Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥትን 84.9 ሚሊዮን ብር በማሳጣት የተጠረጠሩ የመሬት ባለሙያዎች ተከሰሱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ተጠርጣሪዎቹ ከንፋስ ስልክ ላፍቶና ጉለሌ ክፍላተ ከተሞች ናቸው

መንግሥት በሊዝ ቢሸጠው ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከ84.9 ሚሊዮን ብር በላይ ስውር በሆነ መንገድ በመመሳጠር እንዲያጣ በማድረግ ወንጀል የተጠረጠሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶና ጉለሌ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ በተለያየ ደረጃና የሥራ መደብ በመሥራት ላይ የነበሩ 26 የመሬት ባለሙያዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ እና አንደኛ ወንጀል ችሎቶች ባቀረባቸው ክሶች እንዳብራራው፣ ተጠርጣሪዎቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በድምሩ መንግሥት ሊያገኝ ይችል የነበረውን 84,980,894 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን በዝርዝር በክሱ ገልጿል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሕግ ጉዳዮች አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ በዛብህና የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ አቶ ሀብተወልድ ወልደፃዲቅ፣ ከአራት ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ለአራቱም ግለሰቦች የተለያየ ስፋት ያለው መሬት ያላግባብ እንዲይዙ በማድረግ መንግሥት 22,137,953 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

በዚያው ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ የሕግ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ አቶ ዳርጌ ሞረዳ፣ የቴክኒክ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያዎች አቶ ጌትነት ተካ፣ ፍቅርተ በላይ፣ መረጃ አሰባሰብና አጣሪ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አብርሃም ሐጐስና የፕሮጀክት ዴስክ ኃላፊ አጥናፍወርቅ ፀጋዬ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ሕገወጥ ሰነድ ሕጋዊ በማስመሰል የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለአንድ ግለሰብ በመስጠታቸው፣ መንግሥት 6,731,285 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ጠቅሷል፡፡

ከሰነድ አልባ ይዞታዎች ጋር በተገናኘ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ ሆነው ይሠሩ የነበሩት አቶ ዳርጌና ሀብተወልድ፣ ከክፍለ ከተማው ስለሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ተሻሽሎ የወጣውን መመርያ ቁጥር 18/2006 አንቀጽ 23ን በመተላለፍ፣ ለሦስት ግለሰቦች የተለያየ ስፋት ያለው መሬት ሕጋዊ አስመስለው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ፈርመው በመስጠት፣ መንግሥት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከመሬት ሊያገኝ ይችል የነበረውን 20,193,855 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

አቦነህ መንገሻ፣ ሀብተወልድ ተክለማርያምና ሙለታ ፀሐዬ በዚያው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ይዞታዎች የሕግ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ፣ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪና የመስተንግዶ ፕሮጀክት ዴስክ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ የተለያየ ስፋት ያለው መሬት ለሦስት ግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሠርተው በመስጠት፣ መንግሥት 11,205,570 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የይዞታ ንብረት (የኮንዶሚኒየም) ማስረጃ አሰጣጥ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ሰይፉ፣ የሕግ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያ አቶ በረከት ወርቁና የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ነገዎ፣ ሕጋዊ ያልሆነን ይዞታ ሕጋዊ በማስመሰል ለአንድ ግለሰብ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሠርተው በመስጠት፣ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያው አበራ ገለታም 242 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመንግሥት ቦታ ለግለሰብ ጨምረው በመስጠት፣ መንግሥት 656,425 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

የጉለሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሥዩም ደግሞ፣ በፍርድ አፈጻጸም የዕግድ ትዕዛዝ የተሰጠባቸውን ንብረቶች አንድ ግለሰብ በሕገወጥ መንገድ እንዲያገኙ በማድረጋቸው፣ መንግሥት 21,673,964 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን በክሱ ተዘርዝሯል፡፡ በክፍለ ከተማው በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩት አቶ ሰለሞን ደስታ፣ ወርቁ ከበደና አባተ አራጋው ከአንድ ግለሰብ ጋር በመመሳጠር ንብረትነቱ የኪራይ ቤቶች የነበረን ቤት በመቀላቀል የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመሥራት ግለሰቡ እንዲወስዱ በማድረጋቸው፣ መንግሥት 438,840 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

መንግሥት 1,290,576 ብር እንዲያጣ በማድረግ ተጠርጥረው የተከሰሱት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመስተንግዶ ፕሮጄክት ዴስክ ኃላፊ አቶ አባተ አራጋው፣ የኮንዶሚኒየም ማስረጃ አሰጣጥ ቡድን አስተባባሪ አቶ ተሾመ ዓብይ፣ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያዎች አቶ ኢሳያስ ይታየው፣ አበራ ገለታና ትዕግሥት አበበ ናቸው፡፡ ፈጽመዋል የተባለው ወንጀልም ከግለሰብ ጋር ተመሳጥረው የመንግሥትን ይዞታ ከግል ይዞታ ጋር በማቀላቀል ሕጋዊ አስመስለው የይዞታ ማረጋገጫ መስጠታቸው መሆኑን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ክፍላተ ከተሞች የተከሰሱት 26ቱም ተጠርጣሪዎች፣ ከሰነድ አልባና ከመንግሥት ይዞታ ጋር በተገናኘ መንግሥት ከ84.9 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ በማድረጋቸው፣ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምና የጥቅም ተጋሪ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱ ተነቦላቸው መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለግንቦት 3 እና 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች