Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለዳያስፖራው የተጠረገው መንገድ ይታደስ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበትና በሹመታቸው ዕለት ካደረጉት ንግግር ጀምሮ፣ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን በተመለከተ ተስፋ ሰጪ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የፖለቲካ አለመግባባቶችን ያረገበውን ንግግራቸውን በተግባር ለመተጎርም የሚያስችል የፖለቲካ ሥራ ለመሥራትና በርካታ ኢትዮጵያንን በአሜሪካ ከተሞች እየተዘዋወሩ በማነጋገር ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ፣ በዳያስፖራውና በመንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነትና መተማመን፣ ዳያስፖራው ለአገሩ ማበርከት ስለሚችለው አስዋጽኦና የመሳሰሉት ነጥቦች የውይይት አጀንዳዎች እንደነበሩ ታይቷል፡፡ እንደሌላው ጊዜ ባለሥልጣን ወደ አሜሪካ በሄደ ቁጥር ማንጓጠጥና ማጥላላቱ ቀርቶ ኢትዮጵያውያን በስደት ሳሉ በፍቅር ሲጠባበቋቸውና ሲቀበሏቸው፣ በየንግግራቸው መካከል ድጋፋቸውን ሲገልጹላቸው የታየው ሁሉ መልካም የለውጥ መንገድ ስለመገንባቱ አመላካቾች ነበሩ፡፡  

በእነዚህ የምክክር መድረኮች ዳያስፖራው ለአገሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ምን መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይም መሠረታዊ አጀንዳ ነው፡፡ የዳያስፖራው አስፈላጊነትና በአገሪቱ ምድር በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት ዘርፎች ተሳታፊ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በአገር ውስጥ ሊስተካከሉ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው አይታበልም፡፡

አካሉም መንፈሱም በአገሩ አንድነትና በቀና አሳቢ መሪዎች የተነሳሳውን ስደተኛ ሕዝብ ለመልካም አስተዋጽኦ የሚያበረታ ሥራና ዝግጅት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ዳያስፖራውን የተመለከቱ ሕግጋትን መከለስ ያስፈልጋል፡፡ የበለጠ እንዲሳተፉ የሚያግዙ እንደ ጥምር ዜግነት ያሉ ጉዳዮችም መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ ለዳያስፖራው የተለየ ነገር ይደረግለት ማለትም ባይሆን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩላቸው ግን ይገባል፡፡ እትብታቸው የተቀበረበት አገር ነውና ስለአገራቸው ፍቅር ደፋ ቀና እንዲሉ ከተፈለገ፣ በአገር ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈንም ያስፈልጋል፡፡ ይህም የሚሆነው እነርሱ ለማስደሰትና ለእነሱ ብቻ ተብሎም ሳይሆን፣ አገር ላለውም ለሁሉም ወገን አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

ከኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አገሪቱ መጠቀም ያለባትን ያህል ልትጠቀም አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን መጠቀም በሚገባት መጠን አለመጠቀሟን በማመን፣ አላፈናፍን ያሉ ሕጎችና ልክ ያጣውን ቢሮክራሲ ማስተካከል ያሻል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ያልተመቻቹ ሁኔታዎች ዳያስፖራውን በሩቁ አስቀርተውት ቆይተዋል፡፡ አገር ቤት በመግባት የበኩላቸውን ለማዋጣት ሲጣጣሩ የሰነበቱት ስደተኞች፣ በሚረግጡት  የመንግሥት ቢሮ ሲገጥማቸው የቆየው መጉላላትና ውጣ ውረድ ለዚህች አገር ለመሥራት የነበራቸውን ሞራልና ተነሳሽነትን አዳፍኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከፖለቲካ ጋር የተያዙ አመለካከቶችና ሥጋቶች በትልውድ አገራቸውና ሠርተው፣ ጥረውና ተወዳድረው በሚኖሩባቸው አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት የትየለሌ በማድረግ መራራቅ ተፈጥሮ ማዶ ለማዶ በመናቆር ለመኖር አስገድዶ ቆይቷል፡፡ አሁን እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ አንፃር ግን፣ ሩቅ ቆሞ ከመናቆር ሰብሰብ ብሎ ስለአገር መምከር የተቻለበት ዕድል መገኘቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በርካታ ተስፋ ሰጭ ጉዳዮች እየታዩ መምጣታቸው ታይቷል፡፡ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩና በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች መካከል የሚደረሰው ስምምነት ምንም ይሁን ምን፣ ዳያስፖራው አገራዊ አሻራ እንዲኖረው ከተፈለገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ መልስ ለዳያስፖራው የማይመቹ ሕግጋት እንዲቀየሩ ማድረግ የመጀመርያ ሥራቸው መሆን አለበት፡፡ የጥላቻና የልዩነት ግንብ ይፍረስ ከተባለ ዳያስፖራውን ገድቦ የቆየው ግንብም ሊፈርስ ይገባል፡፡ መፍረስ ካለባቸው ደንቦች መካከል ደግሞ ዳያስፖራውን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተሳታፊ አትሁኑ ‹‹ድርሽ›› እንዳትሉ የሚለው ሕግ አንዱ ነው፡፡  

ምክንያቱም እነዚህን ዳያስፖራዎች በአገሪቱ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ በውጭ ምንዛሪ አክሲዮን ገዝተው ባለአክሲዮን እንዲሆኑ ማድረግ አሁን አገሪቱ ላለችበት ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዕገዛ እንዲደረጉ በመፈለግ ብቻ ሳይሆን የእነሱ መግባት የፋይናንስ ተቋሞቻችንም ጠንካራ እንዲሆኑ ስለሚያግዝ ነው፡፡

ዛሬ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚሆን ካፒታል ለማሰባሰብ ያለውን ፈተና ላየ እነሱን በውጭ ምንዛሪ ባለአክሲዮን ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ይህ አንዱ ጥቅም ሲሆን፣ ከዚህም በላይ አገር ሊጠቀም የሚችል መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ዕድል ይገኛል፡፡

በአሜሪካ ኢትዮጵያውያንን ያህል ዳያስፖራ የሌላቸው እንዲያውም አንድ ሦስተኛ እንኳን የሚያህል ዜጎች የሌላቸው ግብፅና ናይጄሪያ ከውጭ ሐዋላ ገቢ ብቻ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ሲታይ፣ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን በማራቃችን ምን ያህል እንደጎተተን ያመላክታል፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ውጭ ከሚኖሩ ናይጄሪያውያን በዓመት 16 ቢሊዮን ዶላር፣ ከግብፃውያንም 19 ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ሐዋላ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ (የውጭ ሐዋላ ገቢ አኃዛዊ መረጃዎች የተለያየ መጠን እንደሚያሳዩ ልብ ይባል) ይህ የውጭ ሐዋላ ገቢ በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥር አንፃር ሲታይ ኢምንት ነው፡፡

ይህም የሆነው ከዳያስፖራው ጋር የነበረው የተበላሸ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራው ለአገሩ በአግባቡ እንዳይጠቅም ታግዶ ቆይቷል ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ምሳሌ የምንወስደው ከውጭ ወደ አገር የሚገባው የዳያስፖራው ገንዘብ በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ከውጭ ወደ አገር የሚላከው ገንዘብ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከባንኮች ውጭ የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት ለመድፈን ከተፈለገም ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ሲልክ በመደበኛ ባንክ እንዲልክ የሚያበረታታ አሠራር መቀረፅ አለበት፡፡

ከኢንቨስትመንቱ ዶላር በባንክ እንዲላክ በማድረግ ባለፈ ደግሞ ዳያስፖራው እንደፈለገ የሚንቀሳቀሰው የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲኖረው ማድረግም ዳያስፖራው ለማበረታታት ያግዛል፡፡ ሁሉም ነገር ግን በሕግና በአግባብ መሆን እንዳለበት መረሳት ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንደሚሰማው በአንዳንድ አገሮች ዳያስፖራው ገንዘብን በውጭ ባንኮች ሲያስቀምጥ የሚከፈለው የወለድ ምጣኔ እጅግ አነስተኛ በመሆኑና የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ ምጣኔ ደግሞ የተሻለ በመሆኑ ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥ የሚችሉበት ዕድል ከተፈጠረ ለእነሱም ለአገርም ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም ዳያስፖራው ያስፈልጋል ከተባለ እንዲህ ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን መተግበር ያሻል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርም እንዲህ ያሉትን አዳዲስ አሠራሮች በቅጡ የተመለከተ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡  

ሌላው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ዳያስፖራው በአገሩ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማራ፣ ከሌሎች የውጭ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጋር በሚያመቸው መንገድ ለአገር በሚጠቅም ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ እንዲሰማራና ተነሳሽነት እንዲኖረው የሚያነሳሳና የሚጋብዝ አሠራር እንዲፈጠር፣ ኤምባሲዎቻችንም ለዚህ ብርቱ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቀልጣፋ ዲፕሎማቶችንም ለዚሁ ተግባር መመደብ ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት