Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጣም በጠዋት ቤታቸው ደርሷል]

  • ዛሬ እንዴት በጠዋት መጣህ?
  • አሁንማ ሁሉን ነገር ተውኩ፡፡
  • ከእንቅልፍህ በግፊ አልነበረም እንዴ የምትነሳው?
  • አሁንም እንደ ድሮው አይደለሁም፤ ነዳጅ ጠፍቷል፡፡
  • የምን ነዳጅ ነው?
  • ያው ቢራውንም፣ ድራፍቱንም እርግፍ አድርጌ ትቸዋለሁ፡፡
  • ምን ተገኘ?
  • የኑሮ ንረቱ ነዋ፡፡
  • ምን አልከኝ?
  • ክቡር ሚኒስትር ከዚህች ደመወዝ ላይ የቤት ኪራይ ተከፍሎ፣ ቀለብ ተቆርጦ፣ የልጅ ትምህርት ቤት ተከፍሎ ቢራና ድራፍት ማሰብ ከባድ ነው፡፡
  • እሱስ ልክ ነህ፡፡
  • በዛ ላይ ደግሞ እቆጥባለሁ፡፡
  • ባንክ ታጠራቅማለህ ማለት ነው?
  • ኧረ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች በየወሩ እቆጥባለሁ፡፡
  • ጎብዘሃል ማለት ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የቤት ኪራይ እኮ እያንገበገበኝ ነው፡፡
  • ይኸው መንግሥት ኮንዶሚኒየም የሚሠራው ለዚህ አይደል እንዴ?
  • ክቡር ሚኒስትር ግን አይረዱኝም?
  • ምንድን ነው የምረዳህ?
  • ኮንዶሚኒየም አያሰጡኝም?
  • ስማ ከቀን ተሌት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ስዋጋ እንደምውል ታውቃለህ አይደል?
  • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ስለዚህ አንተም እንደማንኛውም ዜጋ ዕድልህን መጠበቅ አለብህ፡፡
  • ያው ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ነገር ያለሰው አይሆንም ብዬ ነው፡፡
  • ይኼ የኪራይ ሰብሳቢዎች ፀባይ ነው፡፡
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይልቁን ቤቱ እንዲደርስህ ከፈለግክ አንድ ነገር እንድታደርግ እመክርሃለሁ፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ተግተህ ፀልይ፡፡

  [በቅርቡ በነበረው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ በሕገወጥ መንገድ ቤት ይዞ የነበረና ሰብሮ ከያዘው ቤት የተባረረ የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ደወለላቸው]

  • ሄሎ ጋሼ!
  • አቤት ጐረምሳው፡፡
  • ተሰቃየሁ እኮ ጋሼ፡፡
  • ምን ሆነህ?
  • ኧረ ይኸው የቤት ኪራይ እያንገበገበኝ ነው፡፡
  • ምን አባቴ ላድርግህ?
  • አንድ ወሬ ሰምቼ ነበር፡፡
  • ምን ሰማህ?
  • በቅርቡ የ40/60 ቤቶች ዕጣ መውጣቱ አይቀርም፡፡
  • የተቀማኸው ቤት ዓይነት ማለት ነው?
  • ይኼኛውማ በጣም የተሻለ ነው፡፡
  • በምንድን ነው የተሻለው?
  • በሁሉ ነገሩ ጋሼ፡፡ የቤቱ ጥራት ብትል፣ ሎኬሽኑ ብትል ብቻ በሁሉ ነገር የተሻለ ነው፡፡
  • መጽሐፉ ግን እውነት ነው የሚናገረው ማለት ነው?
  • የቱ መጽሐፍ?
  • ነገር ሁሉ ለበጎ ነው የሚለው ነዋ፡፡
  • እንዴት ጋሼ?
  • ምንም እንኳን ያኛው ቤት ቢወሰድብህም፣ ይኸው አሁን ከዚያ የተሻለ ውስጥ ትገባለሃ፡፡
  • ታሰጠኛለህ ጋሼ?
  • የእናትህን ውለታ እኮ በምንም መክፈል አልችልም፡፡
  • እግዚአብሔር ያክብርህ ጋሼ፡፡
  • ስማ አስተምራ ለዚህ ያበቃችኝ እናትህ መሆኗን አትርሳ፡፡
  • አመሰግናለሁ ጋሼ፡፡
  • አደራዋም አለብኝ፡፡
  • ጋሼ ቤቱን ለማግኘት ግን 40 በመቶ መቆጠብ አለብኝ፤ ለዚያም ነው 40/60 የተባለው፡፡
  • ችግር የለም ለሱም መላ አለኝ፡፡
  • የምን መላ?
  • ለአንተ በሌላ ፕሮግራም አሰጥሃለሁ፡፡
  • በምን ፕሮግራም?
  • በዜሮ/መቶ ፕሮግራም!

  [የክቡር ሚኒስትሩ አክስት ደወሉ]

  • እንዴት ነሽ እቴቴ?
  • ሰላም ነህ ወንድም?
  • አለሁልሽ ዛሬ ከየት ተገኘሽ?
  • ዘመድ ተደውሎ አይጠየቅም ብለህ ነው?
  • ልጆቹ እንዴት ናቸው?
  • ያው አንዱ እየተማረ ነው፤ ታላቁ ደግሞ ትምህርቱን ጨርሶ እየሠራ ነው፡፡
  • በርትተዋል ማለት ነው?
  • ይኸው ቁጭ አድርገው ገንዘብ እየላኩ የሚያስተዳድሩኝ እነሱ አይደሉ እንዴ?
  • በጣም ደስ ይላል እቴቴ፡፡
  • አንተን መቼም ለዘላለም ያኑርልኝ፡፡
  • ምን አደረግኩ ብለሽ ነው?
  • አንተ አይደለህ እንዴ ለመሥሪያ ቤታችሁ የመጣውን ስኮላርሽፕ ለሁለቱም ያሰጠህልኝ፡፡
  • ቀጣይ አገር ተረካቢዎች እነሱ ናቸው ብዬ ነዋ፡፡
  • ቢሆንም ከስንቱ ወጣት ላይ ነጥቀህ አይደል እንዴ ለእነሱ የሰጠህልኝ?
  • ኧረ ምንም አታስቢ እቴቴ፡፡
  • ለማንኛውም ዛሬም አንድ ነገር ላስቸግር ነው የደወልኩት፡፡
  • ምን እቴቴ?
  • በቅርቡ የ40/60 ቤቶች ዕጣ ይወጣል፡፡
  • እሺ፡፡
  • እና ያው አንተን የመሰለ ወንድም እያለኝ መቼም ቤቱ አያመልጠኝም ብዬ ነዋ፡፡
  • እቴቴ ቤት አለሽ አይደል እንዴ?
  • 40/60 የለኝማ?
  • እሱማ አውቃለሁ፡፡
  • እውነት ወንድም አማረኝ በቃ፡፡
  • በስተርጅና አረገዝሽ እንዴ?
  • ባላረግዝም በቃ አማረኝ፡፡
  • ምንድን ነው ያማረሽ?
  • 40/60!

  [ክቢር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

  • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • እስቲ ስለ 40/60 የቤቶች ፕሮግራም ንገረኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር በቅርቡ የቤቶቹ ዕጣ ይወጣል፡፡
  • ለማን ነው የሚወጣው?
  • መጀመሪያ 100 ፐርሰንት ለከፈሉት ይሰጣል፡፡
  • እሺ፡፡
  • ለመሆኑ ምን ያህል ሰው ነው የተመዘገበው?
  • ከ160 ሺሕ በላይ ነው፡፡
  • ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ 100 ፐርሰንት ከፍሏል?
  • ወደ 11 ሺሕ የሚሆነው ተመዝጋቢ ሙሉ ሒሳብ ከፍሏል፡፡
  • አሁን ለ11 ሺውም ቤቱ ይሰጣል?
  • አይ የተጠናቀቁት ቤቶች ብቻ ናቸው ዕጣ የሚወጣባቸው፡፡
  • ለመሆኑ ቤቶቹ የት አካባቢ ነው የሚሠሩት?
  • አብዛኞቹ በከተማችን እምብርት ቦታዎች ላይ ነው የሚገነቡት፡፡
  • ጥራታቸውስ እንዴት ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር የከተማችንን ገጽታ በደንብ ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡
  • ትቀልዳለህ?
  • ከተማችን ኒውዮርክ ልትመስል ትችላለች ስልዎት፡፡
  • ሳትቀደም ቅደም ነዋ የምትለኝ?
  • ኢትዮጵያ ትቅደም ነው ያሉኝ?
  • ኧረ እኔ ልቅደም!

  [ከውጭ የመጣች የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ቢሯቸው መጣች]

  • አገሩን ለመድሽ?
  • ምን ምርጫ አለኝ?
  • ለነገሩ ጓዝሽን ጠቅልለሽ ነው አይደል የመጣሽው?
  • አገርሽ ገብተሽ ኑሪ ባልከኝ መሠረት እዚሁ ለመኖር ወስኛለሁ፡፡
  • ምን እያደረግሽ ነው ታዲያ?
  • ይኸው ቤት ለመግዛት እየተሯሯጥኩ ነው፡፡
  • አገኘሽ ታዲያ?
  • ምን አገኛለሁ ብለህ ነው? ዋጋው እኮ አይቀመስም፡፡
  • ሪል ስቴቶቹን ሞከርሻቸው?
  • የሚታመን ሪል ስቴት እኮ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡
  • እና ምን አሰብሽ?
  • ዛሬ አመጣጤ አንድ ነገር ላማክርህ ነው፡፡
  • ምንድን ነው?
  • 40/60 የሚሉት የቤቶች ፕሮጀክት በቅርቡ ዕጣው ሊወጣ ነው አሉ፡፡
  • አዎን ሰምቻለሁ፡፡
  • ስማ ቤቶቹ የተሠሩበት ቦታ ብትለኝ፣ የቤቶቹ ጥራት ብትለኝ በጣም አሪፍ ነው፡፡
  • እና ምን አሰብሽ?
  • እነዚህ ቤቶች ውስጥ ብገባ በጣም አሪፍ ነው፡፡
  • ቤቶቹ እኮ የመንግሥት ናቸው፡፡
  • ታዲያ አንተ አይደለህ እንዴ መንግሥት?
  • ለመሆኑ ተመዝግበሻል?
  • አልተመዘገብኩም ግን አንተ ታስመዘግበኛለሃ፡፡
  • መቼ ነው የማስመዘግብሽ?
  • አሁን!

  [የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]

  • ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር ልጠይቅዎት ነበር፡፡
  • ምንድን ነው?
  • በቅርቡ የ40/60 የቤት ዕጣ እንደሚወጣ ሰምተዋል?
  • አንቺም ተመዝግበሻል እንዴ?
  • መመዝገብ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ክፍያውን ከፍያለሁ፡፡
  • ከየት አምጥተሽ?
  • ያው እኔና ባሌ ዘመናችንን ሙሉ ያጠራቀምናትን ገንዘብ ለዚህ ቤት ክፍያ አውለነዋል፡፡
  • ሰው ጨምሯል ልበል?
  • ተርፎኝ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እና ተቸግረሽ ነው ሙሉውን የከፈልሽው?
  • ክቡር ሚኒስትር የቤት ኪራይ ቢኖርብዎት፣ የቤት ጉዳይ በሚገባ ይገባዎት ነበር፡፡
  • አሁን ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ፈልገሽ ነው?
  • ያው ቤቱ እንዲደርሰኝ ቢተባበሩኝ ብዬ ነው?
  • ስሚ ከመቼ ጀምሮ ነው ይህ የኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብ የያዘሽ?
  • እ….
  • ከእኔ ጋር እየሠራሽ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ትይዣለሽ?
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለማንኛውም እኔ ብቻ ነኝ የተኛሁት ማለት ነው?
  • ምን አሉኝ?
  • አሁን ነቅቻለሁ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋ እየሄዱ ነው]

  • ዛሬ ምንድን ነው ጃሙ?
  • ሰው ተሠልፎ ነው፡፡
  • ይኼ ሁሉ የመኪና ሠልፍ ምንድን ነው?
  • ከተማ ውስጥ እኮ ነዳጅ የለም፡፡
  • ለዚህ ነው ይኼ ሁሉ ሠልፍ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔማ ሌላ ነገር መስሎኝ ነበር፡፡
  • ሌላ ምን?
  • ሕዝቡ ሰላማዊ ሠልፍ ሲከለከል ሌላ ሠልፍ የጀመረ መስሎኝ፡፡
  • የምን ሠልፍ?
  • የመኪና ሠልፍ!

  [ሾፌሩ በመንገዳቸው ላይ የነበረ የ40/60 ፕሮጀክት ለክቡር ሚኒስትሩ ሲያሳያቸው ገብተን ካላየነው ብለው ፕሮጀክቱን አዩት፡፡ ወዲያው ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

  • እስከዛሬ የት ነበርሽ?
  • አገሬ ነዋ፡፡
  • ለመሆኑ 40/60 የሚባለውን የቤቶች ፕሮግራም ታውቂዋለሽ?
  • አዎን አውቀዋለሁ፡፡
  • ታዲያ እንዴት አልነገርሽኝም?
  • የእናንተው ፕሮጀክት እኮ ነው፡፡
  • ለመሆኑ ቤቶቹን አይተሻቸው ታውቂያለሽ?
  • ያው በመንገድ ሳልፍ በርቀት ነዋ፡፡
  • ዛሬ አንድ ያለቀ ፕሮጀክት አይቼ በጣም ልዩ አይደል እንዴ?
  • ወደድከው?
  • ሪል ስቴት ከምንገዛ እኮ እዚህ ይሻለን ነበር፡፡
  • ላለው ይጨመርለታል ስለሚል፣ ይህንንም መጨመር ነዋ፡፡
  • ዛሬ ያልደወለልኝን ዘመድ ጠይቂኝ፡፡
  • ለምንድን ነው የደወሉልህ?
  • ቤቱን አሰጠን ብለው ነዋ፡፡
  • እና ምን አሰብክ?
  • ለእነሱም ለእኛም የሚበቃንን ቤት መውሰድ አለብን፡፡
  • ምን ያህል ይበቃናል?
  • ሙሉውን መውሰድ ነው እንጂ፡፡
  • ሙሉ ምኑን?
  • ሙሉ ብሎኩን!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...

  ወጋገን ባንክ ከገጠመው ቀውስ በማገገም በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ትርፍ አገኘ

  ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው ከተስተጓጎለባቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ በዕረፍት ቀናቸው እርጅና የተጫጫናቸው አጎታቸውን ለመጠየቅ ቢሄዱም ሚኒስትሩ ራሳቸው ተጠያቂ ሆነዋል]

  ዛሬ እንዴት ትዝ አልኩህ ክቡር ሚኒስትር? ልትመዛት ያሰብካት ነገር አለች ማለት ነው? እንዴት? ክቡር ሚኒስትር ብለህ ጠራኸኛ?! ክቡር ሚኒስትር አይደለህም እንዴ? እንደዚያ ብለህ በጠራኸኝ ቁጥር አንድ ያልተዋጠለህን ነገር ታነሳለህ።...

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር! ቀድሜ ቀጠሮ እንዲያዝልኝ ስጠይቅ እንደገለጽኩት በተቋሙ ሠራተኛ ተወክዬ ነው የመጣሁት። እንዴ? አንተ የእኛ ተቋም ባልደረባ አይደለህም...

  [የተቃዋሚ ፓርቲው ትይዩ ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደውለው መንግሥት በሙሰኞች ላይ ለመውሰድ ስላሰበው የሕግ ዕርምጃ ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]

  ሄሎ… ማን ልበል? ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል? የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡  አቤት? ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡ ኦ... ገባኝ… ገባኝ...  ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል? ትይዩ...