፡፡

ስለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቡን አለመምታት ምክንያት ስንነጋገር፣ ስለሚታዩት የመንግሥት ድጋፍ አሰጣጥ አለመሟላት ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ የሚከሰቱትን የሙስና ድርጊቶች ብቻ አድርገን እንቆጥራለን፡፡ የሚታየውን ብቻ በማውራት የማይታየውን የአምራቹን በሆነ ምክንያት የማምረት ተነሳሽነት መቀነስ ሳንነጋገርበት እንቀራለን፡፡ ሸማቹ ሊመረትልኝ የሚፈልገውን ዓይነት ምርት የማውቀው እኔ ነኝ ብሎ ቢያምንም መንግሥት ግን እኔ ልምረጥልህ እያለ ነው፡፡ አምራቹም የመንግሥትን እኔ በጭንቅላቴ ሀብት እያከፋፈልኩ እናንተ በእጅና በእግራችሁ እየሠራችሁ ተባብረን አገርን እናሳድግ አልወደደውም፡፡ እኔም የማስብበትና የሚበጀኝን የማውቅበት በራሴ መንገድ እጅና እግሬን የማንቀሳቅስበት ጭንቅላት አለኝ ብሏል፡፡

ይኼን በሕዝቡና በመንግሥት መካከል ምን መመረት እንዳለበት የመወሰን አለመጣጣም በሌጣ ዓይን አይቶ መረዳት ስለሚያዳግት፣ ኢኮኖሚስቶች ስላለው ነገር ግን በገሀድ ስለማይታየው በመናገርና በመነጋገር የሕዝብ ችግር ስለሚወገድበት ምክር ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅዶች አመልካች እንጂ አስገዳጅ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አመልካች ዕቅዶች ማቀድ ማለት ለፈጻሚ አምራቾችም ሆነ ለተጠቃሚ ሸማቾች የገበያዎችን ዝንባሌ አጥንቶ መንገር ማለት ስለሆነ፣ ዕቅዶቻችን ስለዋጋ አወሳሰን ሥርዓት መርምሮ ማሳወቅና የመንግሥት ፖሊሲ በሀብት ክፍፍልና በዋጋ አፈጣጠር ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ሸማቹና አምራቹ አውቀው አካሄዳቸውን እንዲገሩበት ማድረግ ስላልቻሉ ውጤት አልባ ሆኑ፡፡ ሸማቾችና አምራቾች በግላቸው ለፖሊሲው የሚሰጡት ምላሽ ገበያዎችን በማጥራትና የዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ስለሚያደርገው የኢኮኖሚው ዕድገት ጤናማ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ግን እንደታማሚ ሰው የኢኮኖሚው ዕድገት እብጠት ይሆንና ከጊዜ በኋላ ይፈርጣል፡፡

በዚህ ዘመን በአደጉት አገሮች ውስጥ የመንግሥት ፖሊሲን ሚና በሚያጎሉት የኬንስ ኢኮኖሚክስ ደጋፊ ኢኮኖሚስቶችና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሚናን በሚያጎሉት የጥንታውያን ኢኮኖሚስቶች ደጋፊዎችን አስተሳሰብ እያስታረቀ ያለው፣ ሁለቱንም አውቆ ከሁለቱም የሚጎዳውን ትቶ የሚጠቅመውን መውሰድ ወይም ሁለቱን የሚያዋህድ መንገድ መምረጥ ነው፡፡ በልማታዊ ኢኮኖሚ መንገድ መመራትም የመንግሥትንና የግልን የሀብት ይዞታ ቅንብር በትክክል በመምረጥ ወሳኝ በሆኑ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ አትኩሮ መሥራት ብቸኛው የዕድገት ጎዳና ሆኗል፡፡

የኢኮኖሚስቶች ምክር መሆን ያለበትም ጠለቅ ወዳለ ሙያዊ ትንታኔ ሳይገቡ ሙያዊ ክህሎታቸውን ተጠቅመው ቅንብሩና ወሳኝ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ምርጫ የላቀ ጥቅም በሚሰጥበት ደረጃ እንዲሆን ለማድረግ፣ በሌጣ ዓይን ስለማይታየው በሙያ ዓይን አይተው መምከር ነው፡፡ እኔ ሊበራል ነኝ እኔ ልማታዊ ነኝ መባባል አይጠቅምም፡፡ አሜሪካም ሊበራል ኢኮኖሚ ብቻ አይደለችም፡፡ ቻይናም ልማታዊ ኢኮኖሚ ብቻ አይደለችም፡፡ ኢኮኖሚስቶች ከላይ የተመለከቱትን በሌጣ ዓይን ብቻ የማይታዩትን የኑሮ ሁኔታ ጽንሰ ሐሳቦችን ብቻ እንኳ በሕዝቡ ዘንድ ቢያሰርፁ፣ ገበያዎቻችን ተስተካክለው የተሻለ ኑሮ ልንኖር እንችላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡                                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...