የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እየተጠናከረ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ ፈተና እንደሆነበት ለፓርላማው አሳወቀ፡፡
ከአገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ዝውውር እንደ ቀድሞው በእንስሳት ጀርባ ሳይሆን በተሽከርካሪዎችና በሞተር ብስክሌቶች የታጀበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አዘዋዋሪዎችም ከሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ወንጀለኞች ጋር ቡድን ፈጥረው እየሠሩ መሆኑም ተወስቷል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኮንትሮባንድ ወደ አገር ሲገቡ በባለሥልጣኑ ቁጥጥር ሥር የወደቁ ዕቃዎች ግምታዊ ዋጋ 450 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ፣ የባለሥልጣኑ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ንጉሤ ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡
ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት በቁጥጥር ሥር ከዋለው ወደ አገር ሊገባ የነበረ የኮንትሮባንድ ዕቃ በ61 በመቶ ወይም በ189 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተጨማሪ በመርካቶ የሚታየው የታክስ ሥወራና ሕገወጥ ንግድ ሌላው ፈተና መሆኑን፣ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተሩ ለፓርላማው አብራርተዋል፡፡
‹‹በመርካቶ አካባቢ የሚታየው የታክስ ሕግ ተገዥነት ችግር በአጠቃላይ የታክስ ሥርዓቱና የንግድ እንቅስቃሴውን ፍትሐዊነት የሚገዳደር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት ባለሥልጣኑ ከወትሮው የተለየ ትኩረት በመስጠት በጥናት ላይ የተመሠረተና ዋና ዋናዎቹ የሕግ ጥሰቱ ተዋናዮች በሆኑ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በየካቲትና በመጋቢት ወር ብቻ መርካቶን ጨምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ በታክስ ሥወራ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ በማይቆርጡና በኮንትሮባንድ ላይ በተሰማሩ በ109 ድርጅቶችና በ177 ግለሰቦች ላይ (አብዛኛው መርካቶን ያካትታል) በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሕጉ መሠረት ማጣራትና የምርመራ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ከባለሥልጣኑና ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ፣ ከሕዝብ ክንፍና ከነጋዴው ኅብረተሰብ የተወከሉባቸው ስድስት ጥምር የተለያዩ ኮሚቴዎች በማቋቋም፣ የቤት ምዝገባና ቁጥጥር ሥራ በማካሄድ ያለ ንግድ ፈቃድ የሚነግዱትንና ደረሰኝ የማይቆርጡትን የማጣራት ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም. በአጠቃላይ 165.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ 94.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉንም ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡