Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ዴሞክራሲን የማጎልበት ጉዞ በኢትዮጵያ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  በፍሬዴሪክ ኤበርት ስትፊቱንግ ኢትዮጵያ ሐሙስ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የማጎልበት ጉዞ› በሚል ርዕስ አካሂዶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለማጎልበት ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ ባለሙያዎች ተሰንዝረው ነበር፡፡

  የተለያዩ ባለሙዎች ስብጥር በታየበት መድረክ ላይ ዴሞክራሲን ባህል ለማድረግና በኅብረተሰቡ ውስጥ ይሰርፅ ዘንድ ሊደረጉ ይገባቸዋል፣ ወይም ደግሞ ቢደረጉ መልካም ይሆናሉ የሚሉ የተለያዩ ሐሳቦች ከተለያዩ የኅብረተሰብና የሙያ ባለሙያዎች አንፃር ቀርበውበታል፡፡

  በመድረኩ ላይ ዴሞክራሲን ማጎልበት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የተለያዩ አማራጭ የመነሻ ሐሳቦች በተለያዩ አተያየቶች ያቀረቡት ግለሰቦች ስብጥርም፣ ጽንሰ ሐሳቡን ከተለያዩ ማዕዘናት ለመመልከት ዕድል የሚሰጡ ነበር፡፡

  በዚህም መሠረት በሴቶች መብት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት ወ/ሪት ብሌን ሳህሉ ዴሞክራሲን ለማጎልበት የሴቶች ተሳትፎና መካተት ስለሚኖረው ጠቀሜታ አጠቃላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ እነዚህን ነገሮች በቅጡ የሥርዓቱ አካል ለማድረግ ደግሞ የተለየ አተያይ ሊኖር እንደሚገባና በርካታ ማኅበረሰባዊ እሴቶች ተብለው የሚገለጹ ነገሮች መዳሰስ እንደሚኖርባቸው አውስተዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች መነሻ ሐሳብ ሰንዛሪዎች ማለትም መንበረ ፀሐይ ታደሰ (ዶ/ር)፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ቁምላቸው ዳኜና አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ከሙያቸውና ከሕይወት ተሞክሯቸው በመነሳት ምን ቢሠራ መልካም ሊሆን እንደሚችል በማውሳት ምልክታቸውን አጋርተዋል፡፡

  ምንም እንኳን እነዚህ ከላይ የተገለጹት ግለሰቦች ከተለያዩ ሙያዎች የሕይወት ክህሎትና ልምድ አንፃር ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማጎልበት ምን መሠራት ይኖርበታል? የሚለው ሰፊ ሐሳብ ላይ ምልከታቸውን ያቀረቡ ቢሆንም፣ ከእነሱ በፊት ግን አጠቃላይ ዴሞክራሲን የማጎልበት ሒደቶችን አስመልቶ በአቶ ዛዲግ አብርሃ አማካይነት የተለያዩ ጽሑፎችን መሠረት ያደረገ መነሻ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡

  አቶ ዛዲግ ለመነሻ በሰነዘሩት ሐሳብ እስካሁን ተለምዷዊ በሆነ መንገድ በተለያዩ ጽሑፎች በብዙዎች ዘንድ ዴሞክራሲን በተመለከተ ያለውን ‹‹ዴሞክራሲ የምዕራባውያን ባህል ነው›› የሚለውን አተያይ በመተቸትና በመቃወም ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡

  ‹‹በብዙ ሥነ ጽሑፎች እንደተመለከትነው ብዙዎቻችን ዴሞክራሲን የምዕራባውን ባህል አድርገን ነው የምንረዳው፡፡ በዚያ ምክንያት ሐሳቡን ውጫዊ የማድረግ ነገር አለው፤›› በማለት ያለውን ባህላዊ አተያይ በመተቸት፣ ‹‹በእኔ እምነት ዴሞክራሲ የሰው ልጅ በራሱ መንገድ ነገሮችን ሲመረምርና ለመረዳት ሲሞክር ያከማቸው ዕውቀትና ጥበብ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሐሳቡ ሁለንተናዊ እንጂ የአንድ አካል ወይም ማኀበረሰብ ውጤት አሊያም ንብረት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

  ስለሆነም እንደ አቶ ዛዲግ ገለጻ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያውያን፣ የቻይናውያን፣ የህንዶች፣ ወዘተ ጥበብና ዕውቀት ተደምሮበታል፡፡ ግሪካውያን ወይም ሮማውያን የፈጠሩት አለመሆኑንና፣ የመከማቸት ሒደት የፈጠረው ድምር ውጤት እንደሆነ ገልጸው፣ የዴሞክራሲን ሁለንተናዊነት አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

  ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ሐሳብ ደግሞ ዴሞክራሲን ለማፅናት፣ ዴሞክራሲን ፍፁም ውጫዊ ነገር አድርጎ መመልከት ስለማይገባ በእያንዳንዱ ማኀበረሰብ ውስጥ ያሉ ለዴሞክራሲ መጎልበት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ እሴቶችን መንከባከብ ተገቢ፣ እንዲሁም አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

  ዴሞክራሲን ከማጎልበት አንፃር የሚነሱ ተገዳዳሪ ሐሳቦችን በስፋት በዳሰሰው ገለጻቸው፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ በዋነኛነት የሚታዩት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን አውስተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዴሞክራሲን ከሽግግር ሒደት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲን ከማፅናት አንፃር ያሉ የተለያዩ ጽሑፎችን ዋቢ በማድረግ ገለጻ አድርገዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ዴሞክራሲ እንደ ሽግግር በሚታይበት ወቅት ወይም ሁኔታ ያሉ ኩነቶችን ዘርዝረዋል፡፡ የሽግግር ዴሞክራሲ የሚባለው ዴሞክራሲን መለማመድና ባህል ወደ ማድረግ የሚደረግ የሽግግር ጉዞ እንደሆነ ጠቁመው፣ በዚህም የሽግግር ወቅት ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት፣ ምርጫ የማከናወን ሒደትንና የመሳሰሉትን ዓበይት ሁኔታዎች እንደሚያካትትም ገልጸዋል፡፡

  በዚህ ደረጃ የተጀመረው የሽግግር ዴሞክራሲ መዳረሻ ዓላማውና ግቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትን መሠረት ያደረገ ነው በማለት፣ በዚህ ሥሌት መሠረት የሽግግር ዴሞክራሲን መጀመር ብቻ ሳይሆን የተጀመረው የሽግግር ዴሞክራሲ ረዥም ርቀት የሚጓዝበትን ሒደት የሚያረጋግጥም ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  ዴሞክራሲን ማፅናት ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ብቸኛው ወደ ፖለቲካ ሥርዓት መምጫና መሄጃ መንገድ መሆኑ ሲረጋገጥ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ‹‹በዚህም መሠረት ዴሞክራሲን ማፅናት የሚመጣው የሽግግር ዴሞክራሲን ከጨረስን በኋላ ነው፤›› ሲሉም በሁለቱ የዴሞክራሲ መገለጫዎች ላይ ያላቸውን ምልከታ አጋርተዋል፡፡

  ከዚህ ትንታኔ አንፃር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሽግግር ዴሞክራሲ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ‹‹አሁን ዋነኛው ጥያቄ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ እንዴት እናስኪደው? ወደኋላ እንዳይመለስ ነገር ግን ወደ ፊት ብቻ የሚገሰግስ ማድረግ እንዴት ይቻላል? የሚለው ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፤›› በማለት፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት እንዴት ይጠናከር የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ለተወያዮቹ ወርውረዋል፡፡

  ‹‹ይህ ጥያቄ ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ መልሶቹ ግን ውስብስብ ከመሆን ባለፈ በርካታ ጥያቄዎችን ይፈጥራሉ፤›› በማለት ዴሞክራሲን የማጎልበት ጥያቄ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ባለቤት እንደሆነ፣ ጥያቄውም መልስ ሳይሆን በርካታ ጥያቄዎች እንደሚወልድ ገልጸዋል፡፡

  ሆኖም ግን ጠያቂ ማኅበረሰብ መፈጠሩ ሒደቱን ከማጎልበት አንፃር እንደ አንድ ፀጋ የሚታይ መሆኑን በመጥቀስ፣ የተቋማት አለመጠናከር ደግሞ ዴሞክራሲን የማጎልበት ፈተና እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ዴሞክራሲን የማጎልበት ሒደት ውስጥ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ልዩነት ያላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በመግለጽ፣ ‹‹በሩን ከፍተን የምናስገባውና በሩን የምንጠረቅምበት ዜጋ ሊኖር አይገባም፤›› በማለት ዴሞክራሲን የማጎልበት ሒደቱ ላይ ሁሉም እንደየችሎታውና እንደ አቅሙ መሳተፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

  በተመሳሳይ ለመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት ወ/ሪት ብሌን ሳህሉ ደግሞ፣ ‹‹ዴሞክራሲን ለማጎልበት በሚደረገው ሒደት ላይ እነማን መካፈል አለባቸው የሚለውን ውሳኔ ስንወስን ውሳኔ የምንሰጥበት መንገድና አተያይ በቅጡ መቃኘት ይኖርበታል፤›› ሲሉ አውስተዋል፡፡

  ‹‹የሁላችንንም ሕይወት የሚነኩ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚሞክር ሥርዓት ብንገነባ ዴሞክራሲ ይጠነክራል፤›› ብለው የሚያምኑት ወ/ሪት ብሌን፣ ይህንንም ለማድረግ ሁሉንም ሊያስማማ ይችላል ያሉዋቸውን ጥያቄዎች ሰንዝረዋል፡፡

  በዚህም መሠረት፣ ‹‹መልካምና ፍትሐዊ የሆነ ማኅበረሰብ እንዴት አድርገን ነው የምንገነባው? እነ ማንን ያካትታል? ምን ዓይነት ጥያቄዎችን ይመልሳል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሁላችንንም የሚስማማን መስለኛል፤›› ሲሉም ዴሞክራሲን ለማጎልበት በመሠረታዊነት ሊነሱ ገባቸዋል ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

  ‹‹ከዚህ አንፃር ፍትሐዊ የሆነ ማኅበረሰብ ምን ዓይነት እሴቶች አሉት? ምን ዓይነት ተቋማትን ይገነባል? ምን ዓይነት ነገሮች ላይ ይደራደራል? ምን ዓይነት ነገሮችስ ላይ አይደራደርም? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የምንጓዝበት ሒደት ዴሞክራሲን ለማጎልበት ለሚደረገው ጉዞ ወሳኝ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

  ታዋቂው የሕግ ባለሙያና ምሁር መንበረ ፀሐይ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የዴሞክራሲና የአስተዳደር መስተጋብር ዴሞክራሲን ለማጎልበት ዋነኛው መነሻ መሆን እንዳለበት በመግለጽ፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ የጠንካራና የገለልተኛ ተቋማት መገንባት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአስተዳደር ፍትሕ ዴሞክራሲን ለማጎልበትም ሆነ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ግንባታውን ለማጠናከር ከፍተኛውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ሕግ የማውጣት ችግር እንደሌለ የገለጹት የሕግ ምሁሩ፣ ዋናው ጉዳይ የሚወጡትን ሕጎች ሊተገብሩ የሚችሉ ተቋማትን መገንባት ላይ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

  ‹‹በርካታ ተቋማት ተቋቁመዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ተቋማት ከማቋቋም አልፎ የተቋማቱን የሥልጣን ገደብ፣ የአሠራር ሒደት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከመሥራት አንፃር ብዙ የሚቀረን ይመስለኛል፤›› በማለት ሕጎቹን የሚደግፉ ዝርዝር የአስተዳደር ሕጎችና ጠንካራ ተቋማት ዴሞክራሲን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

  ‹‹መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መንግሥት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ በኅብረተሰቡም በኩል በጣም በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱ እንሰማለን፡፡ ችግሮቹ ግን አሁንም አሉ፡፡ እነዚህ በርካታ የማሻሻያ ዕርምጃዎች እንዳሉ ሆነው ለምንድነው ተቋማዊ የሆነ ገጽታችን ላይ ረዥምና ጎላ ያላ ለውጥ ልናመጣ ያልቻልነው የሚለውን ጥያቄ ልናየው ይገባል፤›› በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

  ጥያቄውን ከማቅረብ ባለፈ ግን የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት የተቋማትን ሥልጣን የሚገድብ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ ‹‹ተቋማት በአዋጅ ይመሠረታሉ፡፡ ከዚያ በኋላ መመርያ ወጥቶ ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ሥራው በሕግ በተሰጠው መጠን የተከናወነ መሆኑን የምናረጋግጥበት ማዕቀፍ የለንም፡፡ የአስተዳደር ሕግ አትኩሮት የተሰጠው አይመስለኝም፤›› ሲሉም ዴሞክራሲን  ለማጎልበትና ተቋማትን ጠንካራ ለማድረግ የአስተዳደር ሕግ የአገሪቱ የሕግ አካል እንዲሆን ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

  ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ብሔር ተኮር የሆነ ፖለቲካ እያራመዱ ስለዴሞክራሲ ማሰብ እንደሚከብድ ገልጸዋል፡፡

  ‹‹እስካሁን በመጣንበት መንገድ ዴሞክራሲ ላይ መድረስ እንደማንችልና ወደ መፍረስ አደጋ እንደምንደርስ ስንናገር ቆይተን ነበር፤›› በማለት የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በመተቸት የጀመሩት አቶ ልደቱ፣ ‹‹የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ችግር ብሔር ተኮር መሆኑ ላይ ነው፤›› ሲሉም ከብሔር ተኮር ፖለቲካ መውጣት ዴሞክራሲን ለማጎልበት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የመጀመርያው መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት ያካሄድነውን ዓይነት የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ ጥላቻና መከፋፈልን ይዘን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ ብሔረ ተኮር የሆነ ፖለቲካ አካሂደን ከዚህ የተለየ ውጤት እናመጣለን ማለት አይቻልም፤›› በማለት፣ ከሁሉም አስቀድሞ ከብሔር ተኮር ፖለቲካ መውጣት ጊዜ የሚሰጠው አጀንዳ እንዳልሆነ ሞግተዋል፡፡

  በዚህ መድረክ ላይ አቶ ቁምላቸው ዳኜ የሲቪል ማኅበረሰቡ ሚና ዴሞክራሲን ከማጎልበት አንፃር፣ እንዲሁም አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ዴሞክራሲን ከማጎልበት አንፃር በሚኖራቸው ሚና ላይ ያላቸውን አተያይ አካፍለዋል፡፡

  በዕለቱ የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በመሰንዘር የግማሽ ቀኑ የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -