Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ግብርና ግራና ቀኞች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ላይ የተመሠረቱ የኢንዱስትሪ ልማት ግቦችን ለዘመናት ስትተገብር ቆይታለች፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም ሆነ የቀደሙቱ መንግሥታት ለግብርና የሰጡት ትኩረት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ሚናና አስተዋፅኦ የተገነዘበ ቢመስልም፣ እንደየመንግሥታቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ የተለያየ አካሄድ ይታይ ነበር፡፡ ግብርና መር ይባል የነበረው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቢሸጋገርም ግብርናውም ኢንዱስትሪውም በሚፈለገው ደረጃ ፈቅ አላሉም፡፡ ይህን የተገነዘበው መንግሥት አደጋ መጋረጡን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ግብርናው ሀብት ሊያመነጭ ቀርቶ ሕዝቡን መግቦ ማደር እየተሳነው በመሆኑ ምክንያት አምራችነቱ ላይ፣ የሕዝብን የምግብ ፍላጎት መሸፈን ብቻም ሳይሆን፣ የኢንዱስትሪውን የግብዓት ፍላጎት ማሟላቱ ላይ ተዳክሞ ስለሚገኝበት ምክንያት በርካታ ምሁራን የየራሳቸውን ግምገማና ድምዳሜ ያስቀምጣሉ፡፡ መንግሥትም የሚለው አላጣም፡፡ በአሁን ወቅት ስለሚታየው የግብርና ዘርፍ ችግሮችና ምሁራን ስለሚሰነዝሯቸው ሐሳቦች ከመነጋገራችን በፊት ቀደምት ታሪኮችን እንቃኝ፡፡

የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት የአሁኗ ሩስያ ሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ በማረስ ከፍተኛ የግብርና ውጤት እንዳገኘችበት ስለሚነገርለትና የድንግል መሬቶች ዘመቻ ወይም ‹‹ዘ ቨርጂን ላንድስ ካምፔይን›› ስለሚባለው ግዙፍ የእርሻ ልማት አብዮት፣ የቀድሞው የሩስያ ፕሬዚዳንት ሊዮኔድ ኢሌዩች ብሬዥኔቭ በዘመቻው ስያሜ ‹‹ዘ ቨርጂን ላንድስ›› የሚል መጽሐፍ ጽፈው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ እ.ኤ.አ. በ1978 በጻፉት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ ከ20 ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተጉዘው፣ ያልተነኩና ያልታረሱ ድንግል እንዲሁም የተተው መሬቶችን በማረስ፣ እርሻዎችን በማስፋፋት የያኔዋን የሶቪዬት ኅብረትን የምግብ ሰብል እጥረት ለመቅረፍ የምትችልበትን መንገድ እንዲያስፈጽሙ የተደረገበትን ታሪክ ይዘክራሉ፡፡ ትንሿ መጽሐፋቸው ከ40 ዓመታት በኋላ ቆይታም በአማዞን ድረ ገጽ ሽያጭ ላይ ትገኛለች፡፡ በበርካታ ቋንቋችዎች ተተርጉማ በሽያጭ ላይ ትገኛለች፡፡

ብሬዥኔቭ በጉልምስናቸው ወቅት ያልተነኩ የሩስያ መሬቶችን በእርሻ እንዲያጥለቀልቁ ከተመደቡባቸው ግዛቶች መካከል በካዛኪስታን ሪፐብሊክ፣ የአሁኗ ራሷን የቻለች አገር በሆነችው ካዛኪስታን፣ ውስጥ ያከናወኑት የሁለት ዓመት ተግባር በመጽሐፋቸው ሰፊውን የትረካ ድርሻ ይዟል፡፡ የካዛክን ሰሜናዊ ክፍልን በእርሻ ማሳያዎች ለማጥለቅለቅ የዘመተው የሶቪዬት ወጣት፣ 250 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም ታላቋ ብሪታኒያን በሙሉ የሚሸፍን መሬት ወደ እርሻነት እንዲቀይር ይጠበቅ ነበር፡፡ አሳክቶታልም፡፡

በመላው ሩስያ እ.ኤ.አ. ከ1954 እስከ 1955 ባለው ጊዜ ውስጥ ከታረሰው አዳዲስ የእርሻ መሬት ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው በካዛኪስታን ግዛት እንደነበር የሚያወሱት ብሬዥኔቭ፣ በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ለእርሻ ሥራ ከተዘጋጀው 42 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 25 ሚሊዮን ሔክታሩ በካዛኪስታን ግዛት ውስጥ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ሶቪዬት ኅብረት ወደ መጠነ ሰፊ የእርሻ ማስፋፊያ ዘመቻ ከማምራቷ በፊት፣ እ.ኤ.አ. በ1953 31 ሚሊዮን ቶን እህል ይመረት ነበር፡፡ ሆኖም የምግብ እህል ፍጆታዋ 32 ሚሊዮን ቶን ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ብሬዥኔቭ በጠቀሱት አኃዝ መሠረት ነው፡፡

ይሁንና የአገሪቱን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ በወቅቱ የሶቪዬት ፕሬዚዳንት ኒኪታ ክሩሽቼቭ አመራር ፀድቆ ወደ ተግባር ለገባው ዕቅድ መተግበሪያ፣ በአራት ዓመታት ውስጥ 30 ሚሊዮን ሩብል ወይም በአሁኑ ምንዛሪ ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብታወጣም፣ ከ7.6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ48.8 ቢሊዮን ሩብል በላይ ግምት ያለው የምግብ ሰብል ማምረት መቻሏን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ምንም እንኳ ያልታረሱና ያልተነኩ መሬቶችን በሰፊው የማልማቱ ዕርምጃ ከጅምሩ በሶቪዬት ፖለቲከኞችና ምሁራን ዘንድ ትችት ቢሰነዘርበትም፣ ክሩሽቼቭም ሆኑ ብሬዥነቭን የመሳሰሉ ደጋፊዎቻቸው ዕቅዱን ለማስፈጸም ተፍ ተፍ በማለት የአገሪቱን የምግብ እህል እጥረት ለመቅረፍ በቅተዋል፡፡ አካሄዱ ግን በክፉም በበጎም ዛሬም ድረስ ይነሳል፡፡ በትንሹ ከ300 ሺሕ በላይ ወጣቶች የእርሻ ልማት ማስፋፊያ በሚካሄድባቸው ክልሎችና ግዛቶች ተሰማርተዋል፡፡ የወጣቶቹ ከወታደራዊ ተልዕኮ ያልተናነሰ ዘመቻ አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ሆኖም ዘመቻው በርካቶችን ለሞት ዳርጓል፡፡ በርካቶችንም ለከፋ ውድቀት አብቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሩስያ ታላቋ ሩስያ የሆነችበትን ትልቅ ዕርምጃና ውጤቷን አመላክቷል፡፡ እንደ አገር የማይቻለውን የሚችልና ለድል የሚተጋ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር መሆኗን ያሳየችበት የታሪክ ምዕራፍ ስለመሆኑ ብሬዥኔቭ በኩራት ጽፈዋል፡፡ 

የሶቪዬት ኅብረትና የኢትዮጵያ ውዳጅት

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ ስለአገራቸው የእርሻ ስኬቶች ብቻም ሳይሆን፣ ስለአገራቸው ሕዝብ ታላቅ ተጋድሎ ባወሱበት ክታብ፣ ከጠቀሱት ውስጥ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ትራክተርና ኮምባይነር ማግኘት ከባድ በነበረበት ወቅት እንኳ፣ ዶማና አካፋ በመያዝ በርካታ መሬት በማረስ ሰብል ማምረታቸውን ይተርካሉ፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ታርሶ የተመረተው ምርት ከሚጠበቀው በላይ ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ ምርቱን ከማሳ ሰብስቦ ወደ ፋብሪካ ለመውሰድ ፈታኝ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም በሰው ጫንቃና በእንስሳት ሸክም ወደ መኪኖች እየተጫነ ምርቱን ወደሚፈለግበት መውሰድ ግዴታ ስለነበረበት ሁኔታም አስታውሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ ስለአገራቸው የእርሻ ልማት ብቻ አልነበረም የሚታወሱት፡፡ እሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩትበት ወቅት በኢትዮጵያም የደርግ መንግሥትን የሚመሩት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወዳጅ እንደነበሩም የሚዘክሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ጋዜጠኛዋ ሜቼላ ሮንግ ስለሁለቱ የኮሚዩኒስት መሪዎች ግንኙነት ‹‹አይ ዲድንት ዱ ኢት ፎር ዩ›› በተሰኘውና በአብዛኛው ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ በሚተርከው መጽሐፏ የጠቀሰችው ታሪክ ይገኝበታል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ብሬዥኔቭን ‹‹እንደ አባቴ የማየው ወዳጄ›› እንደሚሏቸውና ብሬዥኔቭም ከአፍሪካ መሪዎች ምሳሌ የሚያደርጓቸው የልብ ወዳጃቸው እንደሆኑ የተናገሩትን በመጽሐፏ አስፍራለች፡፡

የሁለቱ ርዕሰ ብሔሮች የግል ግንኙነት ብቻም ሳይሆን፣ የየአገሮቹን ግንኙነት በምትጠቅስበት ምዕራፍም ሶቪዬት ኅብረት፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ምሳሌና ሞዴሏ ለማድረግ የነበራትን ጉጉት ትተርካለች፡፡ አገሪቱ ለኢትዮጵያ በየዓመቱ ስትመድብ በነበረው ገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ኃይል ሆና እንድትወጣ፣ በዚህም የሶቪዬት ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ከካፒታሊዝም የሚልቅበት ጉልበቱን በአፍሪካ የማሳየት ፍላጎት እንደነበራት ጋዜጠኛዋ ትተነትናለች፡፡ በየጊዜው እያደገ ሄዶ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰው የገንዘብ ድጋፍ ግን፣ ለኢኮኖሚ ልማት ከመዋል ይልቅ ለጦርነት መማገዱ የኋላ ኋላ ሶቪዬቶችን እንዳላስደሰታቸው ተጽፏል፡፡

ግብርናችንና የሶቪዬት የእርሻ ዘመቻ

ከሶቪዬቶች ግዙፉ የእርሻ ዘመቻ ትይዩ በኢትዮጵያም በሜካናይዜሽን የታገዘ የሰፋፊ እርሻዎች ፕሮግራም ዳዴ ማለት ጀምሮ ነበር፡፡ የዚህ ሥራ ጅማሮን በሚመለከት የወቅቱን ሁኔታ የሚዘግቡ ድርሳናት እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለመጀመርያ ጊዜ የምግብ እህል ከውጭ ገዝታ ማስገባት የጀመረችበት ወቅት ነበር፡፡ በእርሻው መስክ የአገሪቱን የምግብ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በማሰብ የጭላሎ ግብርና ልማት ቡድን፣ የአርሲ ግብርና ልማት ቡድን፣ የወላይታ ግብርና ልማት ቡድንና ሌሎችም ዘመናዊ የግብርና ፕሮግራሞች ብቅ አሉ፡፡

እነዚህ ፕሮግራሞች ግን የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይህም ሆኖ በአርሲ አካባቢ የተጀመረው ሥራ መጠነኛ ውጤት እንዳሳየና ዛሬም ድረስ በአካባቢው የሚታየው የግብርና ሥራ በሜካናይዜሽን የተቃኘ የመሆኑ ምሥጢር መነሻው በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት የተጠነሰሱት እነዚህ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎች ያመጡት ተፅዕኖ እንደነበር ከሚጠቅሱት ምሁራን መካከል ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ይጠቀሳሉ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው (ዶ/ር) በቅርቡ ባሳተሙትና ‹‹ኦቨርካሚንግ ኢትዮጵያን አግሪካልቸራል ኤንድ ፉድ ክራይሲስ›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ግብርና እጅጉን ኋላ ቀር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረግጠው ጠቅሰዋል፡፡

በመጽሐፉ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታም፣ ‹‹መጽሐፉን የጻፍኩት ከቁጭት በመነሳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ጥንት በኒዮሊቲክ ዘመን ከነበሩ አሠራሮች አኳያ ሲታይ ብዙም ለውጥ አለማሳየቱ ያስቆጫል፤›› በማለት ከ60 ዓመታት ቀደም ብሎ በአርሲ በተለይም እሳቸው ተወልደው ባደጉባት የዶሻ ቀበሌ ውስጥ ሕይወት ለነዋሪዎቿ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፣ በእነኚህ ዓመታት ውስጥም የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል፡፡

የአርሲ ገጠር ግብርና ልማት ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የመጀመያ ተጠቃሚዋ ዶሻ ቀበሌ እንደነበር የሚያብራሩት የግብርና አኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ቀበሌ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማግኘት ከቻሉ የዚያን ጊዜ አካባቢዎች የመጀመያዋ ልትባል እንደምትችልም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ ተደርጎም የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት አልተሻሻለም፡፡ ጥሩ የኑሮ ደረጃ ስለሚባለውና የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት ከነበረው በምንም መልኩ ለምን እንዳልተለወጠ እንመለከታለን፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪ ቤተሰቦች ብዛት በሦስት እጥፍ ጨምሯል ማለት ይቻላል፡፡ አካባቢው፣ የደኑ ይዞታ፣ የዱር እንስሳቱ በሙሉ ልጭ ብለው ጠፍተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመሬት እጥረት ትልቁና ዋናው ፈተና ነው፡፡ ወጣቶች ወደ ከተማ አካባቢ ለትምህርትና ለሥራ ፍለጋ ይሰደዳሉ፡፡ ነዋሪዎች የባንቧ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በማሳቸው ያመረቱትን በአህያ፣ በፈረስ ሲከፋም በትከሻቸው ተሸክመው ወደ ገበያ ቦታ ይዳሉ፡፡››

ምሁሩ ይኼንን ካነሱ በኋላም እንዲህ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያውያን ቁልፉ ጥያቄ የሚሆነው በእንዲህ ያለው ሁኔታ እስከመቼ እንቀጥለን? የሚለው ነው፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ መንደሮች አኳያ ስትታይ ዶሻ የምግብ እጥረት ላይታይባት ይችላል፡፡ ይህ በአወንታዊነት ሊታይ ቢችልም ድህነቱ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ሕዝቡ ወደ ዕርዳታ ተቀባይነት እያዘገመ መሆኑ ነው፡፡ የሰብል ምርት ችግር ውስጥ ከገባ ዶሻ የእህል ዕርዳታ መፈለጓ አይቀሬ ነው፤›› በማለት ሊመጣ ያለውን ሥጋት አመላክተዋል፡፡

እንደ ጌታቸው (ዶ/ር) ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ግብርና አሁንም ድረስ ከ10 ሺሕ ዓመታት በፊት በነበረ የእርሻ መሣሪያዎች የሚታገዝ፣ የበሬና የገበሬ ጉልበት የሚፋተጉበት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ዘርፍ መሆኑን ቀጥሏል፡፡

በ2007 ዓ.ም. እንዲሁም በ2009 ዓ.ም. ሁለት ዳጎስ ያሉ ሙያዊ መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁት ሌላው የግብርና ኢኮኖሚ ምሁር ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)ም ኢትዮጵያ ለገበሬዎቿ የሰጠችውን አነስተኛ ትኩረት ይተቻሉ፡፡ ገበሬው ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቆ፣ ያሻውን አምርቶ፣ ባሻው ጊዜ በገበያ ሸጦና ለውጦ ለመኖር የሚችልበትን አቅምና ዕድል አላገኘም የሚሉት ደምስ (ዶ/ር)፣ ገበሬው በግሉ እንደ ማንኛውም ነጋዴ ወይም አምራች አካል ከመታየት ይልቅ በግብርና ሥራው ላይ ያለመንግሥት ምንም ማድረግ የማይችል መደረጉን ይሞግታሉ፡፡ ማዳበሪያ ለማግኘት የመንግሥትን እጅ መጠበቅን ጨምሮ የኤክስቴሽን አገልግሎት ለማግኘት፣ ምርጥ ዘርና ሌላውንም አቅርቦት ለማግኘት የመንግሥት እጅ የሚጠብቅበት አሠራር መለወጥ እንዳለበትም ‹‹ዘ ኩዌስት ፎር ቼንጅ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲሁም 900 ገጾችን ባካተተው ‹‹ኢትዮጵያስ ኢንዲጂኒየስ ፖሊሲ ኤንድ ግሮውዝ፡ አግሪካልቸር፣ ፓስቶራል ኤንድ ሩራል ደቨሎፕመንት›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ሰፊ ሐተታዎችን እንዳቀረቡ ጠይቀሰዋል፡፡

ነገሮች እንዲህና እንዲያ ቢጠቀሱም፣ የአገሪቱ የምርት መጠን በዚህ ዓመት 300 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ይህ መጠን እ.ኤ.አ. ከ1954 በፊትም ስታመርተው ከነበረው ጋር እኩል ነው፡፡ ሩስያ የእርሻ ማስፋፊያ ዘመቻ ከመጀመሯ ቀድሞ 31 ሚሊዮን ቶን ታመርት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ለፍጆታ የሚውለው ግን 32 ሚሊዮን ቶን ስለነበር፣ ይኼንን ክፍተት መድፈን ብቻም ሳይሆን ለምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደልብ የሚበቃ የተትረፈረፈ የግብርና ምርት ማምረት ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነቱ አቅመ ግብርና አልበቃችም፡፡

አደጋም ሥጋትም ያጠሉበት ኢኮኖሚ?

የቀድሞው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከባልደረቦቻቸው ጋር የመሩት የምክክር መድረክ በአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ትግበራ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንኩ ገዥ እንደ ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣን ሳይሆን እንደ ተሰናባቹ ኮሚሽነር የመሩት ስብሰባ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የዕቅዱ አተገባበር ምን ይመስል እንደነበር ብቻም ሳይሆን ቀሪዎቹን ዓመታት በምን መልኩ መጓዝ አለበት የሚለው ትኩረት የተሰጠው የውይይት ነጥብ ነበር፡፡

በመድረኩ የ2007 ዓ.ም. መነሻ በማድረግ እስከ 2010 ግማሽ ዓመት ድረስ የነበረው የዕቅዱን ሒደት በስፋት ያቀረቡት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም (ዶ/ር) ነበሩ፡፡ በዕቅዱ የተዘረዘሩት አብዛኞቹ ግቦች በእስካሁኑ አካሄድ ከቀጠሉ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ መንገድ መቅረቱ አይቀሬ እንደሚሆን የሚያሳዩ አኃዞችን እያጣቀሱ አቅርበው እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ከ110 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ውስጥ 36 በመቶው መታረስ የሚችል መሬት እንደሆነ (እንደ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) አኃዝ እስከ 60 በመቶ የሚደርሰው መሬት ሊታረስ የሚችል ነው) መረጃዎችን አጣቅሰው የገለጹት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ሊታረስ ከሚችለው ከዚህን ያህል መሬት ውስጥ እስካሁን በኢትዮጵያ የታረሰው 16 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ግብርና መሠረታዊ ክለሳ ይፈልጋል፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ከሽፏል፡፡ ሁለተኛውም እንዳይከሽፍ የሚሠሩትን ሥራዎች ከወዲሁ እንያቸው፤›› በማለት ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ የኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ ዕቅድ ስለመስኖ እርሻ በሚገባ አለማቀዱ፣ ምን ያህል የአገሪቱ መሬት ለእርሻ ሥራ እንደሚውል በውል አለማስቀመጡም የዕቅዱ ክፍተቶች እንደሆኑም አውስተው ነበር፡፡

በአንድ ወቅት ሩስያና ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት እኩል ሊባል በሚችል የጊዜ ክልል ውስጥ የጀመሩት የሚካናይዝድና የተስፋፋ የግብርና ልማት በኢትዮጵያ በኩል በአቅም ማነስና በቴክሎጂ ዕጦት እንዲሁም እየተጋጋመ በመጣው የፖለቲካ ትኩሳት ከመንገድ ቀርቷል፡፡ እንደ ጌታቸው (ዶ/ር) ትውስታ፣ የኢትዮጵያ የሜካናይዜሽን ግብርና እንዳጀማመሩ ካልሄደባቸው ምክንያቶች አንዱ የንጉሠ ነገሥቱን ዙፋን የገረሰሰው የደርግ መንግሥት በ‹‹መሬት ላራሹ›› ሞገድ የግብርና መሬቶችን ከባላባቶች በመንጠቅ ለገበሬዎች ማከፋፈሉ ነው፡፡

ምንም እንኳ አካሄዱ ለሰፊው ጭሰኛ ገበሬ የመሬት ባለቤትነትን ማረጋገጡ ላይ ትልቅ ሚና ቢኖረውም፣ ምርትና ምርታማነትን ግን ሊያመጣው አልቻለም፡፡ የሩስያ መጠነ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍም ታክሎበት የኢትዮጵያ ግብርና ሕዝቡን የሚመግብበት አቅም አላገኘም፡፡ እንደውም የተፋፋመው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ጭርሱኑ ገበሬው ተረጋግቶ እንዳያርስ አስገድዶታል፡፡ የ1977 ዓ.ም. ድርቅ ሲጨመርበት የግብርና ዘርፍ የቁልቁለት ጉዞውን አፋጥኖታል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት መምጣት በኋላም ቢሆን ግብርና ከእንቅልፉ ለመንቃት ብዙ ባጅቷል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፉት 15 ዓመታት ለውጦች እየታዩ፣ ምርት እንደሚፈለገውም ባይሆን በየጊዜው ጨምሮ ነበር፡፡ ይሁንና አደጋ ማንዣበቡ እየተነገረ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ የሚጠበቅበትን ለውጥ ባለማምጣቱ፣ ምርት እንደሚጠበቀው ባለማደጉ፣ የወጪ ምርትና ገቢ በማሽቆልቆሉ ወዘተ. አደጋ ማንዣበቡን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢናገሩም፣ የግብርና ኢኮኖሚ ምሁሩ ደምስ (ዶ/ር) ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ በቅርቡ በሪፖርተር እንግሊዝኛው ጋዜጣ በወጣው ቃለ ምልልሳቸው ይኼንኑ አቋማቸውን አስፍረዋል፡፡ 

ኢኮኖሚው በጥሩ መንገድ እየሄደ ስለመሆኑ የሚሞግቱት ደምስ (ዶ/ር)፣ ወደፊት ሊያሰጉት የሚችሉ ችግሮች አሉበት ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢኮኖሚው በርካታ ችግሮችን እያለፈ መምጣቱንም ያስታውሳሉ፡፡ እንደ ደምስ (ዶ/ር)፣ ከሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተው ከፍተኛ መጠን ያለው ድርቅን ተቋቁሞ ማለፉ አንዱ የኢኮኖሚው አቋም መገለጫው ነው፡፡

በፍጆታ መጠን ከመንግሥትና ከግለሰብ ወጪዎች፣ ከሕዝብ አኗኗር አኳያ ሲታይ ኢኮኖሚው እንደ አቅሙ የሚችለው እያቀረበ ነው የሚሉት እኚህ ምሁር፣ ይህም ሲባል ግን ባለውና በሌለው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ የመምጣቱ ጉዳይ ላይ ሌላ ዕይታ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ኢኮኖሚው ችግር ያለበት የሥርጭት ችግር ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለው የፖሊሲ ዕርምጃ ደካማ ነው፤›› ያሉት ደምስ (ዶ/ር)፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌሎች መለኪያዎች ሲታይ ‹‹በጥሩ መንገድ እየሄደ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ ተብሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት አነስተኛ ሜካናይዜሽንን ለመተግበር ወዲያ ወዲህ ማለት ጀምሯል፡፡ ይህም ቢሆን እንደ ጃፓን ባሉ አገሮች ድጋፍና ምክር ሲሆን፣ በአነስተኛ መሬት፣ በተበጣጠሰ የእርሻ ማሳው የሚታትረውን ገበሬ የሚያግዙ የእርሻ መርጃ መሣሪያዎችና የመስኖ እርሻ በእንፉቅቅ ላይ ቢገኙም፣ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር በዚህ መስክ በሰፊው ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን ሚኒስትር ዴኤታው ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) ባገኙት መድረክ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

ዘርፉን ለቴክሎጂ ቅርብ በማድረግ፣ ገበሬውን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚፈለግ ይገለጻል፡፡ ይህ ሁሉ በሚባልበት በዛሬው ጊዜም ግን የሰፊው ገበሬ ጥያቄ ‹‹ምርጥ ዘር አጣሁ፣ ማዳበሪያ አጣሁ፤›› የሚል መሆኑም እየታየ ነው፡፡ እንዲህ ባለው አካሄድ የመንግሥት ዕቅድም የገበሬው ልፋትም ሳይገጣጠሙ ሌሎች አምስት ዓመታት፣ ሌሎች አሥርታት ማለፋቸው እንደማይቀር ሹማምንቱ በአደባባይ እያሳሰቡ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች