የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው አሠራር መሠረት አገናኝ አባላት ከዚህ ቀደም ሲሠሩበት የነበረውን ደንበኛ ወክሎም ሆነ በራሳቸው የማገበያየት ሥርዓት የሚለውጥ በመሆኑ፣ ይህ አሠራር ተግባራዊ መደረግ የለበትም የሚል ቅሬታ ከአገናኝ አባላቱ ቀርቦበታል፡፡ ምርት ገበያው ግን የአገናኝ አባላቱን ጥቅም የሚጎዳ አሠራር እንዳላመጣ በመግለጽ አስተባብሏል፡፡
ይህንን ተከትሎ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ፣ በአዲሱ አሠራር መሠረት አገናኝ አባላት በሁለት ወገን ሻጭና ገዥን ወክለው ግብይት የሚፈጽሙበት አሠራር የገበያውን ተዓማኒነት ለማስፈን የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አንድ አገናኝ አባል ሁለቱም ሻጭና ገዥን በመወከል የሚገበያይበት አሠራር በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ወቅት በግልጽ የሚታይ የተዓማኒነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ መውደቁን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም አንድ ግለሰብ ሁለት ወገንን ወክሎ እንደሻጭም እንደገዥም ከሚሠራ ይልቅ፣ አንዱን በመምረጥ እንዲሠራ ማድረጉ ከዚህ ቀደም ለሁሉም አባላት ተገልጾና የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በተገኙበት ተብራርቶ ወደዚህ አሠራር እንደሚገባ ምርት ገበያው ይፋ ካደረገ መቆየቱን አቶ ኤርሚያስ አስታውቀዋል፡፡ አዲስ አሠራርም ሳይሆን ከዚህ ቀደም በምርት ገበያው የቡና ግብይት ሕግ ላይ በግልጽ የተደነገገ አሠራር መሆኑንና ንግድ ሚኒስቴር ያወጣው አዲስ መመርያም ሳይሆን የምርት ገበያው ማኔጅመንት የወሰነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ አሠራር መሠረት የአገናኝ አባላት ጥቅም በምንም መልኩ እንደማይነካ የሚናገሩት አቶ ኤርሚያስ፣ ይልቁንም አንድ አገናኝ አባል የሁለት ወገን መረጃ በመያዙ ምክንያት ግብይቱ ላይ ያሳድር የነበረውን ተፅዕኖ እንደሚቀርፈው አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ካለፈው ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ አገናኝ አባላት ሚናቸውን እንዲለዩ የተደረገውም በዚሁ አግባብ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በስድስት ቀናት ውስጥ አሳውቁ የተባለው ከገዥና ሻጭ አንዱን በመወከል ምርጫቸውን እንዲያሳውቁ እንጂ እስከ መጪው ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ አገናኝ አባላቱ በምርት ገበያው ማገበያየት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሻጭን ለመከወል የመረጡ አገናኝ አባላት ከዚህ ቀደም የነበሯቸውን ገዥ ደንበኞች ለሌሎች እንዲስረክቡ፣ በተመሳሳይም ገዥን ለመወከል የመረጡ ደግሞ ሻጭ ደንበኞችን ለሌሎች አገኛኝ አባላት የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ በመሆኑ ምንም የጥቅም ጉዳት እንደማይከሰት፣ ገበያው የሁለቱን ወገን ሚዛን አስጠብቆ እንደሚሔድ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 350 ያህል ወንበር ያላቸው አባላት ያሉት ምርት ገበያው፣ ግብይት ፈጻሚና አገናኝ አባላትን ያካተተ ነው፡፡ እዚህም የሙሉና የውሱን አባላትን ያቀፈ ሲሆን፣ ሙሉ የአባልነት መብት ያላቸው አባላት ቋሚ ወንበር ያላቸው፣ ግዥና ሽያጭንም በራሳቸውና በሌሎች በኩል ያለገደብ ማከናወን የሚችሉ ናቸው፡፡ ውሱን አባላት የሚባሉት የአንድ ዓመት የግብይት መብት ያላቸው፣ በሻጭነት አለያም በገዥነት ካልሆነ በቀር በሁለቱም ወገን ግብይት መፈጸም የማይችሉ ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ መተግበር የጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ አንድ ሺሕ ግብይት ፈጻሚ አባላት ሠልጥነው የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ቢጠበቅም፣ እስካሁን 600 ብቻ መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ይህም የግንዛቤ ችግር የፈጠረው መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ገልጸው፣ አባላቱ እንዲህ ባሉ አቅምን በሚያጎለብቱ የግብይት ሥርዓቱን ተዓማኒነትና ዘመናዊነት በሚያጎለብቱ ሥራዎች ላይ መሳተፍና አቅማቸውን ማዳበር እንደሚገባቸው አስታውቀዋል፡፡