ዘንድሮ ለ45ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ይከናወናል፡፡ በሻምፒዮናው ከሰባት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 551 ሴቶችና 756 ወንዶች የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ ይፎካከሩበታል ተብሏል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ተቋም (ብሔራዊ አንቲ ዶፒንግ ኦርጋኔዜሽን) ቁጥራቸው እስከ 50 ለሚደርሱ አሸናፊ አትሌቶችና ከሌሎችም እንዳስፈላጊነቱ በሚመርጡ አትሌቶች ላይ የአበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ ይደረጋል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉ የሕክምናና ለምርመራው የሚያግዙ ቁሳቁሶች በመንግሥት ልዩ ትዕዛዝ ተሟልተው እንዲቀርቡ የሚያደርግ አሠራር መፈጠሩም ተነግሯል፡፡ አትሌቶችና የአትሌት ተወካዮች ለምርመራው ሒደት ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በሻምፒዮናው የታዋቂ አትሌቶችን ተሳትፎ በሚመለከትም ክልሎችና ክለቦች ባስመዘገቡት ዝርዝር መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ነው የተገለጸው፡፡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በስተቀር የተቀሩት ክልሎችና ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት የዘንድሮው ሻምፒዮና መክፈቻና መዝጊያው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀጥታ ሥርጭት እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡