Wednesday, May 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ራሱን ይውቀስ!

በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚደርስ አደጋ የአገር አደጋ ነው፡፡ ሐዘኑም የጋራ ነው፡፡ ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋና በበርካታ ሕፃናት ላይ የተፈጸመው ታፍኖ የመወሰድ አደጋ እንደ አገር ሁሉንም ወገን ማስቆጨትና ማንገብገብ ያለበት ቢሆንም የአገርን ሰላም፣ የሕዝብ ፀጥታና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ድንበር አቋርጦ የሚገባ ጠላት በሕዝብ ላይ ግድያና ዝርፊያ እንዳይፈጽም የመከላከል ኃላፊነት ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ጥቃቱን የፈጸመውን የገባበት ገብቶ ለፍርድ ማቅረብ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች በተገቢው ጊዜና ሥፍራ በፍጥነት ለመፈጸም አለመቻል ያስጠይቃል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ለምን ዜጎቹን ከጥቃት ለመከላከል አልቻለም ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ለዚህም ጥያቄ ጥርት ያለ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡ ራሱንም መውቀስ እንዲሁ፡፡

ሌላው መንግሥት የሚጠየቀው የጋምቤላ ክልል አገሪቱ ካላት አንፃራዊ ሰላም አንፃር ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ ውስጥ በተደጋጋሚ አደጋዎች ደርሰው የዜጎች ሕይወት ተገብሮበታል፡፡ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ በተጨማሪ ክልሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጎረቤት አገር ስደተኞች ይስተናገዱበታል፡፡ አገሪቱ በስደተኞች አያያዝ ከምትመሰገንባቸው ሥፍራዎች አንዱ ቢሆንም፣ ስደተኞችን ተከትለው የሚመጡ የፀጥታ ሥጋቶች ይታያሉ፡፡ የጋምቤላ ክልል ካለው ልዩ ባህሪ አንፃር በቀላሉ ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ክስተቶች ስለሚታዩ፣ መንግሥት ሰሞኑን የደረሰውን አደጋ ቀድሞ ለመከላከል ባለመቻሉ ምንም ዓይነት ማመካኛ ማቅረብ አይችልም፡፡ እንደ ዓይን ብሌን ጥበቃ የሚያስፈልገው ክልል ከጎረቤት አገር እየተንደረደረ የተለያዩ ዓላማዎችን ያነገበ ጠላት እንደሚመጣበት እየታወቀ፣ አካባቢውን በንቃት አለመጠበቅና ወገንን መከላከል አለመቻል ያንገበግባል፡፡ መንግሥት ራሱን ሊወቅስ ይገባል፡፡

በሌላ በኩል እዚህ አገር ውስጥ ብሔራዊ አደጋ ሲደርስ በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ ሥርዓት የሚኖረው መቼ ነው? አገሪቱ ምን ያህል ሰው ሲሞትባት ነው ብሔራዊ ሐዘን በፍጥነት ታውጆ ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ የሚውለበለበው? ባለፈው ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ድንበር አቋርጠው የገቡ ታጣቂዎች 208 ዜጎችን ገድለውና 102 ሕፃናት አፍነው መውሰዳቸው ወዲያውኑ ሲታወቅ፣ ፓርላማው አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቶ ብሔራዊ ሐዘን ማወጅና አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል ተገቢውን የአፀፋ ምላሽ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠት የነበረበት መቼ ነው? የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ የአገር ጌጥ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ሐዘን መግለጫ ጭምር ነው፡፡ አገር ሲከፋው፣ ሐዘኑንና ቁጣውን ሲገልጽ ጭምር መገለጫው ሰንደቅ ዓላማው ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በፍጥነት ለማካሄድና መሪር ሐዘንን ለመግለጽ ምን ያህል ዜጎች መሞት ነበረባቸው? ምን ያህልስ መታገት ነበረባቸው?

በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን በተፈጸመው ግድያና አፈና ምክንያት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ቤተሰቦች ማፅናናት፣ ዕርዳታ መስጠትና መልሶ የማቋቋም ጉዳይ ውለታ የመዋል ወይም ሐዘን የመግለጽ ሳይሆን የመንግሥት የራሱ ግዴታ ነው፡፡ ቤት ለቤት ታፍነው የተወሰዱ 102 ሕፃናት ቁጥራቸው ብቻ ሳይሆን እነማን እንደሆኑ በስም ሊታወቁ ይገባል፡፡ የሞቱትንም ቢሆን ለቅሶ ከመድረስ በላይ የራሱ የመንግሥት ለቅሶ መሆኑን ጭምር መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ታፍነው የተወሰዱትን ሕፃናት አስለቅቆ የማምጣት ኃላፊነትም የመንግሥት ነው፡፡ መላው አገር ሐዘን ላይ ተቀምጦ የሚያሰላስለው እነዚያ ተጠልፈው የተወሰዱ ሕፃናት በአስቸኳይ ተለቀው ከተረፉት ቤተሰቦቻቸው ጋር ስለመቀላቀላቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥፍራ ሆነው በወገኖቻቸው ላይ የሚደርስ ሰቆቃን ማውገዝ አለባቸው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው የአገሪቱ ቆዳ ስፋት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ወገኖች ነውረኛ ግድያዎችንና ጭፍጨፋዎችን ማውገዝ አለባቸው፡፡ የጋምቤላ ዓይነቱ የሰሞኑ አደጋ ሲከሰት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ለወገኖቻቸው መድረስ አለባቸው፡፡ ከየትኛውም አካባቢ በወገኖቻቸው ላይ የሚደርስ ጥቃት የጋራ መሆኑን በማሰብና ሐዘኑም የጋራ መሆኑን በመረዳት፣ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ በአንድነት ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል፡፡ በአገሪቱ አንደኛው ክፍል የተፈጸመ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ጉዳቱ የጋራ መሆኑን በመገንዘብ፣ በጋራ ማውገዝና በኅብረት መቆም የግድ ነው፡፡ በተለይ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ወገኖችና ቤተሰቦች በሐሳብና በቁሳቁስ መርዳትም የዜግነት ግዴታ መሆኑን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያሉ ዜጎች አንዳቸው ከአንዳቸው የሚበላለጡበት ምንም ምክንያት ስለሌለ፣ የጋምቤላው ጥቃትም በዚህ መንፈስ በጋራ ሊወገዝ ይገባል፡፡

ሚዲያው በተለይ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሰቃቂ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ድንጋጤ ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አገር በልጆቿ ዕልቂት ማቅ ለብሳና በሐዘን ተኮማትራ አስረሽ ምቺው ጭፈራዎችና ደንታ ቢስነቶች አደብ መግዛት አለባቸው፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር ደንገጥ ማለትና ከቡረቃ ውስጥ ወዲያው መውጣት ይለመድ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እንደተስተዋለው አገርና ሕዝብ በሐዘን ውስጥ ወድቀው ዳንኪራን ጋብ አድርጎ ከሕዝብ ጋር አለመቆም ያስነቅፋል፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ አይረቤ አሠራሮች በሙሉ ሊቆሙ ይገባል፡፡ ሚዲያዎች ለአንደኛው ወገን የሚያሳዩትን አዘኔታ ለሌላውም ያለአድልኦ ማሳየት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚታዩ አላስፈላጊ ድርጊቶችም ዕርምት ይፈልጋሉ፡፡ አስደንጋጭ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ቁጥር የዜጎችን ጉዳት ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ ማዋል በጣም እየተለመደ ነው፡፡ በዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ወገኖችን ከማፅናናት ይልቅ መናቆር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም የተሳሳቱትን በማረምና በመገሰጽ ኃላፊነትን መወጣት ይጠቅማል፡፡

በአጠቃላይ የአገር ጉዳይ የጋራ እስከሆነ ድረስ ሁሉም እንደየድርሻው አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ አገሪቱ ሐዘን ላይ ተቀምጣ በግፍ ያለቁ ልጆቿን በምታስብበት በዚህ ወቅት እንደ አገር በጋራ ማሰብ ይበጃል፡፡ በተለይ አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት በዚህ አጋጣሚ የታዩበትን ጉድለቶች በሰከነ መንገድ ይመልከት፡፡ አደጋው እንደተሰማ ከአገሪቱ መሪ ጀምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረትና ፍጥነት ምን ይመስላል? በተፈጸመው አስከፊ ድርጊት ላይ ስለሚሰጠው ምላሽና ተያያዥ ጉዳዮች ያለው ሕጋዊ የአገር ሥርዓት ምን ይመስላል? አደጋውን አስቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ እስከ ምላሽ አሰጣጡ ድረስ ያለው ዝግጁነት እንዴት ይገመገማል? ሕዝቡስ ከአደጋው ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት ላይ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ግዳጁ የተመሰከረለት የመከላከያ ሠራዊት ያላት አገር፣ ድንበር አቋርጠው በገቡ ታጣቂዎች ዜጐቿ ሲጨፈጨፉ ሕዝብ ምን ይሰማዋል? መንግሥት ለእነዚህና ለሌሎች መሰል ጥያቄዎች ምን ምላሽ አለው? ራሱን እየወቀሰ ምላሹን ለሕዝቡ በግልጽ ይንገር!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...