– ለሁለት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጇል
በጋምቤላ ክልል በአኝዋና በኑዌር ዞኖች በሚገኙ 13 ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ለፈጸሙት አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠየቀ፡፡
የምክር ቤቱ አባላት መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ባፀደቁት የብሔራዊ ሐዘን መግለጫ የውሳኔ ሐሳብ ላይ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥትና የጋምቤላ ክልል መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን የታፈኑትን ዜጐች ለማስመለስና በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስዱ እየጠየቅን፣ አካባቢውን ወደነበረበት ለመመለስና የነዋሪውን ማኅበረሰብ ሰላማዊ ኑሮ ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል፤›› ሲል አሳስቧል፡፡
በተጠቀሱት ሁለት ዞኖች በሚገኙ መኩይ፣ ጆሮ፣ ጐግጃካዎና ላሬ ወረዳዎች በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ንፁኃን ዜጐች ባልጠበቁት ጊዜና ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ላይ በነበሩበት ወቅት፣ ፈጽሞ የሰው ክብር በሌላቸውና በጥፋት ዓላማ በተሰባሰቡ የታጣቂ ቡድኖች አረመኔያዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የውሳኔ ሐሳቡ ያስታውሳል፡፡
አሁን ባለው መረጃ መሠረት 208 ዜጐች መገደላቸውንና 108 የሚሆኑ ሕፃናትና እናቶች ደግሞ በታጣቂዎቹ ታፍነው መወሰዳቸውንም ይገልጻል፡፡
‹‹በንፁኃን ዜጐች ላይ በደረሰው ጉዳት ምክር ቤቱ ከፍተኛ ሐዘን የተሰማው ሲሆን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወላጆቻቸውና ለመላ የአገራችን ሕዝቦች መፅናናትን ይመኛል፤›› ብሏል፡፡
በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 22(2) መሠረት በጥቃቱ ሕይወታቸው ለጠፋ ዜጐች ረቡዕ ሚያዝያ 12 ቀንና ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ፣ የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች፣ በኢትዮጵያ ንግድ መርከቦችና ጀልባዎች ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል፡፡
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ሌሊት በተፈጸመው ግድያና ጠለፋ በተመለከተ መንግሥት በአፋጣኝ ምላሽ አልሰጠም በማለት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወቀሳ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡