የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖራቸው ቼክ በማውጣት (በመጻፍ) ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ሰጡ፡፡
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የተመሠረተባቸውን ክስ እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት መፈጸም አለመፈጸማቸውን በሚመለከት እንዲናገሩ ጠይቋቸው፣ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም ወንጀለኛም አይደለሁም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ተጠርጣሪው የተመሠረተባቸውን ክስ ክደው በመከራከራቸው ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ እንደሚያስረዱለት የቆጠራቸውን ምስክሮች አቅርቦ እንዲያሰማ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ግንቦት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አቅርቦ ለማሰማት ተቀጥሯል፡፡
የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ማለትም ፍርድ ቤቱ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅሰው አቶ ኤርሚያስ የተመሠረተባቸው ክስ ዋስትና እንደማያስከለክል በ600 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደ ቢሆንም፣ አለመለቀቃቸውን በመጠቆም በእስር እንዲቆዩ ያደረጋቸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መመርመር ዳይሬክቶሬት እንዲጠየቅላቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ፖሊስ አቶ ኤርሚያስን ለምን እንዳለቀቃቸው ማብራሪያ እንዲሰጠው ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ለተለያዩ ስድስት ግለሰቦች የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖራቸው በድምሩ 4.9 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ ጽፈው ሰጥተዋል ተብለው የተመሠረተባቸውን ስድስት ክሶች ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዋስትና ጉዳይ ላይ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ከተከሳሹ ጋር ክርክር ማድረጉንና ለብይን ለሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. መቀጠሩም መዘገቡ አይዘነጋም፡፡