Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉያለንን ሁሉ ሰጥተን ሳንጨርስ እኛም የምንቀበለውን እንወቅ

ያለንን ሁሉ ሰጥተን ሳንጨርስ እኛም የምንቀበለውን እንወቅ

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ከሦስት ወራት በፊት ከነበረችበት ጋር ስናወዳድረው፣ የአሁኑ ሁኔታ በሁሉም መልኩ ቢሆን አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ ገጽታው ይኼ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሁለት ወቅቶችን አወዳድረን የኋለኛው ከፊተኛው በሁሉም ነገር የተሻለ ከሆነ፣ ጉዟችን በትክክለኛ ወይም በተሻለ ጎዳና ላይ ያለ ከመሆኑም በላይ ተስፋችን ብሩህ መሆኑን ያሳያል፡፡ አንድ አገር ውስጥ ሁሉ ነገር የሚሆነው በመሪዎቿና በሕዝቡ መካከል በሚኖረው መስተጋብር ነው፡፡ መንግሥት በሕዝብ መወደድና መከበርን የሚያጎናፅፈውን ሥራ መሥራት  አለበት፡፡ ሕዝብም መንግሥትን ማክበርና መውደድ አለበት፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ይኼ ነገር ሲሆን አይታይም፡፡ አንድ የኦሮምኛ አባባል ይኼን ጉዳይ እንዴት እንደሚገልጸው ልጥቀስ፡፡ ‹‹አምላክ ሕዝቡን ሲቀየም ክፉ ሰው አምጥቶ በአገሩ ላይ ይሾምበታል፡፡ ሰውዬውን ሲቀየመው ክፉ አገር ወስዶ ይሾመዋል፣ ሕዝቡን ሲታረቀው ደግሞ መልካም ሰው አምጥቶ ይሾምለታል፤›› ይላል፡፡ በአንድ ወቅት እግዚአብሔር የለም ተብሎ በግልጽ በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ልፈፋ ሲደረግ ነበር፡፡ ታዲያ አምላክ ተቀየመንና ክፉ ሰው ሾመብን፣ የሆነውን እናውቃለን፡፡ በዚያ ዘመን እንደ ኖህ ዘመን ያለመጥፋታችንም በቸርነቱ ነው፡፡

የአሁኑን ጅምር ስናይ ግን የትምህርት ዘመን የመጣ አይመስልም? ስለጥላቻ ሳይሆን ስለፍቅር፣ ስለመለያየት ሳይሆን ስለአንድነት (መደመር)፣ ስለበቀል ሳይሆን ስለይቅርታ ሕዝቡን የሚያስተምር መሪ ማግኝቱ በራሱ እርካታን ይሰጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አስተምህሮአቸውን እየተገበሩም ነው፡፡ የታሰሩትን ፈተዋል፡፡ የታመሙትን ጠይቀዋል፡፡ የተሰደዱትን መልሰዋል፡፡ ይቅርባይነት ይኼ ነው፡፡ ለፍቅር ሲሉ ከሃያ ዓመታት በላይ የተለያዩትን የኤርትራንና የኢትዮጵያን የከረረ የጠላትነት መንፈስ አስወግደው ዕርቀ ሰላም ለማውረድ፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዘዋል፡፡ ሕዝቡንም አስፈንድቀዋል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም ማውረድና ተከባብሮ ለመኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገባቸውን አድርገዋል፡፡ ይኼን ጅምር ሒደት ማስቀጠል ከቻለን የምሕረት ዘመን እንደመጣ እንወቅ፡፡ በአሁኑ ወቅት የመንግሥትና የሕዝብ ስሜት የተዋሀደ ስለሚመስል አብዛኛው ሕዝብ መንግሥትን እየደገፈ ለመሆኑ በየዕለቱ ማስረጃ የሚቀርብ ነው፡፡ ለጊዜው መንግሥትም ወዶናል፡፡ እኛም ወደነዋል፡፡ ዓለምም ወዶናል ብለን ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ እንዴት እንጠቀምበት ይሆን?

እንደ አገር መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀምና ማስቀጠል አቅቶን ብዙ ጊዜ ከመንገድ እየወጣን፣ ብዙ ኪሳራ አስከትሎብን አገሪቱን ወደ ኋላ የሚያንሸራትቱ ተግባራት ፈጽመናል፡፡ ይኼ ፀፀት ከልባችን ሊጠፋ አይችልም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ሕዝቡ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት ቃል እየገባ ነው፡፡ ይቅርታን፣ ሰላምንና መደመርን በአባባል ደረጃ የጋራው አድርጎታል፡፡ በርካቶች ግን ተግባሩ ላይ ሲደርሱ የማይዋጥላቸው አሉ፡፡ ይቅርታ ማድረግ ማለት የሚወዱትን ሰው የበለጠ መውሰድ አይደለም፡፡ ይቅርታ የሚደረገው ላስቀየሙንና ላስቀየምናቸው ነው፡፡ እኛስ በእውነት አስቀይመውናል ወይም በድለውናል ብለን ለምንገምታቸው ሁሉ ይቅርታ ለማድረግ ዝግጁ ነን? ለወዳጅ እኮ ፍቅር እንጂ ይቅርታ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ ለተየቀምናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይቅርታ ካላደረግን በጥላቻና በፀባችን ልንቀጥል ነው፡፡ ይኼ እሽክርክሮሽ ነው ወዳልተጠበቀ ቀውስ፣ ገፋ ሲልም ወደ እርስ በርስ ግጭት እያመራ እስከ ዛሬ ድረስ በድቅድቅ ጨለማ እንድንኖር ያደረገን፡፡ ቃል የተገባለትን የፍቅር ድልድይ ለመገንባትና የለያዩንን አጥሮች ለማፍረስ በመጀመርያ ይቅርታ ይቀድማል፡፡ ይኼን ካደረግን እንደ ሕዝብ የሚገባንን ሠርተን የመሪያችንና የአጋሮቻቸውን ራዕይ ተገበርን ማለት ነው፡፡

አንዳንዶቻችን በአንድ ወቅት በሆነ አጋጣሚ የተቀየምናቸውን ወገኖች የማግለል ስሜት እናሳያለን፡፡ መደመር ስንል አዲስ ጨምረን ነባሩን መቀነስ አይደለም፡፡ የተቀነሰውን ደምረን ያለውን ማቆየት ነው፡፡ በፓርቲ ውስጥ የሆነ እንደሆነ ግን መደመርና መቀነስ (Purge and Emerge) ያለና የሚኖር ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ግን መደመር እንጂ መቀነሱ እንዳይኖር ነው የተነገረን፡፡ እኛም ተስማምተን ድጋፋችንን በሆታና በጭብጨባ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የገለጽን ስለሆነ፣ ሁላችንም ራሳችንን እንመርምር፡፡ ይቅርታ እንዴት ፍቅርንና ሰላምን እንደሚያመጣ ከሰሞኑ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትን መረዳት እንችላለን፡፡ የመሪዎቹን እንኳን ብንተው የሁለቱም ሕዝቦች መንፈስ ባለፈው ሁኔታ የመቆጨትን፣ በዛሬው ሁኔታቸው የመፀፀትንና የወደፊት አንድነትን በግልጽ ከግንባራቸው ሳይሆን ከውሳጣቸው ማንበብ ይቻላል፡፡

መሪዎቹም በተለይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በነበረው የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ ኃይል ውስጥ የመሪውን ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ስለሆነ፣ የሁለቱም ሕዝቦች ሁኔታ ልባቸውን በጥልቀት የነካቸውና ከሒደቱ የተማሩ ይመስላል፡፡ የሰሞኑን የኢትዮጵያና የኤርትራን ሁኔታ ስናይ እውነት እነዚህ ሕዝቦች ናቸው ላለፉት 50 ዓመታት ጎራ ለይተው ሲጨፋጨፉ የነበሩት? በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የባከነው? ይኼ ስሜት በውስጣቸው ባሉት አረጋውያን፣ ወጣቶችና ሕፃናት መሀል ነው? ቀደም ሲል ነገሩ ሁሉ እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ እንደ ዶ/ር ዓብይ ይኼን ኃላፊነት ወስዶ ሰላም የሚያወርድ መሪ ቢኖረን ኖሮ ነገሮች እዚህ ደረጃ ላይ አይደርሱም የሚል ስሜት አያጭርብንም? እስኪ ነገሩን በሌላ በኩል እንየው፡፡

በሁለቱም አገሮች በኩል ለዚህ ጦርነት የዋለውን ሀብትና የሰው ኃይል አንድ ላይ ደምረን አሁን አስመራና አዲስ አበባ ላይ በታየው የአንድነት መንፈስ ተዋህደን ብንቆም ኖሮ፣ ከፊታችን የሚቆም ጠላት ይኖራል ተብሎ ይታመናል? ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከመቶ ዓመት በፊት ነው የመደመር ጥቅም የገባቸው፡፡ ምኒልክ ወደ ዕድሜያቸው መጨረሻ አካባቢ ታመው አልጋ እንደያዙ ባደረጉት ኑዛዜ የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ‹‹. . . እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካልተላቀቃችሁ በቀር አገራችን ለሌላ ባዕድ አትሰጥም፡፡ ክፉ ነገር አገራችንን አያገኘውም፡፡ ንፋስ እንዳይገባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፡፡ ወንድሜ ወንድሜ ተባባሉ. . .›› የሚል ነበረበት፡፡ በኑዛዜያቸው ውስጥ ከሳቸው በፊት የነበሩ ባለመስማማታቸው በአገሪቱ ላይ የደረሰውንም የመተላለቅ ታሪክ ዘርዝረዋል፡፡

ይህ ኑዛዜ የተደረገው ከመቶ ዓመት በፊት ግንቦት 3 ቀን 1903 ዓ.ም. ነው፡፡ ዛሬ ዶ/ር ዓብይ እየነገሩን ያለው የመደመር ፍልስፍናም ይኼው ነው፡፡ ልዩነቱ የምኒልክ ኑዛዜ በጃንሜዳ ለተሰበሰቡ ሲሆን፣ የዶ/ር ዓብይ መስቀል አደባባይ መሆኑ ነው፡፡ የሚገመርመው ነገር ከመቶ ዓመት በፊት የተደረገው ኑዛዜ ወይም አደራ እስከ ዛሬ ለምንድነው ሳይፈጸም የቀረውና እንደ አዲስ ዛሬም ያው ነገር የሚነገረው? ለሰላማችን፣ ለአንድነታችንና ለፍቅራችን ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ለምን እስከ ዛሬ ሳይገባን ቀረ? የአንድ ወቅት መተላለቅ እንዴት ለሌላ ጊዜ ትምህርት ሳይሆነን ቀርቶ ነው መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር የምንጨራረሰው? ምናልባት ፈጣሪ ተቀይሞን ክፉ መሪዎችን ብቻ እየሰጠን ነው? ወይስ እሱ የተቀየማቸውን ሰዎች እያሾሙብን ነው?

በእርግጥ መሪዎቻችን አገር ለማዳን ተዋግተዋል፡፡ ክፉና ጨካኞች ግን ነበሩ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ጎጃምና ሸዋን፣ አፄ ዮሐንስ ወሎና ጎጃምን፣ አፄ ምኒልክ የደቡብ ክፍል፣ ደርግ በመላ አገሪቱ ላይ የፈጸሙትን ብንመረምር ብዙ ጥራዝ የሚወጣው የመከራ  ታሪክ ነው፡፡ ይኼ የግፍ ታሪክ እስከ ዛሬ ቀጥሎ በሕግ ጥላ ሥር ያለ ዜጋ አካሉ ከጎደለ፣ ከተዋረደ፣ ከተገረፈና ከሞተ ምን መንግሥት አለን? ስለዚህ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ጊዜ ወዶና ፈቅዶ መሪውን ለመደገፍ ያልሞከረው፡፡

የአዲስ አበባ ሕዝብ ለመጀመርያ ጊዜ ነው አስቦበትና በራሱ ተነሳሽነት መሪውን ለመደገፍ በሙሉ ስሜት አደባባይ የወጣው፡፡ ማንም መንግሥት ቢሆን በአስተዳደሩ ብዙ ሰው ደስ አሰኘሁ ብሎ ከማሰብ የበለጠ ደስታ የለውም፡፡ በኤርትራና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቤተሰቦች ለመገናኘት ቢፈልጉ፣ በአዲስ አበባ ዙረው በሱዳን አድርገው መሆኑን አንድ የአካባቢው ነዋሪ በቴሌቪዥን ሲገልጽ የሰማች ወጣት፣ ዶ/ር ዓብይ ይኼንን ብቻ እንኳን ሠርቶ ከሥልጣን ቢወርድ ይቆጨዋል? ስትል በተመስጦ ስትናገር ሰምቻለሁ፡፡ ጥሩ ታዝባለች፡፡ በአካባቢው የነበረውንም ጭቆና በሚገባ ያስረዳል፡፡ ከአሁን በኋላ አንድ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር ዞሮ ለመሄድ፣ የጥቂት ደቂቃዎችን መንገድ ለቀናት የሚያስረዝም መሪ እንኳ ቢኖር ፈቃደኛ የሚሆን ሕዝብ ከተገኘ እስከ ዛሬ በዓለም ላይ የሌለ ተሞክሮ ለዓለም እናቆያለን፡፡ የእነ ዶ/ር ዓብይ ተነሳሽነት እንዲህ ነው የሚገርመው፡፡

እንዲህ ያሉ መሪዎች የራሳቸውንም ሆነ የሕዝብን ተስፋና ደኅንነት፣ የአገሪቱንም ክብር አስጠብቀው የመጓዝ ግዴታ አለባቸው፡፡ በሕዝብ ዘንድ ዕውቅና በጨመረ ቁጥር ለአደጋ የመጋለጥ ዕድል ይሰፋል፡፡ ሁልጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ልናልፈው የማይገባን፣ ካለፍነው ግን አደጋን የሚያስከትል ወሰን አለ፡፡ ያ ወሰን የግድ መከበር አለበት፡፡ በመሪዎች ደረጃ ያን የአደጋ ወሰን እንዳያልፉ የሚያደርጋቸው አንዱና ዋናው የፕሮቶኮል ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የፕሮቶኮል ሥነ ሥርዓት አንዳንዶችን እንደምናስበው ሁኔታዎችን የማካበድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለመሪው ልዩ ክብር ተብሎ የተፈጠረ ሥነ ሥርዓትም አይደለም፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት ውስጥ የመሪውንና የእንግዶቹን ደኅንነት መጠበቅ፣ ሥራን በተገቢው ሁኔታ ለማሳለጥ ጊዜንና ጉልበትን በተወሰነው ፕሮግራም መጠቀምን ይጨምራል፡፡ በአጠቃላይ ሥነ ሥርዓቱ ከቀይ ምንጣፍ አጠቃቀም ጀምሮ እንግዶቹን እንደየደረጃቸው የምንቀበልበትን፣ የምናስተናግድበትንና የምንቀርብበትን የፕሮግራም አፈጻጸሙን ሁሉ ይወስናል፡፡ መሪዎች በሚፈልጉት ጊዜ የሚፈቀዱትን ጉዳይ በሚመስላቸው መንገድ እንዳይፈጽሙ የሚደረገው ለመሪዎቹ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ አገርን የሚመራ ሰው የሚናገረውም ሆነ የሚፈጽመው ተግባር በአገሪቱ ፖለቲካና ክብር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስላለው ነው፡፡ እንግዲህ ሥልጣንን ጨምሮ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሲደረስ መብታችንም የሚቀነስ መሆኑን አንርሳ፡፡

መንግሥትን ምልዓተ ሕዝቡ ደግፎታል ማለት የሚቃወመውና የሚጠላው የለም ማለት አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ በየትም አገር ያለ ነው፡፡ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስተት የሚያሳየንም ይህንኑ ነው፡፡ ጋንዲና ኬኔዲን የመሳሰሉ ንፁኃን ተወዳጅ መሪዎችም የዚህ ዓይነቱ የጥላቻ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሥራቸው አጋጣሚ የሚያገኙትን ማንኛውንም ሰው ቤተሰባዊ በሆነ መንገድ ለመቅረብ ስለሚፈልጉ፣ መሪነታቸው የሚጥልባቸውን ገደብ ለቁብ የሚቆጥሩት አይመስልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን ለመምራት በቂ ዕውቀት፣ ፍላጎትና ተነሳሽነት አላቸው፡፡ አሁን ያሉበትን የርዕሰ ብሔር ኃላፊነት ለመከወን እንዲያስችላቸው እሳቸው በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ከፍተኛ የሕዝብና የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አገርን መምራት የሚቻለው በፍቅርና በምሕረት ቢሆን ተመራጭና ጥሩው መንገድ ነው፡፡

የዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታና የፍጡራን ባህሪ ግን የግድ ከዚህ መርህ ውስጥ እንድንወጣ የሚያስገድደን ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ፍቅር ሁሉን ነገር እንደሚያሸንፍ ምሕረት ማድረግ የዕለት ተግባራችን እንዲሆን ዓለምን ያስተማረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን እሱ ያስተማራቸው ሰዎች በመሆናቸው ከሰው ባህሪ በሚመነጭ ተንኮል እሱኑ ገድለውታል፡፡ ይኼ እኛ እንድማርበት የተፈጸመ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ይቺን ዓለም ለመምራት ከፍቅር በተጨማሪ ሥልትና በትር አስፈላጊና በሁሉም አገሮች ከፍተኛ የፀጥታ ኃይልና መከላከያ አስፈለገ፡፡ ይኼ ኃይል በአገሮች መካከል ለሚደረጉ ግንኙነቶችም ገዥ ሆነ፡፡ በዚህም ተደግፈው ሁሉም አገሮች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩበት አንዱ ዋና መንገድ ሆነ፡፡ ሕዝብ የወደደው መንግሥት እንዲፀናና ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝ ከጎረቤቶቻችን ጋር የምናደርገው ግንኙነት መጠናከር አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ግን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የየአገሮቹን መንግሥትና ሕዝብ ባህሪም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ያልተረጋጋና የተወሳሰበ በመሆኑ፣ የመንግሥታችን አካሄድ ሁልጊዜ ያለፉትን ሁኔታዎች በጥልቀት በመመርመር ዳግም ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ በመጀመርያ መጤን አለበት፡፡ በጎረቤት አገሮች መካከል ባለው ያለመግባባት እኛ ወደ አንዱ የምንጠጋው የተቃዋሚውን መንፈስ ከግምት አስገብተን፣ የግንኙነታችንን ልክ ሚዛናዊ አድርገን መሆን አለበት፡፡ ሁሉንም ማስደሰት ባይቻልም የሚወሰደው አቋምና ስምምነት ሌላውን እንዳይጎዳና እንዳያስኮርፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ጉልህ ጥቅም የምናገኝበትን፣ ኢኮኖሚያችንና ትልልቅ ፕሮጀክቶች ዋስትና እንዲኖራቸው በማድረግ የግንኙነቶቻችንን ልክ መገደብና ማስፋት አለብን፡፡ በኢሕአዴግና በሻዕቢያ በእኩልነት ላይ ባልተመሠረተ ግንኙነት የከፈልነውን ዋጋ መርሳት የለብንም፡፡ ዛሬ ከማንኛውም የጎረቤት አገሮች ጋር በምናደርገው ግንኙነት የምንፈጽመው ስምምነት ከአገራችን ጥቅም አንፃር ብቻ እየተቃኘ መሆን አለበት፡፡

የኤርትራንና የኢትዮጵያን አዲሱን ግንኙነት ስናይ ለሁለቱም አገሮች ሰላም እንዲወርድ መደረጉ ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ኤርትራ ከጦርነቱ ጊዜ ጀምሮ ስትታገልለት የኖረችውን ሁለት ጥቅሞች አስከብራለች፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበላችንና በኢትዮጵያ ጎትጓችነት እንዲጣልባት የተደረገው ማዕቀብ እንዲነሳላት መጠየቃችን የኤርትራ ጥቅም ሁነኛ ምሰሶዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቅሞች አገሪቱን ቀስፎ ከያዛት የኢኮኖሚና የፖለቲካ አጣብቂኝ የሚገላግሏት ናቸው፡፡ በእኛ በኩል አገኘን የምንለው በውል የታወቀና የታሰረ ነገር አልሰማንም፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በየትም ዓለም እንደተለመደው በጉብኝታቸው መጨረሻ እንኳ ጋዜጣዊ መግለጫ አልሰጡም፡፡ በተደረጉላቸው ግብዣዎች ላይ የሰጡዋቸው መግለጫዎች ሕዝቡ ያደረገላቸውን አቀባበል በድፍን ከማመሥገን በስተቀር፣ በእኛ በኩል ሲነገር እንደነበረው ፍንጭ የሚሰጡ ጥቅሞችን አላነሱም፡፡ በእኛ በኩል ያለንን ሁሉ ሰጥተን ሳንጨርስ የሚሰጠንንም ማወቅ ግዴታችን ነው፡፡ መንግሥት ለመግለጽ ያልፈለገው ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ለአሰብ መንገድ አስቸኳይ ጥገና መደረጉ፣ የባህር ኃይላችን የማገገም ጉዳይ ሹክ መባሉ ሁሉ እሳት በሌበት ጭስ አይኖርምና ስምምነቱን ለማወቅ ጓጉተናል፡፡ ይኼ ግምት የሚመነጨው ጉዳዮች በውይይት ላይ ስለተነሱ ብቻ ማሰሪያ ሳይደረግላቸው፣ መንግሥት የማያስፈልግ ወጪና ድካም ውስጥ ይገባል የሚል እምነት ስለሌለ ነው፡፡

አዲሱ የዶ/ር ዓብይ መንግሥት የውጭ መሪዎችን በኦፊሴል ተቀብሎ ሲያስተናግድ ይህ የመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅግ የተሳካ ነው፡፡ ትምህርትም የሚገኝበት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ደማቁ አቀባበል ሲከናወን ከመጀመርያው ቀን ጀምሮ የታዩትን የፕሮቶኮል ግድፈቶች፣ በተለይም በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው መስተንግዶ አጠያየቂ የነበሩ ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ከዚህ ልምድ በመነሳት ወደፊት ቢስተካከል ጥሩ ነው፡፡

ምንም እንኳን በሕዝብና በመንግሥት መናበብ አገሪቱ ከአደጋ እየራቀች ነው ብንልም፣ አሁንም ተግዳሮቶች ስላሉ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ሁከትና ያለመረጋጋት በሁለቱ ክልሎች መሀል በሚደረግ ውይይት መግባባት ይፈጠራል ተብሎ የተኬደበት ቢሆንም፣ ሁኔታው የመሻሻል ምልክት እንኳ ባለማሳየቱ የግድ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት መፈለጉ ስለማይቀር መንግሥት አሁኑኑ የማስተካከያ ሥራ ቢሠራ ተመራጭ ነው፡፡ ያለበለዚያ ውላ ካደረች የማትቆረጠመዋን ባቄላን ታሪክ ያስከትላል፡፡

ሌላው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ያለመግባባት ከመንግሥት አመራርነት የተለዩ አባላት ያሉበት ሁኔታ በውል ያለመታወቁ ነው፡፡ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነት መቀበሉን ሲገልጽ ይህ ውሳኔ የትግራይን ክልል ሕዝብ መብትና ጥቅም ይነካል በሚል መነሻ ቅሬታዎች መኖራቸው እየተሰማ ነው፡፡ ይኼ የመንግሥታችን አወቃቀር የፈጠረው ጣጣ በመሆኑ የአካባቢውን ሕዝብ ምቾት ቢነሳ አይገርምም፡፡ የትግራይ ሕዝብ በክልሉ ላይ የሚመጣው ማንኛውም አደጋ የራሱ ችግር ብቻ አድርጎ ማየት የለበትም፡፡ የትግራይ ዳር ድንበር የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ነው፡፡ በአካባቢው ላይ የውጭ ወረራ ጭምር በተደጋጋሚ ተካሂዶበታል፡፡ በዓድዋ፣ በተንቤን፣ በማይጨው፣ ወዘተ. ትግራይ ውስጥ የተካሄዱት ሁሉም ጦርነቶች ከሁሉም ቦታ በተወጣጡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንጂ በትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ እስካመንን ድረስ ወደፊትም የሚሆነው ይኼው ነው፡፡ ዳር አገር ከሌለ መሀል አገር ዳር እንደሚሆን ለሁላችንም አይጠፋንም፡፡

ነባር የኢሕአዴግ ታጋዮችም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት ከነበሩበት ኃላፊነት ቢነሱ ምንም የሚያስከፋ ነገር የሌለ በመሆኑ መቀበል ግዴታ ነው፡፡ በጡረታ መገለል፣ ከሥልጣን መሻር፣ መታሰርና መሞት ጭምር በራስ ላይ ሲደርስ ይከብዳል እንጂ ከዚህ ባነሰ ወይም ያለምንም ጥፋት የታሰሩ፣ የተሰደዱና የሞቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ማንም ሹም ቢሆን በዕድሜው የመጨረሻ አካባቢ የሚያስደስተው ነገር ቢኖር በክፉ ጊዜ የሠራው መልካም ሥራ ስለሆነ፣ እናንተም በዚህ እየተፅናናችሁ ወደ መደመር ብትመለሱ ለመላው አገሪቱም ሆነ ለእናንተ የተሻለ ነው፡፡ በተረፈ የፌስቡክ አርበኞችን ችላ ማለት ነው፡፡ መንግሥትም ከእነዚህ ሰዎች ጋር የጋራ መድረክ ፈጥሮ እስካሁን እየተጓዘበት ባለው የይቅርታና የፍቅር ጎዳና ወደ መደመር ቢመልሳቸው ጥሩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...