Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አናዳጅ ሆኖ የሰነበተው የነዳጅ እጥረት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ካለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች እንደወትሮዋቸው ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ አልቻሉም፡፡ በየነዳጅ ማደያዎቹ ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ባለአሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት ለሰዓታት መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል፡፡ በማግሥቱም እጥረቱ ብሶ ከንጋት እስከ ምሽት ጠብቀው ነዳጅ ማግኘት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ነዳጅ እንደጨረሱ ባስታወቁ የነዳጅ ማደያዎች ሳይቀር ከአሁን አሁን ነዳጅ ይመጣል በሚል ተስፋ የሚታዩት ረዣዥም ሰልፎች እስከትናንት ምሽት ድረስ ዘልቋል፡፡ በየመንገዱም ነዳጅ አልቆባቸው የሚፋጉ መኪኖችም ይታዩ ነበር፡፡

  ወትሮ በወር መጨረሻ ላይ ይታይ የነበረው መጨናነቅ በዚህ ወቅት መታየቱ ያልተለመደ ከመሆኑ አልፎ፣ ለቀናት መዝለቁ በተለይ በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ የሚያዝያ ወር የነዳጅ ዋጋ ተመን በመጋቢት ወር በነበረው የመሸጫ ዋጋ ይቀጥላል የሚለው የሕዝብ ማስታወቂያ በንግድ ሚኒስቴር ከተነገረ ከአሥር ቀን በኋላ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት፣ ብዙም ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን ለቀናት መዝለቁ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች አስከትሏል፡፡

  ነዳጅ ለመቅዳት ማደያዎችን ያጨናነቁ ተሽከርካሪዎችን በሙሉ ሊያስተናግድ የሚችል ነዳጅ ባለመኖሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ያለሥራ እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ጭነው ለመጓዝ የተዘጋጁ የጭነት ተሽከርካሪዎች በነዳጅ እጦት ጉዟቸው ተስተጓጉላል፡፡

  አቶ እንዳለ ገብረማርያም በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የተሰማሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ማልደው ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ከሚገኘው የሺ ቶታል ነዳጅ ማደያ ናፍጣ ለመቅዳት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ በመቅረቱ፣ በዕለቱ ለማከወን ያቀዱትን ሥራ ለመሥራት አልቻሉም፡፡ ነዳጅ በማጣታቸው ዕለታዊ ሥራቸውን ለመከወን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በማግሥቱም ከብዙ ድካም በኋላ ነዳጅ ቢያገኙም፣ ለአንድ ቀን ከግማሽ ሥራቸው በመስተጓጎሉና ማስረከብ የነበረባቸውን ሥራ ባለማስረከባቸው ይጠብቁት የነበረውን ክፍያ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

  በተመሳሳይ በተለይ በናፍጣ የሚሠሩ ታክሲዎች ነዳጅ አጥተው አንድና ሁለት ቀናት ለመቆም ተገድደዋል፡፡ ይህም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞና ማክሰኞ ለትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ሆኗል፡፡

  የላዳ ታክሲ ሾፌር የሆነው የ23 ዓመቱ አሊ መሐመድ የሰሞኑ የነዳጅ እጥረት ሥራዬን አስተጓጉሎብኛል ይላል፡፡ ‹‹ሰኞ ማልጄ ተነስቼ ሳሪስ አካባቢ በሚገኝ የኦይል ሊቢያ ማደያ ቤንዚን ለመቅዳት ተሰልፌ፣ ነዳጅ መቅዳት የቻልኩት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ነው፤›› ይላል፡፡ በዚህ መሀል ግን ወደ አራት የኮንትራት ሥራዎች አምልጠውታል፡፡ በዕለታዊው ገቢው ላይም ተፅዕኖ መፍጠሩን ያስረዳል፡፡

  የሰሞኑን የነዳጅ እጥረት የዕለት ሥራን ማስተጓጎሉ ብቻ ሳይሆን ነዳጅ ለማግኘት በየማደያዎቹ የተሰለፉ ተሽከርካሪዎች መንገድ መዝጋት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ እንቅስቃሴን የበለጠ አጨናንቆት ነበር፡፡  

  ከወትሮው በተለየ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ፣ ሰሞኑን የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ዋነኛ መንስዔ በጂቡቲ ድንበር አካባቢ የተከሰተው ጎርፍ ነዳጅ ለማጓጓዝ ባለማስቻሉ ነው፡፡ ለሁለት ቀናት የኢትዮ ጂቡቲን የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የገታው ጎርፍ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ በማዘግየቱ፣ በነዳጅ ሥርጭት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ተብሏል፡፡

  የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰሞኑ የነዳጅ እጥረት የተፈጠረው ከጂቡቲ ወደብ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው ጎርፍ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በመግታቱ ነው፡፡

  ለሁለት ቀናት ነዳጅ ጭነው ወደ መሀል አገር ለመምጣትም ሆነ ነዳጅ ለመጫን ወደ ጂቡቲ በማቅናት ላይ የነበሩትን ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ፣ በመላ አገሪቱ ለተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

  ለሰሞኑ የነዳጅ እጥረት አንዱ ምክንያት ይህ ቢሆንም፣ ሌላም ምክንያት ነበረው ተብሏል፡፡ ይህም የአገሪቱን የናፍጣ ፍጆታ ከ50 በመቶ በላይ ከምታቀርበው ኩዌት ነዳጅ ጭና ወደ ጂቡቲ ወደብ የተንቀሳቀሰችው መርከብ ለአሥር ቀናት ዘግይታ ጂቡቲ በመድረሷ ነው፡፡ የመርከቧ መዘግየት ወደ አገር ውስጥ መግባት የነበረበት ነዳጅ በሚፈለገው መጠን እንዳይገባ በማድረጉ፣ ለሰሞኑ ችግር እንደ ሌላ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ የቀን የናፍጣ ፍላጎት 6.5 ሚሊዮን ሊትር የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት በቀን ከ7.2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ናፍጣ ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ነዳጅ ማጓጓዝ ባለመቻሉ በተፈጠረው ችግር፣ በነዳጅ ማደያዎች ተይዞ የነበረው ናፍጣ እያለቀ ሄደ እጥረቱ ሊፈጠር መቻሉም ተመልክቷል፡፡ በየቀኑ ይጠበቅ የነበረውና ወደ አገር ውስጥ መግባት የነበረበት ነዳጅ በመዘግየቱም፣ ከመጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቻ ወጥቶ እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡

  ባለፉት ሁለት ቀናትም ከሁሉም መጠባበቂያዎች ወደ አሥር ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወጥቶ መሰራጨቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ሙሉ ለሙሉ ሊያቃልል አልቻለም፡፡ አሁን የተፈጠረው እጥረት በአቅርቦት እጥረት ያለመሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ችግሩ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይቀረፋል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በቀን ወደ 200 የሚሆኑ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ መሀል አገር እየገቡ በመሆኑ፣ ችግሩን እንደሚቀርፉ ያላቸውን እምነት አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

  መጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻዎቹ ውስጥ ነዳጅ ካለ እንዲህ ዓይነት እጥረት ሲፈጠር ለምን አፋጠኝ ምላሽ አይሰጥም? ተብለው የተጠየቁት አቶ ታደሰ፣ መጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻዎቹ ያሉት ራቅ ብለው ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ከመጠባበቂያ ማከማቻዎቹ ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት የሚወስደው ጊዜ ረጅም በመሆኑ እንጂ ሌላ ችግር የለውም፤›› ብለዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የተፈጠረው እጥረት አሁንም እየታየ ነው፡፡ በየማደያው የሚታዩት ረጃጅም ሰልፎች ሙሉ ለሙሉ አልቀነሱም፡፡ ነዳጅ ለማግኘት ሰዓታት እየተጠበቀ ሲሆን ምንም ነዳጅ የሌላቸው ማደያዎችም አሉ፡፡ይህ ችግር እስከትናንት ድረስ እየታየ ነው፡፡

  ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ችግር ያለ ሲሆን፣ እንደ ኮምቦልቻ ያሉ ከተሞች ቤንዚን ከጠፋ ስድስት ቀናት እንደተቆጠሩ እየተነገረ ነው፡፡ በድሬዳዋና በሐዋሳም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በነዚህ ከተሞች እስከትናት ቀትር ድረስ በከተሞቹ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰልፎች ታይተዋል፡፡ ከኮምቦልቻ የኖክ ነዳጅ ማደያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የናፍጣ ችግር ባያጋጥማቸውም ቤንዚን ከቀረበላቸው ግን አንድ ሳምንት ሊሞላቸው ነው፡፡

  በአገሪቱ የነዳጅ እጥረት የተከሰተው ሰሞኑን ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም ቀደም በተደጋጋሚ የሚከሰት ነው፡፡ እንደሰሞኑ ላለው ነዳጅ እጥረት ምክንያት የሆኑ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ግን፣ ድጋሚ እንዳይከሰት ለማድረግ አማራጭ የነዳጅ ማስገቢያ መንገዶች መፈለግ ግድ የሚል መሆኑን ያመለክታል፡፡ አቶ ታደሰ እንደገለጹት፣ እንዲህ ዓይነት ክፍተት ሲያጋጥም በጣም አጣዳፊ ለሆኑት ለፀጥታ፣ ለመከላከያና ለመሳሰሉት ከመጠባበቂያው ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ ለኅብረተሰቡም ይሰጣል ብለዋል፡፡ ትልቁ ችግር ነዳጅ የሚገባው በጂቡቲ በር ብቻ በመሆኑ ነው የሚሉት አቶ ታደሰ፣ ከዚህ በኋላ ግን ሌሎች አማራጮችን ማሰብ ማስፈለጉን ያምናሉ፡፡

  ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣው ዓመታዊ ወጪ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል፡፡ በየዓመቱም የነዳጅ ፍጆታም ጨምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አገር ከምታስገባው  50 በመቶውን ናፍጣና 75 በመቶውን ቤንዚን ከኩዌት ታስገባለች፡፡

  የኢትዮጵያ የቀን የቤንዚን ፍጆታ ከ1.2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ሆኗል፡፡ የናፍጣ ፍጆታ ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ሊትር ደርሷል፡፡ የአውሮፕላን ነዳጅ የፍጆታ መጠኑም ወደ ሁለት ሚሊዮን ሊትርና ሲሆን፣ የነጭ ጋዝ ፍጆታ ደግሞ 260,000 ሊትር ይደርሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት 13 አካባቢ መጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻዎች ያሉ ሲሆን፣ 360 ሺሕ ሜትሪ ኪዩብ ነዳጅ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች