የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ ኮንግረሱ የሙስና ምርመራ እንዲደረግባቸው ድምፅ ማሳለፉን በመኮነን፣ ይህንን ኢፍትሐዊነት ያሉትን ውሳኔ እስከ መጨረሻው እንደሚታገሉ ሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ተናግረዋል፡፡
የጥፋተኝነት ምርመራ እንዲደረግባቸው የሚለው ኬዝ ወደ አገሪቱ መንግሥት ሴኔት ከተመራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ንግግር ያደረጉት የብራዚል የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ፣ አለመረጋጋት ቢታይባቸውም የቀረበባቸውን ወንጀል አስተባብለዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በንግግራቸው ኢፍትሐዊነት፣ ያልተገባና ስህተት የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ ተጠቅመዋል፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲያንፀባርቁት የነበረውን አቋማቸውን በድጋሚ በመግለጽ፣ ምንም ዓይነት ሕገወጥ ተግባር እንዳልፈጸሙና ይልቁንም ድራማው በፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
‹‹ከምንም በላይ ዛሬ እንደተበደልኩ ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ ውንጀላ ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት የለውም፤›› በማለት ያላግባብ መወንጀል በጣም መጥፎ ስሜት የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ሩሴፍ ላይ የቀረበው ውንጀላ አስተዳደራቸው የአካውንቲንግ ማታለያዎችን በመጠቀም ከምርጫ በፊት የመንግሥትን ገንዘብ ያላግባብ ተጠቅመዋል የሚል ነው፡፡ እሳቸው ደግሞ የመንግሥት በጀትን በተወነጀሉበት መንገድ መጠቀም በቀደሙት አስተዳደሮችም የነበረ እንደሆነ፣ በወቅቱም በዚህ ማንም ተጠያቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ውንጀላው መሠረት አልባ ነው ሲሉ ለመከራከር ሞክረዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ነገሩ የብራዚል ልሂቃን አገሪቱን ላለፉት 13 ዓመታት ካስተዳደረው ግራ ዘመም የሠራተኛ ፓርቲ ሥልጣን ለመንጠቅ የዘረጉት ወጥመድ ነው፡፡ ‹‹በዚህ አልሽመደመድም፡፡ ይህንን ኢፍትሐዊነት መዋጋት የሚያስችል አቅምም ጥንካሬም አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ ይህ እየተቀነባበረብኝ ነው የሚሉት ሴራ በዴሞክራሲ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነውም ብለዋል፡፡ ምክትላቸውና አፈ ጉባዔ የሆኑት የማይበገሩት ተቀናቃኛቸው ኤድዋርዶ ቹናን ከዚህ ሁሉ ድራማ ጀርባ ያሉት እሳቸው ናቸው በማለት ሩሴፍ ወንጅለዋቸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሩሴፍ ምክትል የሆኑት ቹናም ቢሆኑ በመንግሥት እጅ ከሚገኘው ፔትሮብራስ ከተሰኘው ትልቅ የነዳጅ ኩባንያ አምስት ሚሊዮን ዶላር በመውሰድ ተወንጅለዋል፡፡
በፔትሮብራስ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ብዙ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎችን እንደሚነካም እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሴኔቱ ሩሴፍ ለቀረበባቸው ውንጀላ በፍርድ መዳኘት አለባቸው ብሎ ካመነ፣ ሊተኳቸው የሚችሉትን ምክትል ፕሬዚዳንት ሚኬል ቲመርንም ይጨምራል፡፡ ሩሴፍ ግን በዚህኛው ጉዳይ ስማቸው አልተጠቀሰም፡፡
‹‹ምንም ዓይነት ገንዘብ የመቀበልና ያላግባብ ክፍያ የመፈጸምም ውንጀላ የለብኝም፡፡ የተወነጀልኩት በውጭ ባንኮች አካውንት ስላለኝ ብቻ ነው፤›› የሚሉት ሩሴፍ፣ በተቃራኒው እሳቸው ላይ የተነሳውን ውንጀላ የሚመሩት ሰዎች ደግሞ የተወነጀሉ መሆናቸው የነገሩን ኢፍትሐዊነት የሚያሳይ እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡
ሩሴፍ ላይ ምርመራ ይደረግ አይደረግ በሚለው ላይ ባለፈው እሑድ በኮንግረሱ ድምፅ የተሰጠ ሲሆን፣ ይህ በነሐሴ ወር ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለች ያለችውን፣ ለአሠርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ የገባችውንና በሙስና እየተመሳቀለች የምትገኘውን ብራዚል መንታ መንገድ ላይ ጥሏታል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት አገሪቱ ከመቼውም በተለየ ሁኔታ በእጅጉ ተከፋፍላለች፡፡ ብዙዎች ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ለግብር ከመጠን በላይ ከፍተኛ መሆን፣ እንዲሁም ለዝቅተኛ ደረጃ የሕዝብ አገልግሎት ተጠያቂ የሚያደርጉት ሩሴፍን ነው፡፡ በተቃራኒው ሌሎች በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ከድህነት አረንቋ በማውጣቱ የሩሴፍ የሠራተኛ ፓርቲ ዋጋ ይገባዋል በማለት በሩሴፍ ላይ የተጀመረው ምርመራ ፀረ ዴሞክራሲ እንደሆነ እየተከራከሩ ነው፡፡
ሰኞ ዕለት ከታችኛው የተወካዮች ምክር ቤት የሩሴፍን ውንጀላ የሚመለከተው ሰነድ ወደ ሴኔቱ መላኩን ተከትሎ፣ የሩሴፍ ህልውናን የማስጠበቅ ትግል የሚያተኩረው የሕግ አውጪውን ድጋፍ በማግኘት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
ሕግ አውጪው በሁለት ሳምንት ውስጥ በሩሴፍ ጉዳይ ላይ ድምፅ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ብዙኃኑ ሩሴፍ ለፍርድ ይቅረቡ ብለው ድምፅ ከሰጡ ለጊዜው ከሥልጣን እንዲወርዱና ምክትላቸው እንዲተኳቸው ይደረጋል፡፡
ተንታኞች እንደሚሉት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሩሴፍ በሥልጣናቸው መቆየት አይቻላቸውም፡፡ ምክንያቱም ለረዥም ጊዜ በጥምር መንግሥታቸው ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎችን ድጋፍ እንኳ እያገኙ አይደለምና፡፡
የብራዚል ታዋቂ ጋዜጦች በርዕስ አንቀጾቻቸው በአገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት እየተጋረጠ ያለውን አደጋ እያመላከቱ ነው፡፡ የሥራ ማቆም አድማዎችና የዕለት ከዕለት የተቃውሞ ሠልፎች እንዳይከሰቱ ያስጠነቀቀ ጋዜጣም አለ፡፡
በአገሪቱ ተወዳጅ በነበሩት ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫ ታጭተው የፕሬዚዳንትነቱን መንበረ ሥልጣን የያዙት ሩሴፍ፣ በአጭር ጊዜ አድናቆትን አትርፈው በፖለቲካ ጨዋታና በመሪነት ብቃትም ተጨብጭቦላቸው ነበር፡፡
የሩሴፍ መሠረታዊ ውንጀላ የበጀት ጉድለትን ከመንግሥት ባንኮች ገንዘብ በመውሰድ ለመሸፈን መሞከር ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ግን የመንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ከሆነው ፔትሮብራስ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሩሴፍ የጥምር መንግሥት ውስጥ ላሉ ፖለቲከኞች እንዲሰጥ አድርገዋል፣ የፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸውም ከዚሁ የነዳጅ ኩባንያ በተወሰደ ገንዘብ ተደግፏል በማለት ይወነጅሉዋቸዋል፡፡