Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባንኮች ለቦንድ ግዥ ካዋሉት ገንዘብ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ተመለሰላቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮች ከሚሰጡት ከእያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ ያህሉን እያሰሉ ለቦንድ ግዥ ካዋሉት ገንዘብ ውስጥ፣ የቦንድ ግዥው ከተፈጸመ አምስት ዓመት የሞላውን ገንዘባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መለሰ፡፡ የተመለሰው የገንዘብ መጠንም ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

የግል ባንኮች ከእያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ ለቦንድ ግዢ ማዋል ከጀመሩ ወዲህ እስካሁን ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ የፈጸሙ ቢሆንም፣ አሁን የተመለሰላቸው አምስት ዓመት ለሞላው የቦንድ ግዥ ያወጡት ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ሰሞኑን ለባንኮች ተመላሽ የተደረገው ገንዘብ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ መመርያው ተግባራዊ ሲደረግ ለቦንድ ግዥው ያዋሉት ገንዘብ ሦስት በመቶ ወለድ ታክሎበት አምስት ዓመት ሲሞላው እንደሚመለስላቸው ተመልከቶ ነበር፡፡ ሰሞኑን ተመላሽ የተደረገላቸው ገንዘብ ሦስት በመቶ ወለዱ ያልታከለበት ነው፡፡ ይህም የሆነው አሁን ለተመለሰላቸው ገንዘብ የሚታሰበው ወለድ ቀደም ብሎ ተሰልቶ፣ በየዓመቱ ብሔራዊ ባንክ ይከፈላቸው ስለነበር እንደሆነ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከዚህ በኋላም ለቦንድ ግዥው አምስት ዓመታት የሞላው ገንዘብ በየዓመቱ ከነወለዱ እየተሰላ ለባንኮች ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከመመርያው መውጣት በኋላ ወደ ሥራ የገቡት ባንኮች ግን የቦንድ ግዥውን መፈጸም ከጀመሩ አምስት ዓመታት ያልሞላቸው በመሆኑ፣ እንደ ሌሎቹ ባንኮች ተመላሽ አልተደረገላቸውም፡፡ ከገንዘቡ መመለስ በኋላ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የባንኮች ኃላፊዎች ይኼንን የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃን ያልተጠበቀ ነው ብለውታል፡፡ ገንዘቡ መመለስ መጀመሩ በተለይ ባንኮች በአሁኑ ወቅት ላለባቸው የገንዘብ እጥረት ዕፎይታ የሰጠ በመሆኑ የብሔራዊ ባንክን ሰሞነኛ ዕርምጃ አወድሰዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ሰሞኑን ገንዘቡ የተመለሰላቸው አብዛኛዎቹ ባንኮች በቅርቡ ካጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ ከብሔራዊ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል ሲያስችላቸው፣ ቀሪውንም ገንዘብ ለብድር በማዋል ብድር የመስጠት አቅማቸውን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከፍ ያደርጋል፡፡ በተለይ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሲበደሩ የሚከፍሉት ወለድ ከፍተኛ ስለነበር፣ ለቦንድ ግዥ ካዋሉት ገንዘብ ያገኙትን የተወሰነውን ለብሔራዊ ባንክ ዕዳ ክፍያ ማዋላቸው ዕዳቸውን ለማቃለል ዕድል እንደሰጣቸውም ተገልጿል፡፡ ከዚህ በኋላም ቀሪው ገንዘብ በየዓመቱ የሚመለስላቸው ከሆነ ለቦንድ ግዢው የሚያውሉት ገንዘብ ላይከብዳቸው ይችላል የሚል አስተያየት ያላቸውም አሉ፡፡

ይህ የብሔራዊ ባንክ መመርያ 16ቱን የግል ባንኮችና በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠቀለለውን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን የሚመለከት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደ ግል ባንኮች ሁሉ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ተመላሽ የሚደረግለት አምስት ዓመት የሞላው የቦንድ ግዥ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የባንኮችን ህልውና ይነካል ተብሎ ብዙ ሲያነጋግር የነበረው ይህ መመርያ የተሠጋውን ያህል ባንኮችን አልጐዳም ቢባልም፣ ለቦንድ ግዥው ያዋሉትን ገንዘብ በእጃቸው ላይ ቆይቶ ቢያበድሩት ኖሮ ያገኙ የነበረውን ጥቅም ግን ያሳድግላቸው እንደነበር ብዙዎችን ያስማማል፡፡   

በተለይ ባንኮቹ ከፍ ባለ ወለድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ቦንድ ሲገዙበት የሚታሰብላቸው ሦስት በመቶ በመሆኑ ተጐጂዎች ያደርጋቸዋል የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ባንኮቹ ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶውን እያሰሉ ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድደው መመርያ አሁንም በሥራ ላይ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች